1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ሕወሓት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ለአንድ ዓመት በመራዘሙ ተቃወመ

ሰለሞን ሙጬ
ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 3 2018

ህወሓት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ለአንድ ዓመት መራዘሙ በፕሪቶሪያው ግጭት የማቆም ስምምነት ፈራሚዎች ውይይት ያልተደረገበት፣ ከእውቅናየ ውጪ የተላለፈ እና የኢትዮጵያ መንግሥት የተናጠል ውሳኔ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል አለ።

https://p.dw.com/p/5C1ZB
ህወሓት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ለአንድ ዓመት መራዘሙ ከእውቅየ ውጪ የተወሰነ ነው አለ
ህወሓት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ለአንድ ዓመት መራዘሙ ከእውቅየ ውጪ የተወሰነ ነው አለምስል፦ Million Hailesilassie/DW

ሕወሃት በፌደራል መንግስት ላይ ያቀረበው ተቃዉሞ

 

ህወሓት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ለአንድ ዓመት መራዘሙ በፕሪቶሪያው ግጭት የማቆም ስምምነት ፈራሚዎች ውይይት ያልተደረገበት፣ ከእውቅናየ ውጪ የተላለፈ እና የኢትዮጵያ መንግሥት የተናጠል ውሳኔ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል አለ። ህወሓት የፌዴራል መንግሥት ይህንን ያደረገው "የፕሪቶርያውን ስምምነት ሙሉ በሙሉ ጥሶ" መሆኑን ገልጿል።ብሔራዊ ባይቶ ዓባይ ትግራይ (ባይቶና) በበኩሉ ውሳኔውን "በሕግ ተቀባይነት ያለው ወይም በፖለቲካዊ ሕጋዊ እንደሆነ ተደርጎ ሊወሰድ የማይችል" ሲል ተቃውሞታል።

በጉዳዩ ላይ ከሕግ አንፃር አስተያየት የሰጡን ግለሰብ የህወሓት መግለጫ ያለውን ተጨባጭ ኹኔታ ይቀይራል የሚል ግምት ባይኖራቸውም "ስምምነቱ አለ ከተባለ፣ ሥራው በስምምነቱ መሠረት እየቀጠለ አይደለም የሚል እንድምታ ያለው ይመስላል" ብለዋል።

ሥራው "በስምምነቱ መሠረት እየቀጠለ አይደለም" - የሕግ ባለሙያ

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደርን በፕሬዝዳንትነት ለአንድ ዓመት የመሩት ሌፍትናንት ጀነራል ታደሰ ወረደ ከሚያዝያ 01 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ አስተዳደሩን ለተጨማሪ አንድ ዓመት እንዲመሩ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሥልጣናቸው ተራዝሟል።

ይህንን ተከትሎ የፕሪቶሪያ ዘላቂ ግጭት የማቆም ስምምነት ፈራሚ የሆነው፣ ግን ሕጋዊ ሰውነቱ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰረዘው ህወሓት፣ "የኢትዮጵያ መንግሥት እየፈፀማቸው የቆዩ" ያላቸውን ስምምነቱን "የመጣስ ተግባራት በመቀጠል" ከስምምነቱ በፊት በነበሩ ባላቸው ሕጎችን "ስምምነትቱን ሙሉ በሙሉ ጥሶ" ጊዜያዊ አስተዳደሩን አራዝሟል ሲል ገልጿል።

ህወሓት "የሁለቱም ፈራሚ አካላት ውይይት ያልተደረገበት" ያለው ይህ ውሳኔ ከእውቅናው ውጪ የተላለፈ እና የፌዴራሉ መንግሥት "የተናጠል ውሳኔ" ስለመሆኑ ሚያዝያ 01 ቀን 2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ጠቅሷል።

ቅድሚያ ለሰብዓዊ መብቶች - በኢትዮጵያ የተባለው ሀገር በቀል የሲቪክ ድርጅት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ መብርሂ ብርሃነ ከህወሓት መግለጫ ተነስተው ሥራው "በስምምነቱ መሠረት እየቀጠለ አይደለም" የሚል እንድምታ ያለው ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል" ብለዋል።

"በመጀመሪያው በነበረው አቶ ጌታቸው ነበረ ማለት ነው። ከዛ በኋላ የአሁኑ ጀነራል መጡ ማለት ነው። ሁለተኛው ላይም በተመሳሳይ የእነሱ [ህወሓት] ይሁንታ ነበረው። አሁን በሦስተኛው ላይ ግን ምንም የእነሱ በሰጡት መግለጫ እነሱ ምንም ኢንቮልቭ አላደረግንም የሚል ነገር ነው ያለው። ስለዚህ በስምምነቱ መሠረት እየቀጠለ አይደለም የሚል አንድምታ ያለው ይመስለኛል።"

ጄነራል ታደሰ ወረደ
ህወሓት የፌዴራል መንግሥት ይህንን ያደረገው "የፕሪቶርያውን ስምምነት ሙሉ በሙሉ ጥሶ" መሆኑን ገልጿልምስል፦ Office of the Prime Minister-Ethiopia

ባይቶና የፌዴራሉን መንግሥት ውሳኔ አጣጥሏል

ብሔራዊ ባይቶ ዓባይ ትግራይ (ባይቶና) ውሳኔው "ከባድ የሕግ፣ የፖለቲካ እና የሕገ መንግሥታዊ ሥጋቶችን ያስነሳል" በማለት "ተቀባይነት ያለው ወይም በፖለቲካዊ ሕጋዊ እንደሆነ ተደርጎ ሊወሰድ የማይችል" ሲል የፌዴራሉን መንግሥት ውሳኔ አጣጥሏል። ትግራይ የጊዜያዊ አስተዳደሩን ማራዘም "ለመቀበል ምንም አይነት አስገዳጅ የሕግ ግዴታ የለባትም" ያለው ባይቶና ክልሉ በዚህ ርምጃ የተገደበ ሊሆን እንደማይችል ገልጿል። 

አቶ መብርሂ ህወሓት ሌፍተናንት ጀነራል ታደሰ ወረደን በመጀመርያው ሹመታቸው አምኖባቸው ያቀረባቸው በመሆነ አሁን የአስተዳደሩን መራዘም የተናጠል ዉሳኔ ነው ቢለውም ያለውን ተጨባጭ ኹኔታ ይቀይራል የሚል ግምት እንደሌላቸው ገልፀዋል።

"ከዚህ በፊት ጀነራል ታደሰ ስለሆነ በስልጣን ላይ የነበሩት፣ አሁንም እሳቸው ስለሆነ የቀጠሉት ያን ያህልበተግባር ለውጥ ላያመጣ ይችላል የሚል ግምት ነው ያለው ማለት ነው። ከውጤት አንጻር ካየነው።"

የፕሬዝዳንቱ ሥልጣን መራዘም የፌዴራል መንግሥቱ ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ነው - ትንሳኤ ሰባ እንደርታ

ዶቼ ቬለ በዚህ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት የሥራ ጊዜ መራዘም ዙሪያ ያነጋገራቸው የትንሳኤ ሰባ አንደርታ ፓርቲ

ሊቀመንበር አቶ ከበደ አሰፋ ርምጃው ከፌደራል መንግስቱ የሚጠበቅ አለመሆኑን እና እንዳሳዘናቸው ገልፀው ነበር።

"ከአንድ ኃላፊነት ከሚሰማው መንግሥት የሚጠበቅ ነው ብለን አናምንም" ያሉት አቶ ከበደ "ሕጋዊ ሕልውናውን ያጣ" ያሉት ህወሓት ያቀረበውን ፕሬዝዳንት የሥልጣን ዘመን ማራዘም "የፌዴራል መንግሥቱን ግዴለሽነት እና ኃላፊነት የጎደለው ተግባር" ያመለክታል ሲሉ አጥብቀው ተችተዋል።

ሰለሞን ሙጬ

ታምራት ዲንሳ