ፓሪስ፥ አሸባሪ ወንድማማቾቹ ተገደሉ
ዓርብ፣ ጥር 1 2007ይኽ ከባድ ጦር መሣሪያ የታጠቀ ሰው የሸቀጥ መደብሩ ውስጥ ዘልቆ በመግባት ኹለት ሰዎችን ከመግደሉም በተጨማሪ አምስት ሰዎችን አግቶ እንደነበር ተነግሯል። የሽብር ጥቃቱን የፈፀመው ትናንት በደቡባዊው የፓሪስ መዳረሻ አንዲት ፖሊስን ተኩሶ የገደለው ሰው ሳይሆን እንዳልቀረ ፖሊስ አስታውቋል። የዛሬውን ግድያ የፈፀመው አሸባሪ ከትናንት በስትያ ፓሪስ ውስጥ 12 ጋዜጠኞችን ከገደሉት ወንድማማቾች ጋር በአንድ የእስልምና ቡድን ውስጥ እንደሚተዋወቁም ፖሊስ ጠቅሷል። ኹለቱ ወንድማማቾች «ሻርሊ ኤብቶ» የተሰኘው የስላቅ ጋዜጣ ዋና ጽ/ቤትን ፓሪስ ውስጥ በመውረር ግድያ ከፈፀሙ በኋላ ወደ ሰሜን ፈረንሣይ መሸሻቸው ይታወቃል። ወንድማማቾቹ ዳማታን ኢን ሻሊዬ የተባለው አካባቢ በሚገኝ አንድ የኅትመት መጋዘን ውስጥ እንደተደበቁ መገደላቸው ተገልጧል። ቀደም ሲል ከፖሊሶች ጋር ሲደረግ በነበረው ድርድር ኹለቱ ወንድማማቾች ለመሞት ዝግጁ መሆናቸውን መናገራቸው ተዘግቦ ነበር።
ፖሊስ አካባቢውን በበርካታ ፖሊሶች እና በሔሊኮፕተሮች በመክበብ ወደ ከተማዋ መውጣትም ሆነ እና መግባት አግዶም ነበር። ከትናንት በስትያ አንስቶ በፓሪስ በተከታታይ የተከሰተውን ግድያ በዓለም ዙሪያ በርካቶች አውግዘውታል። የፈረንሣይ የሙስሊም ዲሞክራቶች ሊቀመንበር አብድራህሜ ዳህማኔ፦
«ለጽንፈንነት ፈጣን ምላሽ ያስፈልጋል። ዛሬ የእኛ መልስ፦ እዚያ ምንድን ነው የሚያደርጉት? የሚል ነው። ይኼ እስልምና አይደለም! እጅግ በጣም በግልጥ መናገር ያስፈልጋል። ወጣቶች ከእንግዲህ እነዚህን የወንጀለኞች ቡድን እና አክራሪ ኢማሞችን መስማት የለባቸውም። ያ ዝቅጠት ብቻ ነው የሚያስከትልብን!»
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ኂሩት መለሰ