1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ፖለቲካየመካከለኛው ምሥራቅ

ሃማስ እስራኤልን ያጠቃበት ጥር 7 ፤ 2023 ሲታወስ

ሰኞ፣ መስከረም 27 2017

ጋዛ እንዳልነበረች ሆናለች ፤ ሊባኖስ የጋዛ መንገድ የተከተለች መስሏል ፤ ሞት እና ውድመት እዚህም እዚያም ይሰማል ፤ ከኢራን እና ከምትደግፋቸው ታጣቂዎች ከኋላ እና ከፊት የሚሳኤል እና የሮኬት ዝናብ የሚዘንብባት እስራኤል በቆሰለች ቁጥር ቁጣዋ እያየለ የምትወስደው እርምጃም ሰላማዊን ከጦረኛ ሳይለይ እንዳነፈረ እነሆ አንድ ዓመት ደፈነ ።

https://p.dw.com/p/4lUL0
Jahrestag Terrorangriff der Hamas | Gedenken in Jerusalem - Israel
ምስል REUTERSisrael

አንድ ዓመት የሞላው የሃማስ ጥቃት ቀጣናውን ወደ ቀውስ እየመራው ይሆን ?

ለወትሮም ግጭት ፣ ሰብአዊ ጥፋት እና ቁሳዊ ውድመት የማይለየው ብሎም ሰላም ብርቁ የሆነው የመካከለኛው ምስራቅ የነበረውን የግጭት ጥላቻ ታሪክ በአዲስ አስከፊ ታሪክ የለወጠ  ዕለት ነበር፤ የጎርጎርሳዉያኑ ጥቅምት  7  2023 ወይም መስከረም 26 ቀን 2016 ዓ/ም ፤ 
በቀጣናው መዓት ይዞ የመጣው ያ ክፉ ቀን እነሆ አንድ ዓመት ሞላው ። 
ጋዛ እንዳልነበረች ሆናለች ፤ ሊባኖስ ቤይሩት የጋዛን መንገድ የተከተሉ መስሏል ፤ ሞት እና ውድመት  እዚህም እዚያም ይሰማል ፤ ከኢራን ብሎም ከሊባኖሱ ታጣቂ ቡድን ሄዝቦላ እና ከሁቲ አማጽያን ከኋላ እና ከፊት የሚሳኤል እና የሮኬት ዝናብ የሚዘንብባት እስራኤል በቆሰለች ቁጥር ቁጣዋ እያየለ የምትወስደው እርምጃም ሰላማዊን ከጦረኛ  ሳይለይ እንዳነፈረ እነሆ አንድ ዓመት ደፈነ ። በእስራኤል እና ኢራን መካከል የነገሰው ውጥረት አሜሪካንን አስጠግቷል ፤ ይህ ደግሞ ቀጣናዊ ጦርነት እንዳያስከትል አስግቷል ።
ዕለቱ ቅዳሜ ነው ፤ በአብዛኞቹ ምዕራባዉያን ሃገራት በሽብርተኝነት የተፈረጀው የፍልስጥኤማዊያኑ ታጣቂ ቡድን ሃማስ በፍጹም ያልተጠበቀ እና ድንገተኛ ጥቃት በእስራኤል ላይ ብርቱ ጉዳት አደረሰ ። ጥቃቱ በእርግጥ አፍዝ አደንግዝ ነበር። ከ1100 በላይ እስራኤላዉያን  ተገድለዉበታል፤ ከ250 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ታግተው ተወስደዋል። ይህ ነው እንግዲህ በርካታ የዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞች ጭምር  ሁነቱን ባለማመን ውስጥ ሆነው እስከመዘገብም ያደረሳቸው  ።

 የጋዛ እልቂትና የሰላም ጥሪ
እውነት አላቸው፤ በዓለማችን የስለላ ብቃታቸው ከተመሰከረላቸው እና በመረጃ አነፍናፊነታቸው ኃያል ስም ከገነቡ የስለላ ተቋማት አንዱ የሆነው ሞሳድ ባለቤት የሆነች ሀገር እንደምን እንዲህ ያለ ለዚያውም ዙሪያዋን ከታጠረች ትንሽዬዋ ጋዛ ያልተጠበቀ ጥቃት አስተናገደች ? እንቆቅልሹ ዛሬም ድረስ አልተፈታም። የዶቼ ቬለው ነጋሽ መሐመድ እንደሚለው የሃማስ ድንገተኛ ጥቃት እና የእስራኤል መዘናጋት በእርግጥ እስከዛሬም ድረስ መልስ ያልተገኘለት ጥያቄ ነው።
« እንደተባለው የጋዛ ሰርጥ በጦር ኃይል ብቻ ሳይሆን በጣም በተወሳሰበ እና እጅግ በረቀቀ ቴክኖሎጂ የሚጠበቅ ነው ። ግንብ አለ ፤ ግንቡ ላይ የሚቀጣጠል ሽቦ አለ፤ በኤሌክትሪክ የተያያዘ ።  እዚያ ላይ ካሜራዎች አሉ  ፤ ብዙ የስለላ እንቅስቃሴዎችን እያነፈነፉ ለእስራኤል የጸጥታ ኃይላት የሚጠቁሙ ብዙ መሳሪያዎች አሉ ። ይህን ሁሉ በጣጥሰው ነው እንግዲህ የሃማስ ደፈጣ ተዋጊዎች ደቡባዊ እስራኤል ውስጥ ያንን ሁሉ ሰው የገደሉት …. እስካሁን የተባለ ግልጽ ነገር የለም …»

የመካከለኛዉ ምሥራቅ ግጭትና ዩናይትድ ስቴትስ

ልክ ዛሬ አንድ ዓመት ባስቆጠረው የጋዛው ጦርነት መነሻ የሆነው የሃማስ ጥቃት ያስቆጣት እስራኤል የአጸፋ ርምጃ ለመውሰድ ጊዜ አልወሰደባትም። እንዲያዉም በጋዛ ሃማስን ሳላጠፋ አልመለስም  ስትል በአየር እና በምድር መጠነ ሰፊ ጦርነት ከፍታለች ። በዚህ በአየር እና በምድር ኃያል በታገዘ የጋዛ ጦርነት ብርቱ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ጉዳት ደርሷል። በጥቃቶቹ ወደ 42 ሺ የሚጠጉ ሰዎች መገደላቸውን እና  ከእነዚህ ውስጥ 16,500 ያህሉ ህጻናት መሆናቸውን ሃማስ መራሹ የጋዛ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል። 97 ሺ ገደማ ሰዎች በጥቃቱ የተለያየ መጠን ያለው ቁስለት ሲያስተናግዱ 10 ሺ ያህል ሰዎች ደግሞ የት እንደደረሱ እንዳልታወቀ መረጃው አመልክቷል። በጦርነቱ ከ 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን የጋዛ ነዋሪዎች ከጥቂቶች በስተቀር ከመኖሪያ ቄያቸው ቢያንስ አንድ ጊዜ ተፈናቅለዋል። ወይም በአስጊ ሁኔታ ውስጥ በየመጠለያው ይገኛሉ ። ይህ እስራኤል በኃይል በያዘችው የዮርዳኖስ ወንዝ ምዕራባዊ ዳርቻ ግዛትን ሳያካትት ነው ። እዚያም ቢሆን ፍልስጥኤማዉያኑ ከእስራኤል ወታደሮች እና ከአይሁዳዉያን ሰፋሪዎች ጋር በገቡት ግጭት ከ700 በላይ ፍልስኤማዉያን መገደላቸውን ነው የፍልስጥኤም የጤና ሚኒስቴር ያስታወቀው። ከ10 ሺ የሚልቁት ደግሞ በእስራኤል ወታደሮች ተይዘው ዘብጥያ ተወርውረዋል። 

በጋዛው ጦርነት የወደመ ህንጻ
ልክ ዛሬ አንድ ዓመት ባስቆጠረው የጋዛው ጦርነት መነሻ የሆነው የሃማስ ጥቃት ያስቆጣት እስራኤል የአጸፋ ርምጃ ለመውሰድ ጊዜ አልወሰደባትም። እንዲያዉም በጋዛ ሃማስን ሳላጠፋ አልመለስም  ስትል በአየር እና በምድር መጠነ ሰፊ ጦርነት ከፍታለች ። ምስል Ramadan Abed/REUTERS

«እየተተኮሰብን ነው አምልጠን የወጣነው » ሊባኖስ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን
እስራኤል በዚህ ወታደራዊ ዘመቻዋ በዓለማቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት በዘር ፍጅት ብትከሰሰም ፤ ከዓለማቀፉ ማህበረሰብ ብርቱ ወቀሳ እና ውግዘት ቢደርስባትም ፤ ሰላማዊ ሰዎችን ካልለየው ጥቃቷ ሊያስቆማት የቻለ ግን አልነበረም። ፊቷን በከፊል ከጋዛ ወደ ሊባኖስ ያዞረችው እስራኤል በሊባኖስም ታጣቂውን ከሰላማዊ ሰው ሳትለይ እያደበየችው ነው። የሊባኖስ የጤና ሚኒስቴር እንዳስታወቀው እስራኤል በሊባኖስ በይፋ የአየር እና የምድር ጥቃት መሰንዘር ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ ከ2 ሺ በላይ ሰዎች ተገድለዋል። ከአንድ ሚሊዮን የሚልቁት ተፈናቅለዋል። ከእነዚህ ውስጥ ከ280 ሺ በላይ የሚሆኑት ሀገር ጥለው ወደ  ጎረቤት ሶሪያ እንደተሰደዱ መረጃዎች ያመለክታሉ ። ሁነቱን እግር በእግር ተከትሎ በማህደሩ ሲሰድር የቆየው ነጋሽ መሐመድ ዓለማቀፍ ማህበረሰብ እስራኤልን ብሎም ጦርነቱን መግታት እንዴት እንዳልቻለ ወይም ለምን እንዳልፈለገ የነበረውን ምልከታ እንዲህ ይገልጸዋል። 

ሒዝቦላሕ መሪው ሐሳን ናስረላሕ መገደላቸውን አረጋገጠ
« ዓለማቀፍ ማህበረሰብ የሚባለው ያው ዩናይትድ ስቴትስ የምትመራው ነው በአብዛኛው ። ሌላው አቅመ ቢስ ነው ፤ ይህ ነገር ፍትህን ለሚፈልጉ ሰዎች ፣ ሰላምን የሚፈልጉ መሪዎች ፣ ይሄ ቀደም ሲል እናያቸው የነበሩ በ80ዎቹ በ90ዎቹ ድረስ ረ,ዘም ላለ ጊዜ የሚያስቡ ራዕይ ያላቸው መሪዎች ዓለም የላትም። በአብዛኛው የፖለቲካ ሃይ ሃይታ እንደ አክቲቪዝም ተይዞ ለዚያች ጊዜ የምትጠቅም የፖለቲካ ጥቅምን ማስከበሪያ እንጂ ለሰብአዊ መብት ፣ ለህዝቦች እኩልነት ለሰላም የሚባለው ነገር በአብዛኛው የለም።…  »
በእርግጥ ነው ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ አሜሪካ በተለይ ከግብጽ እና ቃጣር ጋር በመሆን መፍትሄ ለማፈላለግ ብዙ ጥራለች። ለዚህ ደግሞ የዩናይትድ ስቴትሱ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን በአድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ብቻ 12 ያህል ጊዜ ወ,ደ ቃጣናው ተጉዘዋል። የአሸማጋዮቹ ጥረት አንዴ ፍሬ ያፈራበት ወቅት ነበር። በሃማስ ታግተው ከተወሰዱ 251 እስራኤላዉያን እና የውጭ ሃገር ዜጎች 117ቱን በማስለቀቅ በምትኩ በእስራኤል እስር ቤቶች የሚገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ፍልስጥኤማዉያን ተለቀዋል። በተፋላሚዎች መካከል የተኩስ አቁም እንዲደረግ ሲደረጉ የነበሩ ጥረቶች ግን አልሰመሩም ። 

Israel | Jahrestag Terrorangriff der Hamas | Isaac Herzog
በሃማስ ታግተው ከተወሰዱ በኋላ የተገደሉ እስራኤላዉያን ምስል Alexi J. Rosenfeld/Getty Images/Getty Images

እስራኤል በሊባኖስ የከፈተችው ጦርነትና የኢራን የሚሳይል ጥቃት ወዴት ያመራ ይሆን?
ትንሿ ነገር ግን ወታደራዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጡንቻ ያዳበረችው እስራኤል ምዕራባዉያን በሽብርተኝነት ከፈረጇቸው በተለይ የተሻለ ወታደራዊ ኃይል ካደራጁ የፍልስጥኤሙ ሃማስ እና የሊባኖሱ ሄዝቦላ ጋር አንዴ ፋም አንዴ ጋም እያለ በሚነሳ ግጭት ውስጥ ቆይታለች። ከእነዚህ ሁለቱ ኃይላት ጀርባ ደግሞ የኢራን ግልጽ እና የማያወላዳ የፋይናንስ እና ወታደራዊ ድጋፍ አለ። ለዚህ ነው የእስራኤል ጠላትነት ከታጣቂ ቡድኖቹ በላይ ከኢራን ጋር መሆኑ የሚነገርለት። ኢራን በመሪዎቿ አማካኝነት በተደጋጋሚ እስራኤልን ከምድረ ገጽ የማጥፋት ፍላጎት እንዳላት አሳይታለች። የዚህ የኢራን ጽኑ ፍላጎት  እስራኤልን አያስተኛትም ፤ በአንድ በኩል የታጣቂ ቡድኖቹን መሪዎች ጨምሮ የኢራን ወታደራዊ ጠበብቶች እና መሪዎችን እያነፈነፈች ስትገድል ቆይታለች ፤ አሁንም ያንኑ እግር በእግር እየተከተለች እያደረገችው ነው። የሃማሱን መሪ እስማኤል ሃኒያ እና የሄዝቦላውን መሪ ሀሰን ነስረላን ጨምሮ በርካታ የታጣቂ ቡድኖቹ ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ አመራር የእስራኤል ጥቃት ሰለባ መሆን ኢራንን አበሳጭቷታል።

የእሥራኤልና ሔዝቦላ ጦርነት የፈጠረው ስጋት

ለዚህ ነው ባለፈው ሳምንት ኢራን እስከዛሬም ድረስ ታይቶ የማይታወቅ ብርቱ የሚሳኤል ጥቃት በእስራኤል ላይ እንድትሰነዝር ያደረጋት። በጥቃቱ ኢራን  በደቡባዊ እስራኤል በሚገኙ በሁለት የአየር ኃይል ሰፈሮች ላይ ጉዳት ማድረሷን እስራኤል አምናለች። ይህንኑ ተከትሎ እስራኤል ከአሜሪካ ጋር የተቀናጀ የአጸፋ እርምጃ ለመውሰድ መሰናዳታቸው ታውቋል። ለዚህም የአሜሪካው ማዕከላዊ ዕዝ የጦር አዛዥ ስልታዊ የተባለለትን የአጸፋ ጥቃት መሰንዘር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ለመምከር እስራኤል መግባታቸው ተሰምቷል። ቀሪው ጉዳይ የእስራኤል እና አሜሪካ የተቀናጀ ጥቃት የትኛዉን የኢራን ይዞታ ያጠቃል የሚለው ጉዳይ ብቻ ሆኗል። ጥቃቱን ተከትሎ የሚወሰድ ሌላ የኢራን እርምጃ እንዳለ ሆኖ ።   የአሜሪካ በቀጥታ በኢራን ላይ በሚወሰድ እርምጃ ለመሳተፍ እያሳየች ያለው አዝማሚያ ጦርነቱ ቀጣናዊ መልክ ይኖረው ይሆን ? በርካቶችን ያሳሰበ ጉዳይ ሆኗል ? ነጋሽ መሐመድ 

በበርሊን የተካሄደ ሰልፍ
ልክ ዛሬ አንድ አመቱን የደፈነው አዲሱ የመካከለኛው ምስራቅ ቀውስን ተከትሎ በበርካታ ሃገራት በተለይ የቀውሱ ገፈት ቀማሽ ለሆኑ ፍልስጥኤማዉያን ሲቪሎች አጋርነታቸውን የሚያሳዩ ሰልፎች ተካሂደዋል።ምስል Jörg Carstensen/dpa/picture alliance

በሊባኖስ በመልዕክት መቀበያ ስልኮች የደረሱ ፍዳታዎች ያደረሱት ጉዳት
« እንደሚመስለን ሁሉም ወገኖች ሁሉን ሊያነካካ የሚችል የለየለት ጦርነት እንዲከፈት አይፈልጉም። የዚያኑ ያህል ደግሞ አንደኛው ኃይል በተለይ የዩናትድ ስቴትስ እና የእስራኤል ትብብር በሆነ ደረጃ እንኳ ሰጥቶ የመቀበል አዝማሚያ አላየንም። ሊያስገድዳቸው የሚችልም የለም። እስራኤል ህዝቧን የግዛት አንድነቷን እና ፖለቲካዊ ጥቅሟን የማስከበር ሁለንተናዊ መብት አላት ። የዚያኑ ያህል ሌላዉም ሃገር ያንኑ መብት ሊኖረው ይገባል። የእስራኤል ሉአላዊነት እንዲከበር የሊባኖስ ሉአላዊነት መጣስ ይኖርበታል የሚል ተጠየቅ ምን አይነት እንደሆነ ግራ የሚያጋባ ነው።…»
ልክ ዛሬ አንድ አመቱን የደፈነው አዲሱ የመካከለኛው ምስራቅ ቀውስን ተከትሎ በበርካታ ሃገራት በተለይ የቀውሱ ገፈት ቀማሽ ለሆኑ ፍልስጥኤማዉያን ሲቪሎች አጋርነታቸውን የሚያሳዩ ሰልፎች ተካሂደዋል። ከፕሪቶሪያ ደቡብ አፍሪቃ እስከ በርሊን ጀርመን ፤ ከለንደን እስከ ዋሽንግተን ፤ ከዱብሊን እስከ ፓሪስ ፤አሜሪካ ፣አዉሮጳ ፣ አፍሪቃ በርካታ ሺዎች ለፍልስጥኤማዉያን ያላቸውን አጋርነት አሳይተዋል። ከእነዚህ ውስጥ በጀርመን በርሊን እና በሌሎችም የአሜሪካ እና የአውሮጳ ከተሞች  ለእስራኤል ያላቸውን አጋርነት ያሳዩም ሰልፈኞችም ጎዳና ወጥተዋል።

በበርሊን እስራኤልን ለመደገፍ የተደረገ ሰልፍ
ከእነዚህ ውስጥ በጀርመን በርሊን እና በሌሎችም የአሜሪካ እና የአውሮጳ ከተሞች  ለእስራኤል ያላቸውን አጋርነት ያሳዩም ሰልፈኞችም ጎዳና ወጥተዋልምስል Ralf Hirschberger/AFP/Getty Images

 የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ውሳኔዎች
አሁን ችግሩ ወዲህ ነው ፤ ቀዉሱን የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ሊያቆመው አልቻለም  ። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጦር ወንጀለኞች መዳኛ ፍርድ ቤትም ሊገታው ከአቅሙ በላይ የሆነበት መስሏል። ከዚሁ ሁሉ በላይ ደግሞ የአሜሪካ በአቅራቢያ መገኘት ችግሩን ከዚህም በላይ ሃገራትን በጎራ ከፍሎ ወደ ጦርነቱ ጎትቶ እንዳያስገባ ያሰጋል።  ሃማስ የተዳከመ ቢመስልም መልሶ እያንሰራራ መሆኑን እስራኤል አስታውቃለች። ሂዝቦላ መሪዎቹን በእስራኤል ጥቃት አጥቶ ነገር ግን የምድር ላይ ዉጊያውን ገፍቶበታል። የሁቲ አማጽያን አሁንም በእስራኤል ላይ የሚሳኤል እና የድሮን ጥቃት መሰንዘራቸውን ቀጥለዋል። ሶሪያ እና ኢራቅ የሚገኙ ታጣቂ የሚሊሻ ቡድኖችን እንደ አቅማቸው ወደ እስራኤል መተኮስ አላቆሙም ። እና መጨረሻው ምን ወይም እንዴት ይሆን ? ነጋሽ በአጭሩ የተሰማውን እንዲህ ገልጾታል።

የሀማስ ከፍተኛ መሪ ኢስማኤል ሀኔይ ግድያና ተጽእኖው
« በጣም ቀላል ነገር ነው ፤ ዕድሜ ልካችንን ይህንን ስንሰማ ነው ያደግነው፣  የኖርነው ፤ ከኛ በፊት የነበረዉም ትውልድ እንደዚያው ነው። ከሰባ ምናምን አመቱ ነው። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት 19 47 መጨረሻ ላይ የወሰነው  ዉሳኔ አለ ። እስዚያ ዘመን ድረስ ፍልስጥኤም ይባል የነበረዉን ግዛት ለሁለት ተከፍሎ በአንደኛው ግማደ ግዛት እስራኤል በሌላኛው ግዛት  ደግሞ ፍልስጥኤሞች ወይም አረቦች መንግስት መስርተው እንዲኖሩ ነው የፈቀዱት ። ስለዚህ ህግ የሚከበር ከሆነ በጣም ቀላል ነው ሁለቱም በየድንበራቸው ይረጋሉ ፤ አንዱ ሌላዉን ሲያጠቃ ወይም ለመጉዳት ሲፈልግ የዓለም አቀፍ ህግ ተጥሷል ተብሎ በአለምአቀፍ ፍርድ ቤት ይሁን ይከሰሳሉ ይቀጣሉ ፤ ይህንን ማድረግ ነው ዓለም ያልፈለገው … »

መካከለኛው ምስራቅ አዲሱ የጦር አውድማ ወይስ ?

የመካከለኛው ምስራቅ ቀውስ ቀውስነቱ በመካከለኛው ምስራቅ ተገትቶ አልቆመም ወይም አይቆምም። ቀውሱ ከዓለማችን ዋነኛ የንግድ መስመሮች አንዱ የሆነውን የቀይ ባህር መስመርን አስተጓጉሏል። በዓለም የነዳጅ ዋጋ ላይ ጉልህ የዋጋ ጭማሪ ሊከሰት እንደሚችል ምልክቶች እየታዩ ነው። በጦርነቱ ውስጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ያሉበት ሃገራት ኤኮኖሚያቸው መሽመድመዱ አይቀርም ። ከዚህ ሁሉ በላይ ግን የጦርነቱ ፊት አዉራሪዎች እስራኤል እና ኢራን አጋሮቻቸውን ጎትተው ወደ ጦርነቱ የማስገባት ዕድል ካገኙ የሶስተኛው የዓለም ጦርነት ዋዜማ ላይ ላለመድረሳቸን ዋስትና የለንም ።

ታምራት ዲንሳ 

ኂሩት መለሰ