1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፑቲንና ኢትዮጵያዉያኑ በሩስያ 

ሰኞ፣ ጥቅምት 10 2012

«ሩስያ ዉስጥ መካሄድ የጀመሩትን ለዉጦች በቅርብ ነዉ የተመለከትኩት። የፕሬዚዳንት ጎርባ ጆፍን ለዉጥን፤ በመቀጠል የፕሬዚዳንት የልሰንን ለዉጥ፤ በመከታተሌ የታሪኩ ተካፋይ ነኝ ማለት ነዉ። ስለ ፕሬዚደንት ፑቲን ያሳተምኩት መጽሐፍ ከተወለደበት ጊዜ ጀምሮ እስከ 2000 ዓ,ም ማለትም ፕሬዚደንት እስከሆኑበት ድረስ ያለዉን ታሪካቸዉን ያካትታል።»

https://p.dw.com/p/3NyWo
Äthiopien Buchcover Wladimir Wladimirowitsch Putin von Nigusie Kassae
ምስል Nigusie Kassae

ፑቲን እና ኢትዮጵያውን በሩስያ

ሩስያ ሞስኮ በሚገኘዉ በሩሲያ የሕዝቦች ወዳጅነት ዩኒቨርስቲ የታሪክ ምሁሩ ኘሮፌሰር ንጉሴ ካሣዬ ወልደሚካኤል ይባላሉ። ኘሮፌሰር  ንጉሴ ካሣዬ ወልደሚካኤል በአማርኛ ቋንቋ፣ "ቭላድሚር ፑቲን" ርዕስ የፕሬዚዳንት ፑቲንን ታሪክ የመጀመርያ ክፍል አሳትመዋል። ፕሮፊሰር ንጉሴ የቀዳማዊ ኃይለሥላሤን ታሪክ በተመለከተ በሩስያ ቋንቋ እንዲሁ አንድ መጽሐፍ አሳትመዉ ለአንባብያን አቅርበዋል። ነገርን ነገር ያነሳዋል ነዉና ባለፈዉ ሳምንት መጨረሻ ላይ የሩስያዉ ፕሬዚዳንት ፕላድሚር ፑቲን 20ኛ ዓመት የሥልጣን ዘመን ሲታወስ የባህል መድረካችን የኢትዮ-ሩስያን የወዳጅነት ግንኙነት፤ የኢትዮጵያዉያን ሕይወት በሩስያ ብሎም የፕሬዚዳንት ፑቲን የ 20 ዓመት የሥልጣን ጉዞ በጥቂቱ ሊያስቃኘን ተዘጋጅቶአል። በሩስያ መዲና  እና አካባቢዋ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚያስተምሩ ሦስት ኢትዮጵያዉያን ምሁራን ይገኛሉ። በቅርቡ የፕሬዚዳነት ፑቲንን የሕይወት ታሪክ ለኢትዮጵያዉያን፤ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴን ታሪክን ደሞ በሩስያንኛ ቋንቋ አሳትመዉ መዲና ሞስኮ ላይ አስመርቀዉ ለአንባብያን ያቀረቡት ፕሮፊሰር ንጉሴ ካሳይ ወልደሚካኤል ፤ በሩስያ ታዋቂ ከሚባሉ ዓለም አቀፍ ዩንቨርስቲዎች ከሚያስተምሩ ኢትዮጵያዉያን መካከል አንዱ ናቸዉ። በአሁኑ ጊዜ ሩስያ ዉስጥ ተማሪዎችን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዉያን እንደሚኖሩ ይነገራል። ሩስያ በደርግ ሥርዓተ ማኅበር ከቀድሞዋ ሶቭየት ኅብረት ብሎም፤ በሩስያ ፊደሬሽን እስከ 24 ሺህ ለሚሆኑ ኢትዮጵያዉያን የነፃ እድል ትምህርት መሰጠቱን በሩስያ የሚገኙ ኢትዮጵያዉያን ነግረዉናል። የኢትዮጵያዉያን እና የሩስያ ግንኙነት በደርግ ሥርዓተ ማኅበር ተጠናክሮ ቀጠለ እንጂ የሁለቱ ሃገር የወዳጅነት ግንኙነት፤ በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን በአፄ ኃይለሥላሴ በአጼ ዳግማዊ ምንሊክ እና በአድዋ ጦርነት ዘመን ሁሉ ሁለቱ ሃገራት ጠንካራ የወዳጅነት ግንኙነት እንደነበራቸዉ የታሪክ መዝገባት ያሳያሉ። የዛሬ 34 ዓመት የነፃ ትምህርት እድልን አግኝተዉ በሞስኮ በሩሲያ የሕዝቦች ወዳጅነት ዩኒቨርስቲ በቀድሞ አጠራሩ ሞስኮ ፓትሬስ ሉሙምባ ዩንቨርስቲ፤ ትምርታቸዉን የጀመሩት የታሪክ ምሁሩ ኘሮፌሰር ንጉሴ ካሣዬ በዝያዉ በተማሩበት ከፍተኛ ተቋም የታወቁ መምህር ሆነዋል።  

Professor Zenebe Kinfu
ምስል Zenebe Kinfu

« ሩስያ ዉስጥ መካሄድ የጀመሩትን ለዉጦች በቅርብ ነዉ የተመለከትኩት። የመጀመርያዉ የፕሬዚዳንት ጎርባጆፍን ለዉጥ በመቀጠል የፕሬዚዳንት የልሰንን ለዉጥ፤ በመከታተሌ የታሪኩ ተካፋይ ነኝ ማለት ነዉ። አሁን ያሳተምኩት የፕሬዚደንት ፑቲን ታሪክ ከተወለደበት ጊዜ ጀምሮ እስከ 2000 ዓ,ም ማለትም ፕሬዚደንት እስከሆኑበት ድረስ ያለዉን ታሪካቸዉን ያካትታል። መጽሐፉ የፑቲን ታሪክ ይባል እንጂ የሩስያንም ታሪክ ያካተተ ነዉ። ለምን እንደዚህ ሆነ ምክንያቱም የሩስያን ታሪክ ብቻ ለኢትዮጵያዉያን አንባቢ ባቀርብ በተለይም ደግሞ ለመካከለኛዉ አንባቢ ከበድ ሊል ይችላል ስለዚህ በፕሬዚዳንት ፑቲን የሕይወት ታሪክ በኩል፤ የሩስያን ታሪክ ነዉ ለኢትዮጵያዉያን አንባቢ ማቅረብ የሞከርኩት። ለምሳሌ ብናይ የaruseያ መንግሥት አመሰራረት ከኢትዮጵያ መንግሥት አመሰራረት ጋር ተመሳሳይነት አለዉ የሩስያ መንግሥት እንደኢትዮጵያዉ መንግሥት በብዙ ሕዝቦች ኅብረት የተመሰረት ነዉ። አንዳንድ ጊዜ በጦርነት ሊሆን ይችላል አንዳንድ ጊዜ በሰላም ሊሆን ይችላል። ይህንን ታሪክ ነዉ ለማቅብ የሞከርኩት። የፑቲን እና የአፄ ኃይለሥላሴን ወደ ስልጣን አመጣጥን ብንመለከት፤ አፄ ኃይለሥላሴወደ ስልጣን የመጡት ኢትዮጵያ አለቀላት ትበታተናለች በሚባልባትና ሦስቱ ምዕራባዊያን ሃገሮች ማለት ጣልያን እንጊሊዝ እና ፈረንሳይ ይቀራመቱዋታል በሚባልበት ጊዜ ነዉ። 1906 ዓ.ም ዳግማዊ ምኒሊክ ታመዉ ተኝተዉ ሳለ ከሳቸዉ በኋላ ማንም የለም በሚባልበት ጊዜ ነዉ ምክንያቱም ወራሽ የተባሉት እያሱ የራሳቸዉ ጦር እንኳ የሌላቸዉ ገና ለጋ ነበሩ። ማዕከላዊ መንግሥት ክፍለ ሃገሮችን ጠቅላይ ግዛቶችን ማስገበር ያልቻለበት ወቅት ነበር። ከዝያ ወድያ ነዉ አፄ ኃይለሥላሴ ወደ ስልጣን መጥተዉ ጉዳዮችን መስመር ማስያዝ የሚጀምሩት። የሩስያዉን ፕሬዚደንት ፑቲንን ታሪክ በምንመለከትበት ጊዜ ከጎርጎረሳዉያኑ 1991 ጀምሮ፤ ሩስያ ሶቭየት ሕብረት ከሄደ በኋላ የሩስያ ጎረቤት ሃገራት እና ምዕራብ ሃገሮች ሩስያ ራስዋ ትፈረካከሳለች ብለዉ አሰፍስፈዉ የሚጠብቁበት ጊዜ ነበር። በዚህ ወቅት ነዉ ፑቲን ወደ ስልጣን መጥተዉ ቀስ በቀስ ስርዓት ማስያዝ የሚጀምሩት። »  
የምሥራቅም ሆነ የምዕራብ ባለታሪኮች ስለኢትዮጵያ ዉስጣዊ ሁኔታ እና ታሪክ ሳይረዱ ነዉ በአብዛኛዉ መጽሐፍን የሚያሳትሙት ያሉት ፕሮፊሰር ንጉሴ ለሩስያ ቋንቋ አንባቢዎች ያቀረቡት መጽሐፋቸዉ ታሪክን አንድ በአንድ ያስቀመጠ መሆኑን ተናግረዋል።           
"ቭላድሚር ፑቲን" የተሰኘዉ የመጀመርያዉ ክፍል መጽሐፍ እስከ ጎርጎረሳዉያኑ 2000 ዓ,ም ድረስ ያለዉን የፑቲንን የሕይወት ታሪክ ያስቃኛል። ደራሲዉ ኘሮፌሰር ንጉሴ ካሣዬ ወልደሚካኤል ሁለተኛዉን ክፍል ለማሳተም ሥራ ላይ መሆናቸዉን ተናግረዋል። የሩስያዉ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ሶቭየት ሕብረት ተበታትና የልሰንን ተክተዉ ወደ ስልጣን ከመጡ 20 ዓመትን ደፍነዋል። በርግጥ ሁለት ጊዜ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ሁለት ጊዜ ደግሞ በፕሬዚደንትነት መሆኑ ነዉ። የሩስያ ፕሬዚዳንት ቦሪስ የልሰን ስልጣን ዘመን የሩስያ የስለላ ድርጅት ዋና ተጠሪ የነበሩት ቭላድሚር ፑቲን በጎርጎረሳዉያኑ 1999 ዓ,ም ሩስያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነዉ ተሾመዋል። ቭላድሚር ፑቲን ከሳቸዉ ቀደም እንዳሉት እንደ ፕሬዚዳንት ቦሪስ የልሰን በቮድካ የማይታሙ፤ ከ 1990 ዓ,ም ጀምሮ ሩስያ ከገባችበት የድሕነት እና የፖለቲካና ቀዉስ፤ መንግለዉ ያወጡ፤ ሃገሪትዋ የነበረባትን ብድር ከፍለዉ የጨረሱ፤ ሩስያና የቼችንያን ጦርነት ያበቁ እንዲሁም ሞስኮ ዳግም በዓለም የፖለቲካ መድረክ ተሰሚነት እንዲኖራት ያበቁ ሲል የዶይቼ ቬለዉ ሚዮድራግ ሶሪች አሞካሽቶቸዋል። በሌላ በኩል ግን ይላል ሶሪች ባቀረበዉ ሃተታ ወጣት ሩስያዉያን ፈጣን ለዉጥና እድገት በሚታይበት ዓለም እየኖርን የክሬምሊን ቤተ መንግሥት ግን በአለበት እየሄደ ነዉ ሲሉ በፑቲን መንግሥት ላይ ቅሬታቸዉን እንደሚያሰሙ አልደበቀም። ዓለም በተንቀሳቃሽ ስልክ በፈጣን መረጃ በመለዋወጥ ጠባብ በሆነችበት በአሁን ዘመን፤ፑቲን የጀታ ስልክ እስከዛሬ ተጠቅመዉ እንደማያዉቁ ሲናገሩ በመሰማታቸዉ፤ በወጣቱ ዘንድ እጅግም ይሁንታን ባያገኙም፤ የሃገሪቱ ነዋሪዎች በሩስያ የፖለቲካ የፀጥታና የምጣኔ ሁኔታ በመሻሻሉ የፑቲንን መንግሥት አሜን ብለዉ መቀበላቸዉን አስቀምጦአል። በሞስኮ በሚገኝ ዩንቨርስቲ ሌላዉ መምሕርነት የሚያገለግሉት ፕሮፊሰር ዘነበ ክንፉ ታፈሰ ናቸዉ። ፕሮፊሰር ዘነበ በሩስያ የአፍሪቃዉያን ዲያስፖራ ማኅበር ፕሬዚደንትም እንደሆኑ ነግረዉናል። 
«የማስተምረዉ በሞስኮ በሚገኝ ዩንቨርስቲ፤ ዓለም አገፍ ግንኙነት እና ዓለም አቀፍ ጋዜጠኝነትን ነዉ። በዩንቨርስቲዉ ከሦስተኛ ዓመት በላይ ያሉ ተማሪዎችን ሲሆን በኢትዮጵያ በርግጥ አላስተማርኩም አልሰራሁም። ቢሆንም በእስያ በላቲን አሜሪካ በሚገኙ የተለያዩ ዩንቨርስቲዎች አጫጭር ኮርሶችን እሰጣለሁ። ከመጀመርያዎቹ አፍሪቃዉያን የዩንቨርስቲዎች አንዱ ነኝ። በሞስኮ በተለያዩ ዩንቨርስቲዎች የሚስተምሩ ኢትዮጵያዉያን ብሎም አፍሪቃዉያን ይገኛሉ። በሩስያ የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያንን ለማነጋገር መነሻ የሆነኝ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ባለፈዉ ሰሞን ወደ ስልጣን ከመጡ 20 ዓመት መሙላቱን ተከትሎ ነዉ። ከሩስያ የምንሰማዉ ዜና በተለይ በሞስኮ አደባባዮች ባለፈዉ ሰሞን ከፍተኛ ተቃዉሞ እየተካሄደ ነዉ። እንደዉ የፑቲን ተቀባይነት በሃገሪቱ ሆነ በዉጭ ሃገር ዜጎች ምን ያህል ነዉ? የኢትዮ-ሩስያን የወዳጅነት ግንኑነት ያጫወቱን በሩስያ ከፍተኛ ተቋም እና የዲያስፖራ ፕሬዚዳንት ፕሮፊሰር ዘነበ ክንፉ ታፈሰ ከአስራ ሁለት ቀን በኋላ አዲስ አበባ ላይ ለሦስት ቀናት በሚካሄደዉ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ሳምንት ለመካፈል ወደ አዲስ አበባ ያቀናሉ፤ ረዘም ካለ ቃለ ምልልሳችን መጨረሻ ላይ ይሄን ሳልናገር ማለፍ አልፈልግም አሉ።

Professor Zenebe Kinfu
ምስል Zenebe Kinfu
Äthiopien Buchcover Haile Selassie von Nigusie Kassae
ምስል Nigusie Kassae

ሙሉዉን ስርጭት የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉ! 

 

አዜብ ታደሰ
ነጋሽ መሐመድ