1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሁለት ፓርቲዎች ከቀሪ እና ድጋሚ ምርጫ ራሳቸውን አገለሉ

ዓርብ፣ ግንቦት 2 2016

በፀጥታ ምክንያት ስድስተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ባልተደረገባቸው አራት ክልሎች ሊደረግ በታቀደው ቀሪ እና ድጋሜ ምርጫ እንደማይሳተፉ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጀት (መኢአድ) እና እናት ፓርቲ አስታወቁ።

https://p.dw.com/p/4fhh5
የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጀት (መኢአድ)
የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጀት (መኢአድ)ምስል AEUP

ሁለት ፓርቲዎች ከቀሪ እና ድጋሚ ምርጫ ራሳቸውን አገለሉ

በፀጥታ ምክንያት ስድስተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ባልተደረገባቸው አራት ክልሎች ሊደረግ በታቀደው ቀሪ እና ድጋሜ ምርጫ እንደማይሳተፉ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጀት (መኢአድ) እና እናት ፓርቲ አስታወቁ።

"ሀገር በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሥር በመሆኗ እንዲሁም በተለያዩ አካባቢዎች ካለዉ የፀጥታ ሁኔታ" መነሻ ምርጫ ለማካሄድ አስቻይ ኹኔታዎች እንደሌሉ በመጥቀስ ምርጫዉ እንዲዘገይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ጠይቀው እንደነበር ፓርቲዎቹ ገልፀዋል።

ሁለቱ ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ድርጅቶች "ቦርዱ የተጠየቀዉን ማስተካከያ ማድረግ ባለመቻሉ" ከቀሪና ድጋሜ ምርጫው ተሳትፎ ራሳቸውን ማግለላቸውን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በ6ኛው ዙር ሀገር አቀፍ ምርጫ ሥራው ባልተከናወንባቸው አራት ክልሎች ሰኔ 6 ቀን 2016 ዓ. ም ቀሪ ምርጫ ያከናውናል። 

ፓርቲዎቹ ከተሳትፎ የወጡበት ምክንያት 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ 6 ኛው ዙር ቀሪና ድጋሚ ጠቅላላ ምርጫ የሚያካሂደው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በአፋር፣ በሶማሌ እና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች መሆኑን ይፋ አድርጓል። 

በፀጥታ መናጋትና በሰላም እጦት ምክንያት ምርጫ ሳይደረግባቸው በቀሩ፤ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁናቴ ምርጫ ለማስፈፀም የፀጥታ ችግርየሌላለባቸው በተባሉት እነዚህ  ክልሎች ውስጥ በሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ አሁንም ይህንን ሀገራዊ ኹነት ለማዘጋጀት አስቻይ ኹኔታ የለም በሚል ከምርጫው ተሳትፎ ራሳቸውን ማግለላቸውን እናት እና መኢአድ ፓርቲዎች በጋራ ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

ፎቶ ማህደር፤ እናት ፓርቲ እና መኢአድ
ፎቶ ማህደር፤ እናት ፓርቲ እና መኢአድ ምስል Solomen Muche/DW

የመኢአድ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አብርሃም ጌጡ ፓርቲዎቹ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱበትን ምክንያት ገልፀዋል። "በለንበት ነባራዊ ተጨባጭ ኹኔታ ምርጫ እናደርጋለን ብሎ ማለት ትክክል አይደለም"

"ለምርጫው በምናደርገው ዝግጅት ጫና እየተደረገብን ነው"

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ የሚከናወንባቸው 1112 መደበኛ የምርጫ ጣቢያዎች እና 34 የተፈናቃይ የምርጫ ጣቢያዎች እንደሚቋቋሙ ከዚህ በፊት አስታውቋል። 

በተለይ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት ፣ የተፈናቀለ ሕዝብ የሚገኝበት ቢሆንም ክልሉ አሁን ድረስ ባልተመረጠ ምክር ቤት የሚተዳደር በመሆኑ ምርጫው ይደረግ የሚለውን ሲጠይቁት የቆዩት ጉዳይ መሆኑን በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች መካከል የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አንዱ ነው። የፓርቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር መብራቱ ዓለሙ የቅድመ ዝግጅት ሥራ መጀመራቸውን ገልፀው ሆኖም በዚህ ሁደት ችግር እየገጠማቸው መሆኑን አመልክተዋል።

"ወደ 4 ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ወደ 45  ደግሞ ለክልል ምክር ቤት ዕጩ አቅርበናል። ዕጩዎች በሙሉ ተመዝግበዋል። በቅስቀሳ ሂደት ውስጥ አዳራሽ መከልከል ፣ቁልፍ ቆልፎ መጥፋት፣ ወንበሮችን አዳራሽ ውስጥ ማውጣት፣ ባነሮችን የመቅደድ አዝማሚያዎች ታይተዋል" ። 

 እናት ፓርቲ
እናት ፓርቲምስል Enat Party

መኢአድና እናት ፓርቲዎች ኢትዮጵያ የተደራረበ ችግር ውስጥ ትገኛለች ባሉት በዚህ ወቅት ይህንን ሀገራዊ ኃላፊነት ለማከናወን የመፈለጉ አስፈላጊነት ላይ ጥያቄ አንስተዋል ሲሉ አቶ አብርሃም ተናግረዋል።

በሌሎች ክልሎች አሁንም ምርጫ አይደረግም

በስድስተኛው ሀገር አቀፍ ጠቅላላ ምርጫ ፤ ምርጫው አሁን ይደረግባቸዋል ከተባሉት አራት ክልሎች በተጨማሪ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎችም ምርጫ ያልተደረገባቸው ሥፍራዎች ጥቂት አይዱሉም። የትግራይ ክልልም የራሱ ሌላ መልክ ቢኖረውም ምርጫ አልተደረገበትም።

 

ሰለሞን ሙጬ 
አዜብ ታደሰ 
ዮኃንስ ገብረእግዚአብሔር