1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፓሪስ፤ የሶርያ ወዳጆች ጉባኤ

ዓርብ፣ ሰኔ 29 2004

የሶርያ ወዳጆች በሚል ጥላ ሥር የተሰባሰቡት ከአንድ መቶ የሚልቁ ሀገሮች የተሳተፉበት ጉባኤ ፕሬዝደንት በሽር አልአሰድ ስልጣን እንዲለቁ ዛሬ ጠየቀ።

https://p.dw.com/p/15T9i
ምስል dapd

 ፓሪስ ፈረንሳይ የተሰባሰቡት የምዕራብ እና አረብ ሀገር መንግስታት የአሰድ መንግስት እንዲያከትም የተመድ የፀጥታዉ ምክር ቤት ጠንከር ያለ ርምጃ እንዲወስድም አሳስበዋል። የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችና ከፍተኛ ዲፕሎማቶች የተገኙበት ይህ ጉባኤ በማያያዝም፤ ለሶርያ መንግስት ተቃዋሚ ኃይሎች የመገናኛ መሣሪያዎችን ጨምሮ በርከት ያለ ዕርዳታ ሊደረግ ይገባል ሲልም ተስማምቷል። ሩሲያ እና ቻይና በጉባኤዉ አልተሳተፉም ። የዩናይትድ ስቴትስ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሂላሪ ክሊንተን ሁለቱን ሀገሮች አሰላለፋቸዉን ከሶርያ ህዝብ ፍላጎት አኳያ እንዲያስተካክሉ በማሳሰብ ተሰብሳቢዎች ይህንኑ ለመንግስታቱ እንዲገልፁ ጠይቀዋል፣

Frankreich Syrien Treffen der Freunde Syriens in Paris Hillary Rodham Clinton und Guido Westerwelle
የጀርመን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጊዶ ቬስተርቬለ እና የአሜሪካ አቻቸዉ ሂላሪ ክሊንተንምስል dapd

«አሁን እዚህ እያንዳንዱን መንግስትና ቡድን ወክላችሁ የተገኛችሁ ወገኖች ምን ማድረግ ትችላላችሁ? ከቻይናና ሩሲያ ጋ በመገናኘት ከጎንዮሹ ርምጃ በመዉጣት ሕጋዊዉን የሶርያን ህዝብ ፍላጎት መደገፍ መጀመር እንደሚኖርባቸዉ ማሳሰብ ብቻ ሳይሆን እንድትጠይቁ እጠይቃለሁ።»
ሩሲያ ወቀሳዉን አስተባብላለች። የሀገሪቱ ምክትል የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰርጌይ ራይብኮቭ እንዲህ ባለዉ ሁኔታ መንግስታቸዉ አሳድን ይደግፋል መባሉን እንደማይቀበሉ አመልክተዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለም አንድ የሶርያ መንግስት ከፍተኛ የጦር አዛዥ ከድተዉ ቱርክ መግባታቸዉ ተሰምቷል። የብርጋዴር ጀነራል ማናፍ ትላስ የአሳድን መንግስት መክዳት የሶርያ ወዳጆች ጉባኤ ላይ የተገኙትን የፕሬዝደንት አልአሰድ ተቃዋሚዎች ማበረታታቱ ተገልጿል። ጀነራሉ ወደፓሪስ እንደሚያመሩም ተጠቁሟል።

ሸዋዬ ለገሠ

ሂሩት መለሰ