ህወሓት ከጉባኤው በኋላ ፊቱን ወደ ጊዜያዊ አስተዳደሩ መልሷል
ሐሙስ፣ ነሐሴ 16 2016ህወሓት በትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ስላለው ውክልና ከፌደራል መንግስቱ ጋር እንደሚነጋገር የፓርቲው ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ተናገሩ። ደብረፅዮን እንዳሉት አስቀድሞ ህወሓትን ወክሎ ወደ ትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር የገባው አመራር አሁን ላይ ከህወሓት ጋር በመለያየቱ ለውጦች ለማድረግ ግዚያዊ አስተዳደሩ ካቋቋሙ አካላት ጋር ውይይት ይደረጋል ብለዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር፥ ከአስተዳደሩ እውቅና ውጭ ማንኛውም ስብሰባ እንዳይደረግ የስራ መመርያ አሰራጭቷል።
በቅርቡ በተጠናቀቀው ጉባኤ የህወሓት ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡ ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ትላንት ለሀገር ውስጥ እና ውጭ መገናኛ ብዙሐን በሰጡት መግለጫ ካነሷቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ፥ የህወሓት ቀጣይ እቅድ የሚመለከት ነው።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እና የህወሃት ውዝግብ
ክፍፍል ላይ ሆኖ ጉባኤ ያደረገው እና አዲስ አመራር መምረጡ ያስታወቀው ህወሓት፥ ፓርቲው ወክለው የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር እየመሩ ያሉ ባለስልጣናትን በአዳዲስ ተሿሚዎች ለመቀየር ግዚያዊ አስተዳደሩ ካቋቋሙ አካላት ጋር ውይይት እንደሚጀምር የህወሓቱ ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ተናግረዋል። በፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት መሰረት የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ከፌደራል መንግስቱ ጋር በተደረገ መግባባት መመስረቱ የገለፁት ደብረፅዮን፥ አሁን በህወሓት አመራር ላይ ለውጦች በመደረጋቸው ህወሓትን ወክለው በግዚያዊ አስተዳደሩ ያሉ አመራሮች ልንቀይር እንችላለን ብለዋል።
አራተኛ ቀኑን የያዘው የሕወሓት ጉባኤ እና የተቃዋሚዎች መግለጫ
ከዚህ በተጨማሪ በፕሪቶሪያ ውል አፈፃፀም ጉዳዮች፣ የህወሓት ሕጋዊነት እና ቀጣይ ፖለቲካዊ ውይይት ማድረግ ዙርያ ከፌደራል መንግስቱ ጋር ህወሓት ንግግሩ እንደሚቀጥል ዶክተር ደብረፅዮን አክለው ገልፀዋል።
ለሁለት የተከፈለው ህወሓት፥ በእነ ዶክተር ደብረፅዮን የሚመራው ቡድን ጉባኤ በማድረግ አዲስ አመራር የመረጠ ሲሆን፥ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸው ረዳ ያሉበት ሌላው ቡድን ደግሞ ለጉባኤው እና ውጤቱ እውቅና አይሰጥም። ባለፈው ሰኞ ዕለት የተገባደደው የህወሓት ጉባኤ ግን፥ ቀጣይ የፖርቲው ሁሉም ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች በጉባኤው በተመረጠ አዲስ አመራር ብቻ እንደሚከወን ገልጿ ነበር።
ሕወሓት በ50 ዓመት ታሪኩ አጋጥሞት በማያውቅ ፈተና ውስጥ እንዳለ ዐሳወቀ
ይህ በእንዲህ እንዳለ በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር፥ ከአስተዳደሩ እውቅና ውጭ ማንኛውም ስብሰባ እንዳይካሄድ ለዞኖች፣ ወረዳዎች እና ሌሎች የአስተዳደር እርከኖች ባሰራጨው የስራ መመርያ አስታውቋል።
አቶ ጌታቸው በየደረጃው ላሉ የአስተዳደር አካላት ባሰራጩት የስራ መመርያ፥ አመራሩ በክረምት ስራዎች፣ አሳሳቢ ሆኖ ያለው የኮሌራ በሽታ መከላከል ተግባራት፣ በተፈናቃዮች መመለስ እንቅስቃሴ ላይ ትኩረቱ ያድርግ ያሉ ሲሆን፥ ከዚህ ውጭ የሚደረግ ነገር ግን ተጠያቂነት እንደሚያስከትል አስጠንቅቀዋል።
ሚሊዮን ኃይለስላሴ
ታምራት ዲንሳ
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር