1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፓራሊምፒክስ በድምቀት ተፈጸመ

ሰኞ፣ ጳጉሜን 5 2004

ለንደን ላይ ሲካሄድ የሰነበተው14ኛው የአካል ጉዳተኞች ፓራሊምፒክስ ጨዋታ ባለፈው ምሽት በኦሎምፒኩ ስታዲዮም በተካሄደ እጅግ በደመቀ ትርዒት ተፈጽሟል።

https://p.dw.com/p/166Jd
ምስል Getty Images

ለንደን ላይ ሲካሄድ የሰነበተው14ኛው የአካል ጉዳተኞች ፓራሊምፒክስ ጨዋታ ባለፈው ምሽት በኦሎምፒኩ ስታዲዮም በተካሄደ እጅግ በደመቀ ትርዒት ተፈጽሟል።

«ይህ ፓራሊምፒክስ በቀላሉ አስደናቂው ፓራሊምፒክስ ሆኖ ነው ያለፈው። ያላንዳች ማመንታት በእኔም ሆነ በአትሌቶቹ አመለካከት ጨዋታው እስካሁን ያልታየ ታላቅ ፓራሊምፒክስ ነበር»

የኦሎምፒኩ አዘጋጅ ኮሚቴ ፕሬዚደንት ሴባስቲያ ኮው! በዕውነትም ፓራሊምፒክስ ከ 52 ዓመታት በፊት ሮማ ላይ ከተጀመረ ወዲህ ያለፉትን 11 የውድድር ቀናት ያህል ደምቆና ዓለምን ማርኮ የቆየበት ጊዜ ጨርሶ አይታወስም። ለዚህ ደግሞ የአካል ጉዳታቸውን አሸንፈው ታላቅ የስፖርት አስተዋጽኦ ከሚያደርጉት አትሌቶች ድርሻ ባሻገር ከጥቂት ሣምንታት በፊት በኦሎምፒኩ ጨዋታ እንደታየው የለንደን ነዋሪዎች ድርሻም እጅግ ከፍተኛ ነው።

እያንዳንዱ ውድድር ዋናም ሆነ አትሌቲክስ ወይም የኳስ ጨዋታ በሰፊው በተመልካች በመጎብኘቱ ለጨዋታው ትልቅ ድምቀት እንደሰጠውና ምናልባትም ተወዳጅነቱን በዓለም ዙሪያ ከፍ እንዳደረገው አንድና ሁለት የለውም። በጨዋታው ከ 165 ሃገራት የመነጩ ከአራት ሺህ የሚበልጡ አትሌቶች ሲሳተፉ ሕዝባዊት ቻይና 95 ወርቅ፤ 71 ብርና 65 ናስ፤ በጠቅላላው 231 ሜዳሊያዎችን በማግኘት እንደ ቤይጂንግ ሁሉ በፍጹም ልዕልና ቀደምቷ ሆናለች።

ሩሢያ በ 36 ወርቅ፤ በጠቅላላው በ 102 ሜዳሊያዎች ሁለተኛ ስትሆን ለአዘጋጇ ብሪታኒያም በ 34 ወርቅ፣ በጥቅሉ በ 120 ሜዳሊያዎች ሶሥተኛ መውጣቷ ከዚህ ቀደም ያልተለመደ ታላቅ ውጤት ነበር። ኡክራኒያ አራተኛ፣ አውስትራሊያ አምሥተኛ፣ ዩ ኤስ አሜሪካ ስድሥተኛ፤ እንዲሁም ብራዚል ሰባተኛና ጀርመንም ስምንተኛ ሆነዋል። ከአፍሪቃ ክፍለ-ዓለም ቱኒዚያ በዘጠን ወርቅ 14ኛ፤ ደቡብ አፍሪቃ በስምንት ወርቅ 18ኛ፤ ናይጄሪያም በስድሥት ወርቅ ሜዳሊያ 22ኛ በመሆን ጠንካሮቹ ነበሩ።

Paralympics Oscar Pistorius
ምስል Glyn Kirk/AFP/GettyImages

የፓራሊምፒክሱ ውድድር ኮከብ ያላንዳች ማመንታት ከጉልበቱ በታች ሁለት እግሮቹ የተቆረጡት ደቡብ አፍሪቃዊ ሯጭ ኦስካር ፒስቶሪዩስ ነበር። በሰው ሰራሽ እግሮች የሚሮጠው አትሌት በለንደኑ ኦሎምፒያ ስታዲዮምም የተመልካቹን ስሜት በመቀስቀስ ቀደምቱ መሆኑ ተሳክቶለታል። ይህ ደግሞ በተለይ ትናንት በ 400 ሜትር ሩጫ በፍጹም ልዕልና ሲያሸንፍ በጣሙን ነበር ጎልቶ የታየው።

እርግጥ ፒስቶሪዩስ በለንደኑ ፓራሊምፒክስ ብቸኛው የማይበገር ሯጭ አልሆነም። በ200 ሜትር በብራዚላዊው በአላን ኦሊቪየራ ለዚያውም በአዲስ የዓለም ክብር-ወሰን መሸነፉ ለፉክክሩ እየጠነከረ መሄድ ምስክር ነው። ግን ፒስቶሪዩስ ታላቁ ስፖርተኛ ሆኖ የሚቀጥል ሲሆን የለንደኑ ፓራሊምፒክ በሕዝብ አመለካከት ላይ ለውጥ ማስከተሉም ብዙ ነው ያስደሰተው።

«በዓለም ዙሪያ ይበልጥ ተጨማሪ ሕዝብ ይህን ፓራሊምፒክስ ተመልክቷል በዬ አስባለሁ። ስፖርቱ ይበልጥ ለሕዝብ ሊቀርብ ችሏል። ለንደን በዓለም ላይ ስኬታማ ከሆኑት ቦታዎች አንዷ ስትሆን ይህም በዓለም ዙሪያ በሕዝብ የተንጸባረቀ ጉዳይ ነው። ለመጀመሪያ ጊዜ ውድድሩ ከአካል ጉዳት አንጻር ሣይሆን ከስፖርት ብቃት በኩል ሊታይ ችሏል። ይህ ነው እንግዲህ ድንቁ ነገር። የአስተሳሰብ ለውጥ እየተደረገ ሲሆን ለዚሁ አስተዋጸኦ ያደረጉትን ሁሉ ላመሰግን እወዳለሁ»

የሚቀጥለው ፓራሊምፒክስ ከአራት ዓመታት በኋላ ብራዚል-ሪዮ-ዴ-ጃኔይሮ ላይ 31ኛውን የኦሎምፒክ ጨዋታ ተከትሎ ይካሄዳል። እንግዲህ ትናንት ለንደን ላይ የጠፋው የፓራሊምፒክስ ችቦ መልሶ በሪዮ እስከሚቀጣጠል በጉጉትና በናፍቆት የሚጠበቅ ነው የሚሆነው።

Brasilien Stadion Maracana
ምስል AP

የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ማጣሪያ

ብራዚል ውስጥ ከሁለት ዓመታት በኋላ ለሚካሄደው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ዙር ለማለፍ የሚደረገው ማጣሪያ ውድድር በዚህ በአውሮፓ ባለፈው ሰንበት ተጀምሯል። በዘጠን ምድቦች በሚካሄደው የአውሮፓ ማጣሪያ በምድብ አንድ ውስጥ ቤልጂግና ክሮኤሺያ የመጀመሪያ ግጥሚያቸውን በማሸነፍ ሲወጡ ሰርቢያና ስኮትላንድ በእኩል ለእኩል ተወስነዋል። በነገው ምሽት ክሮኤሺያና ቤልጂግ እርስበርስ የሚገናኙ ሲሆን ሰርቢያ ከዌልስ፤ ስኮትላንድም ከማቄዶኒያ ትጫወታለች። ምድብ-ሁለት ውስጥ አርሜኒያ በአሸናፊነት የምትመራ ሲሆን ቡልጋሪና ኢጣሊያ፤ እንዲሁም ዴንማርክና ቼክ ሬፑብሊክ በመጀመሪያ ግጥሚያቸው ከእኩል ለእኩል ውጤት አላለፉም።

አርሜኒያ ነገ ከቡልጋሪያ የምትጋጠም ሲሆን ኢጣሊያ ከማልታ ጋር ቀላል ጨዋታ ነው የሚጠብቃት። በምድብ-ሶሥት ውስጥ ጀርመን ፌሮ ደሴቶችን፤ አየርላንድም ካዛክስታንን ሲያሸንፉ ስዊድንና አውስትሪያ ውድድሩን የሚጀምሩት ገና በነገው ምሽት ነው። አውስትሪያ ጀርመንን በማሸነፍ ለዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ለማለፍ ከወዲሁ ጠቃሚ ዕርምጃ ለማድረግ የምታልም ሲሆን ስዊድንም ካዛክስታንን በማሸነፍ የመጀመሪያ ሶሥት ነጥቦቿን ለማረጋገጥ ትፈልጋለች።

በምድብ-አራት ውስጥም ሁንጋሪያ፣ ሩሜኒያና ኔዘርላንድ ማጣሪያውን በማሸነፍ ሲጀምሩ ኤስቶኒያ፣ ቱርክና አንዶራ ባቡሩ ከወዲሁ እንዳያመልጣቸው በነገው ተከታይ ግጥሚያ ስኬት ማግኘት አለባቸው። ከባዱ ግጥሚያ የሚጠብቃት ከኔዘርላንድ የምትገናኘው ሁንጋሪያ ናት። ምድብ-አምሥት ውስጥ አልባኒያ፣ ስዊስና አይስላንድ ለመጀመሪያ ድል ሲበቁ በምድብ-ስድሥት ደግሞ ሩሢያና ፖርቱጋል አሸናፊ በመሆን ቀደምቱ ናቸው። ከዚሁ ሌላ ምድብ-ሰባትን ቦስና ሄርሴጎቪና፤ ምድብ-ስምንትን እንግሊዝ፤ እንዲሁም ምድብ-ዘጠኝን ፈረንሣይ ይመራሉ።

Fußball Argentinien Nationalmannschaft Lionel Messi
ምስል picture alliance/Pressefoto Ulmer

በደቡብ አሜሪካ ማጣሪያ ባለፈው አርብ በተካሄዱት ስድሥተኛ ግጥሚያዎች አርጄንቲና ፓራጉዋይን 3-1 በማሸነፍ የምድቡን አመራር በኮሉምቢያ 4-0 ከተቀጣችው ከኡሩጉዋይ ተረክባለች። አርጄንቲና ለተከታታይ ስድሥተኛ ድል መብቃቷ ሲሆን አሁንም እንደገና ድንቅ ተጫዋቿን ሊዮኔል ሜሢን የሚያቆም አልተገኘም። አርጄንቲና በወቅቱ አያያዟ የዓለም ዋንጫ ባለቤት ለመሆን ትልቅ ዕድል ከሚሰጣቸው ሃገራት አንዷ ናት።

በተቀሩት ግጥሚያዎች ኤኩዋዶር ቦሊቪያን 1-0 ስታሸንፍ ፔሩም ቬኔዙዌላን 2-1 ረትታለች። አርጄንቲና አሁን የደቡብ አሜሪካውን ምድብ በ 13 ነጥቦች የምትመራ ሲሆን ቺሌና ኤኩዋዶር አንዲት ነጥብ ወረድ ብለው ሁለተኛና ሶሥተኛ ናቸው። ኡሩጉዋይ በ 11 ነጥቦች አራተኛ ስትሆን ቬኔዙዌላ ደግሞ በስምንት ነጥቦች አምሥተኛ ናት። የመጀመሪያዎቹ አራት ሃገራት በቀጥታ ለዓለም ዋንጫው ፍጻሜ ለማለፍ የሚበቁ ሲሆን አምሥተኛው ከኮንካካፍ ምድብ አራተኛ ጋር ተጋጥሞ ወደፊት የመዝለቅ ዕድል ይኖረዋል።

በሶሥት ምድቦች ተከፍሎ በሚካሄደው የሰሜንና ማዕከላዊ አሜሪካ ካራይብ የኮንካካፍ ማጣሪያ ጃማይካ በምድብ-አንድ አሜሪካን 2-1 በማሸነፍ በሰባት ነጥቦች አመራሩን ለመያዝ በቅታለች። አሜሪካ አራት ነጥቦች ሲኖሯት ከጉዋቴማላ ጋር እኩል ናት። ስለዚህም ወደፊት ለመራመድ ከጃሜይካ በምታደርገው የመልስ ግጥሚያ ማሸነፏ ግድ ነው። በምድብ-ሁለት ሜክሢኮ ሶሥት ተከታታይ ግጥሚያዎቿን በማሸነፍ ጥሩ እየተራመደች ነው። ወደ ተከታዩ ማጣሪያ ዙር ለማለፍ ከእንግዲህ አንዲት ድል ትበቃታለች። ኮስታ ሪካ ሁለተኛ ስትሆን በምድብ ሶስት ደግሞ ካናዳ ፓናማን በማሸነፍ አመራሩን ይዛለች።

በእሢያው ማጣሪያ ደቡብ ኮሪያና ጃፓን ሁለቱን ምድቦች በየፊናቸው ይመራሉ። በነገው ዕለት በምድብ-አንድ ውስጥ ኡዝቤኪስታን ከደቡብ ኮሪያ፤ እንዲሁም ሊባኖስ ከኢራን የሚጋጠሙ ሲሆን በምድብ-ሁለት የሚገናኙት ደግሞ ዮርዳኖስ ከአውስትራሊያና ጃፓን ከኢራቅ ናቸው። በተረፈ በአፍሪቃ ዋንጫ የሁለተኛ ዙር የመጀመሪያ ማጣሪያ ኢትዮጵያ ትናንት ካርቱም ላይ ከሱዳን በተካሄደ ግጥሚያ 5-3 ተሸንፋለች።

ከብዙ በጥቂቱ የቀደምቱን ሃገራት ወጤት ለመጥቀስ ያህል ያለፈው ዋንጫ ባለቤት ዛምቢያ ከኡጋንዳ 1-0፤ ዚምባብዌ ከአንጎላ 3-1፤ ጋና ከማላዊ 2-0፤ አይቮሪ ኮስት ከሴኔጋል 4-2፤ ዴሞክራቲክ ሬፑብሊክ ኮንጎ ከኤኩዋቶሪያል ጊኒ 4-0 ተለያይተዋል። የመልሱ ግጥሚያ ከአንድ ወር በኋላ የሚካሄድ ሲሆን የየምድቡ አሸናፊዎች በመጨው ጥር ወር ደቡብ አፍሪቃ በምታስተናግደው ፍጻሜ ውድድር ይሳተፋሉ።

Serena Williams siegt bei den US Open
ምስል Reuters

ቴኒስ

አሜሪካዊቱ ሤሬና ዊሊያምስ ባለፈው ምሽት የዩ ኤስ ኦፕን የሴቶች ቴኒስ ፍጻሜ ግጥሚያ በዓለም የማዕረግ ተዋረድ ላይ አንደኛ የሆነችውን የቤላሩሷን ቪክቶሪያ አዛሬንካን በፍጹም ልዕልና በማሸነፍ ለታላቅ ድል በቅታለች። ሤሬና ባለፉት ሶሥት ወራት ውስጥ ከታች ተነስታ ለወቅቱ ጥንካሬ መብቃቷ በጣም የሚያስደንቅ ነው።

«ይህን ዕድል ማግኘቱ በመጀመሪያ ትልቅ ነገር ነው። 13 ዓመት በመጀመሪያና በመጨረሻው መካከል ረጅም ጊዜ ነው። ግን ተሥፋ አልቆረጥኩም።ብዙ ጊዜ ተመልሼ ለመምጣት ችያለሁ። እና ጨርሶ ድንጋጤ አልነበኝም»

ሤሬና ዊሊያምስ ባለፉት ወራት በዊምብልደን፤ እንዲሁም በለንደን ኦሎምፒክ በነጠላና በድርብ በማሸነፍ የተለየ ጥንካሬ ስታሳይ የትናንቱ አራተኛው የዩ ኤስ ኦፕን ድሏ መሆኑ ነው። በወንዶች የሰርቢያው ኖቫክ ጆኮቪች የስፓን ተጋጣሚውን ዴቮድ ፌሬርን ሲያሸንፍ በሴቶች ጥንድ ሣራ ኤራኒና ሮቤርታ ቪንቺ ከኢጣሊያ የቼክ ተጋጣሚዎቻቸውን በሁለት ምድብ ግጥሚያ ረትተዋል።

Formel 1 Grand Prix - Lewis Hamilton
ምስል Getty Images

ፎርሙላ-አንድ

በትናንትናው ዕለት ኢጣሊያ-ሞንሣ ላይ ተካሂዶ በነበረው የፎርሙላ-አንድ አውቶሞቢል እሽቅድድም የብሪታኒያው ዘዋሪ ሉዊስ ሃሚልተን ለአሸናፊነት በቅቷል። የሜክሢኮው ሴርጆ ፔሬዝ ሁለተኛ ሲሆን የስፓኙ ፌርናንዶ አሎንሶ ደግሞ ሶሥተኛ ወጥቷል። በአጠቃላይ ነጥብ ፌርናንዶ አሎንሶ በ 179 አንደኛ ሲሆን ሉዊስ ሃሚልተን በ 142 ሁለተኛ ነው። የፊንላንዱ ኪሚ ራይኮንን በ 141 ወደ ሶሥተኛው ቦታ ከፍ ሲል እሽቅድድሙን በብልሽት ምክንያት ያቋረጠው ጀርመናዊው የዓለም ሻምፒዮን ዜባስቲያን ፌትል በ 140 ነጥቦች ወደ አራተኛው ቦታ ማቆልቆሉ ግድ ሆኖበታል።

ይህ የስፖርት ዝግጅታችን ዛሬ በመገባደድ ላይ ባለው 2004 ዓመተ-ምሕረት የመጨረሻው እንደመሆኑ መጠን የኢትዮጵያ ስፖርተኞች፤ በተለይም አትሌቶች እስከ ቅርቡ የለንደን ኦሎምፒክ ጨዋታ አገርን በበጎ ለማስጠራት ላደረጉት ታላቅ አስተዋጽኦ ልናመሰግን እንወዳለን። የጎረቤት ተፎካካሪያችን የኬንያ ልዕልና ሊውጠን የተቃረበ መስሎ በታየበት ጊዜ እነ ቲኪ ገላናንና መሐመድ አማንን የመሳሰሉ ወጣት አትሌቶች እየተተኩ ሲሄዱ ማየቱ የሚያኮራና ለወደፊትም የተሥፋ ምንጭ የሚሆን ነው።

የኢትዮጵያ የእግር ኳስ ብሄራዊ ቡድንም ቢሆን በዓለም ዋንጫው ማጣሪያ ግሩም ጅማሮ ሲያሳይ ወደፊት ዘልቆ የቆየ ሕልሙ ዕውን እንዲሆንለት ምኞታችን ነው። በዚሁ መንፈስ ለናንተም ከዘመን ዘመን በደህና ያሸጋግራችሁ እያልኩ ከወዲሁ ደጉን እመኝላችኋለሁ፤ በአዲሱ ዓመት ቸር ይግጠመን!

መሥፍን መኮንን

ሒሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ