1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ህወሓት ከ2013 ዓ.ም በፊት የነበረው የትግራይ ክልል ምክር ቤት ወደ ሥራ እንዲመለስ ወሰነ

ሰለሞን ሙጬ
ሰኞ፣ ሚያዝያ 12 2018

ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ከጥቅምት 24 ከ2013 ዓ.ም በፊት የተመረጠው የትግራይ ክልል ምክር ቤት ወደ ሥራ እንዲመለስ መወሰኑን አስታወቀ። የፖለቲካ ፓርቲዎች እና አንድ የሲቪክ ድርጅት፣ የህወሓት ውሳኔ በክልሉ ዳግም የጦርነት ሥጋት እንደሚፈጥር ገልፀዋል።

https://p.dw.com/p/5CVcF
የህዝባዊ ወያነ ሃርነት ትግራይ ህወሃት አርማ
የህዝባዊ ወያነ ሃርነት ትግራይ ህወሃት አርማ ያለበት ሰንደቅ ፎቶ ከማኅደርምስል፦ Million Haileyessus/DW

ስጋት ያስከተለው የህወሃት ውሳኔ

 

ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ከጥቅምት 24 ከ2013 ዓ.ም በፊት የተመረጠው የትግራይ ክልል ምክር ቤት ወደ ሥራ እንዲመለስ መወሰኑን አስታወቀ። በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሕጋዊ ሰውነቱ የተሰረዘው ህወሓት ለሁለት ቀናት ያካሄደውን ስብሰባ ተከትሎ ትናንት ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ መንግሥት የፕሪቶሪያን ስምምነት «እንደ ሌላ የማጥፊያ መሣሪያ ለመጠቀም እየጣረ« ነው ሲል ከሷል። በጉዳዩ ላይ አስተያየቱ የሰጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና አንድ የሲቪክ ድርጅት፣ የህወሓት ውሳኔ በክልሉ ዳግም የጦርነት ሥጋት እንደሚፈጥር ገልፀዋል። የህወሓት መግለጫ በግልጽ ባይጠቅሰውም የፕሪቶሪያው ዘላቂ ግጭት የማቆም ስምምነት መፍረሱን የሚያመለክትና አወንታዊ ውጤት የማይኖረው እንደሆነም ጠቅሰዋል።

ህወሓት ሚያዝያ 7 እና 8 ቀን 2018 ዓ.ም ስብሰባ ማካሄዱን ገልፆ ውጤቱን ትናንት እሑድ ሚያዚያ 11 ቀን ይፋ ያደረገ ሲሆን፣2.8 ሚሊዮን ሕዝብ የመረጠው ያለውንና ከ2013 ዓ.ም በፊት የነበረውን የክልሉን ምክር ቤት ወደ ሥራው እንዲመለስ መወሰኑን ጠቅሷል።

ህወሓት የፕሪቶሪያው ዘላቂ ግጭት የማቆም ስምምነት እንዲፈረም፣ ስምምነቱም ወደ ዘላቂ የሰላም ስምምነት እንዲሸጋገር ጥረት ማድረጉን ገልፆ በፌዴራል መንግሥቱ መፈፀም የነበረባቸው ያላቸው ጉዳዮች «አልተፈፀሙም» ሲል በመግለጫው አስፍሯል።

በተጨማሪም የክልሉን የአስተዳደር ወሰን አለመመለስ፣ የድርጅቱን እውቅና መንፈግ፣ የትግራይ ሕዝብ እርስ በእርሱ እንዳይተማመን ለማድረግ መጣር፣ የመንግሥት ሠራተኞችን ደመወዝ መከልከል፣ በትግራይ ላይ ዳግም ከበባ ማድረግና ዳግም ጦርነት ለመክፈት መዘጋጀት፤ የሚሉ ምክንያቶችን በፌዴራል መንግሥቱ ላይ በማንሳት ለውሳኔው ምክንያት አድርጎ ዘርዝሯል።

የፕሪቶሪያው ስምምነት ሲፈረም ሕወሓትን ወክለው ከፈረሙት ከፍተኛ ባለሥልጣናት መካከል አንዱ የነበሩት እና በኋላ ስምረት ፓቲን ያቋቋሙት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ ይህንን የህወሓትን መግለጫ አጥብቀው ተቃውመውታል።

«እጅግ አሳሳቢ» ያሉት ይህ የህወሓት ውሳኔ «የፕሪቶሪያን ስምምነት ውድቅ የሚያደርግ እርምጃ» እንደሆነ ገልፀዋል።

የአረና ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር እና የፓርቲው የሕግ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ካህሳይ ዘገዬ በበኩላቸው፣ በወቅቱ ትግራይ ክልል ተደርጎ የነበረው ምርጫ «ሕገ-ወጥ ነው» በሚል አለመሳተፋቸውን አስታውሰው፣ ይህንን ውሳኔ «ተቀባይነት የለውም» ብለዋል። ይህንን ሲሉ መፍትሔ ያሉትን በማመላከት ጭምር ነው።

«መልካም ውጤት ይመጣል የሚል እምነት የለንም» - አረና

«በጊዜያዊ አስተዳደሩ ህወሓት አንዱ ራሱ አንድ አካል ነው። እዚያ ጋር ሆኖ ምንም ያመጣው መፍትሔ የለም። አካታች እንዳይሆንም እንቅፋት ከሆኑት አንዱ እሱ ነው። ስለዚህ መልካም ውጤት ይመጣል የሚል እምነት የለኝም።»

የፌዴራል መንግሥት የፕሪቶሪያውን ዘላቂ ግጭት የማቆም ስምምነት ተከትሎ ያቋቀመውን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት የሥራ ዘመን ባለፈው ሳምንት በአንድ ዓመት አራዝሟል። ሕጋዊ ሰውነቱ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰረዘው ህወሓት የጊዜያዊ አስተዳደሩ የሥራ ጊዜ መራዘም ላይ ተሳትፎም፣ እውቅና የለኝም በሚል ውድቅ አድርጎታል።

የፕሪቶሪያ ስምምነት ፈራሚዎች
ለሁለት ዓመታት በፌደራል መንግሥትና በህወሃት መካከል ትግራይ ክልል እና በሰሜን ኢትዮጵያ የተካሄደውን ጦርነት ያስቆመው የፕሪቶሪያው ስምምነት ፈራሚዎችፎቶ ከማኅደርምስል፦ PHILL MAGAKOE/AFP

ህወሓት ስምምነቱ በግልጽ ፈርሷል ባይልም ይዘቱ ግን ያንን ያሳያል - ሲቪክ ድርጅት

ቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች ኢትዮጵያ የተባለውና የትግራይን ጉዳይ በቅርበት የሚከታተለው የሲቪክ ድርጅት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ መብርሂ ብርሃነ እንደሚሉት ህወሓት በግልፅ ባይለውም ባወጣው መግለጫ የፕሪቶሪያው ስምምነት መፍረሱን የሚጠቁም ነው።

«በግልጽ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ፈርሷል ባይልም፣ ይዘቱ ግን ያንን ነው [የሚያሳየው]። ምክንያቱም ከጦርነቱ በፊት የተደረገ ምርጫ ውጤት አልባ እንደሆነ በስምምነቱ የተደረሰበት ጉዳይ ነው።»

የህወሓት ውሳኔ ሊያስከትልየሚችለውን ውጤት በተመለከተም አቶ መብርሂን ጠይቀናቸው፤ «በውሳኔው መሠረት የሚሄዱ ከሆነ በክልሉ እና በፌዴራል መንግሥቱ መካከል ያለው ግንኙነት ይቋረጣል ማለት ነው። ትልቁ ሥጋት ምንድን ነው ወደ ጦርነት የመመለስ ሥጋት ይፈጥራል በዋናነት።» ብለዋል። 

ከጎረቤት ሃገራት እና አጎራባች ክልሎች ጋር ያለኝን ትስስር ለማጠናከር እሠራለሁ - ህወሓት

ህወሓት ስም ባይጠቅስም «ከጎረቤት ክልሎችና ከሌሎች የ ኢትዮጵያ ሕዝቦች እንዲሁም ከጎረቤት ሃገራት ሕዝቦች ጋር በማንኛውም ጊዜ ያለውን ትስስር ለማጠናከር እንደሚሠራ» በትናንቱ መግለጫው አሳውቋል። አክሎም ከኢትዮጵያ «ፌዴራል መንግሥት ጋር ያሉ ልዩነቶችን በንግግር ለመፍታት» ፍላጎት እንዳለው ገልጿል። በህወሓት እና በፌዴራል መንግሥት መካከል ያለው ውጥረት እና የግንኙነት መሻከር መስተዋል ከጀመረ ቆየት ብሏል።

ሰሎሞን ሙጬ

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ