ፓሪስ፤ የሽብር ጥቃቱ አቀነባባሪ ተገደለ
ሐሙስ፣ ኅዳር 9 2008ትዉልዱ ከሞሮኮ የሆነዉ ይህ ግለሰብ ሶርያ ዉስጥ ሰልጥኖ እንደመጣ እና ባለፈዉ ዓመት ጥር ወር የቤልጅየም ፖሊስን ሊገድል ሞክሮ እንደከሸፈበትም ተገልጿል። በወቅቱ አንዲት ሴት አጥፍቶ ጠፊ የታጠቀችዉን የፈንጂ ቀበቶ ካነጎደች እና ሰባት ሰዓት ከፈጀዉ የተኩስ ልዉዉጥ በኋላም ቢያንስ ሁለት አስከሬን በስፍራዉ መገኘቱን አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ዘግቧል። የእጅ አሻራን የሚመረምሩ ባለሙያዎች ከሟቾቹ አንዱ ተፈላጊዉ የቤልጂየም ዜጋ መሆኑን መለየታቸዉንም አመልክቷል። ትናንት ከተካሄደ ከበባዉና የተኩስ ልዉዉጥ በኋላ የሀገሪቱ የምክር ቤት አባላት ዛሬ በፈረንሳይ የተደነገገዉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም እንዲራዘም ወስኗል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ፖሊሶች እና የፀጥታ ኃይሎች መሣሪያቸዉን ከሥራ ሰዓት ዉጭም ይዘዉ እንዲንቀሳቀሱ እና የፈረንሳይ መንግሥትም የኢንተርኔት እና የማኅበራዊ መገናኛ ብዙሃን ግንኙነቶችን እንዲዘጋም ይፈቅዳል። ምክር ቤቱ አዋጁን ሲያራዝም ጠቅላይ ሚኒስትር ማኑዌል ቫልስ አሁንም ፈረንሳይ ምናልባትም የኬሚካል ጦርመሳሪያ አደጋ እንደሚያሰጋት አሳስበዋል።
«አሁንም የኬሚካል ወይም ባዮሎጆካል ጦር መሣሪያ እንደሚያሰጋን እናዉቃለን። ድንበር አልፎ ሊሄድ የሚችል አዲስ የጦርነት ዓይነት እያየን ነዉ። በእስላማዊ መንግሥት ወይም በአልቃይዳ የግንኙነት ሰንሰለት አማካኝነት ከረዥም ርቀት የሚካሄድ ጦርነት። በዚህ አማካኝነት ተዋጊዎች ይመለመላሉ፤ ይሰለጥናሉ፤ ንጥረነገሮች ይቀመሙና ትዕዛዝ ይተላለፋል። በአንድ ትዕዛዝ ብቻም ትርምሱ ተደራጅቶ ይጀመራል።»
ሸዋዬ ለገሠ
አርያም ተክሌ