1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፍትህ የራቃት ቡሩንዲ

ሐሙስ፣ ጥር 26 1997

የቡሩንዲን ችግር አስመልክቶ በአገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በሚየርጉት ጥረት ዙሪያ ለመነጋገር የደቡብ አፍሪካዉ ምክትል ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ ከዑጋንዳዉ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒና ከታንዛንያዉ ፕሬዝዳንት ቤንጃሚን ምካፓ ጋር ኢንቴቤ ተገናኝተዋል።

https://p.dw.com/p/E0kT

በአገሪቱ አስር አመታት በላይ የፈጀዉ የእርስበርስ ጦርነት ያስከተለዉ መዘዝ የዜጎቹን አጠቃላይ ደህንነት ጥያቄ ላይ የጣለ ሆኗል።
ሁለቱ ተፎካካሪና ተፋላሚ ወገኖች ጉዳዩን ሊተዉ በተቃረቡበት ወቅት ደግሞ በመላዉ አገሪቱ ወንጀል ነግሷል።
በቅርቡ በተካሄደዉ ጥናት መሰረትም 300 የግድያ፤ 72 የአፈናና 500 የታጣቂዎች ዘረፋ በሶስት ወራት ዉስጥ መፈፀሙ ተመዝግቧል።
ከቅኝ ገዢዎቿ ከፓርቱጋሎች ተላቃ ነፃነቷን ከተቀዳጀች ወዲህ ዜጎቿ የተረጋጋ ህይወትም ሆነ ሰላም አይተዉ አያዉቁም።
ከነፃነት በኋላ በ1956ዓ.ም. ቡሩንዲ በሙዋሚ ሙዋምቡስታ መሪነት ራሷን የቻለች መንግስት ለመሆን በቃች።
ሆኖም ብዙም ሳይቆዩ ሙዋምቡስታ በገዛ ልጃቸዉ በናታራ ቪ መፈንቅለ መንግስት ተካሂዶባቸዉ ከስልጣን ተወገዱ።
በሁለት አበይት ጎሳዎች ማለትም በሁቱና ቱትሲ መካከል በሚደረግ የበላይነት ፉክክር ሰላሟ የደፈረሰዉ ቡሩንዲ ነፃ ከወጣችበት ጊዜ ወዲህ የፓለቲካ ግለት እየተባባሰባት በተደጋጋሚ መፈንቅለ መንግስት እየተካሄደባት ኖራለች።
በአገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በዲሞክራሲያዊ ምርጫ በሰኔ 1985 የተመረጡት የቀድሞዉ ፕሬዝዳንቷ ሜልሾር ናዳዳዬ በተመረጡ በአንድ ወር ጊዜ ዉስጥ በተካሄደ መፈንቅለ መንግስት ነበር የገደሉት።
ሁለተኟዉ ከሁቱ ጎሳ የመጡት ፕሬዝዳንት ሳይፕሪን ናታርያሚራም በሚያዝያ 1986ዓ.ም. እሳቸዉንና የወቅቱን የሩዋንዳ ፕሬዝዳንት ጁቬናል ሃባያሪማናን በጫነችዉ አዉሮፕላን ላይ በተከፈተዉ ተኩስ ተገደሉ።
በወቅቱ የተፈፀመዉ ግድያ ባስከተለዉ መዘዝ የተቀሰቀሰዉ ግጭትም ወደ300,000 የሚደርሱ ንፁሃን ዜጎችን ህይወት ለሞት ዳረገ።
በአሁኑ ጊዜ አገሪቱን የማስተዳደር ኃላፊነት የተረከበዉ ከሁለቱ ጎሳዎች የተዉጣጡ መሪዎች ያሉትና የዛሬ አራት አመት ታንዛንያ አሩሻ ላይ በተደረሰዉ ስምምነት መሰረት የ36 ወራት ስልጣን የተሰጠዉ የሽግግር መንግስት ነዉ።
ከሁቱ ጎሳ የመጡት ፒተር ቡዮያ በፕሬዝዳንትነት የሁቱዉ ዶሚቲየን ናዳይዝየ በምክትል ፕሬዝዳንትነት የሚመሯት ቡሩንዲ የተኩስ አቁም ስምምነት ቢደረግባትም አልፎ አልፎ ዉጊያና ግጭቱ አልቆመም።
ከነፃነቷ ማግስት ጀምሮ ሰላም የራቃት ቡሩንዲን ለማረጋጋት የመሸምገል ኃላፊነት ከወሰዱት የታላቁ ሃይቅ አባል አገራት መካከል የዑጋንዳዉ ፕሬዝደንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ቡድኑን በሊቀመንበርነት ሲመሩ የታንዛንያዉ ፕሬዝዳንት ቤንጃሚን ምካፓ ምክትል ናቸዉ።
የደቡብ አፍሪካዉ ምክትል ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማም ኔልሰን ማንዴላን በመተካት የሽምግልና ተግባር እያከናወኑ ቢሆንም የአሁኑ የቡሩንዲ ፕሬዝዳንት በአገሪቱ መቼ ፍትህ ሰፍኖ እናይ ይሆን በማለት አቤቱታቸዉን እያሰሙ ነዉ።
በአገሪቱ ከሚካሄደዉ ግጭት በተጨማሪ ሙስና ግንባር ቀደም ችግር መሆኑን ለግብረ ሰናይ ስራ በአገሪቱ የሚገኙ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በይፋ የሚናገሩት ጉዳይ ሆኗል።
በስፍራዉ የሚገኙ የተባበሩት መንግስታት ባለስልጣኖች እንደሚሉት በአገሪቱ በሰፈነዉ ስርዕተ አልበኝነት ሳቢያ በዋና ከተማዋ ቡጁምቡራ ቢያንስ ስምንት ሰዉ በቀን ዉስጥ ይገደላል።
ካለፈዉ ሰኔ ወር ጀምሮ የተባበሩት መንግስታት የሰላም አስከባሪ ጦር በቡሩንዲ ስራዉን በመጀመር የቀድሞ አማፅያንና የመንግስትን ወታደሮችን ትጥቅ ማስፈታት ጀምሯል።
እለት እለት ሰዎች አንድ በአንድ እየተገደሉ ነዉ፤ መቼ ይሆን ፍትህ በጣም ርቆ ከሄደበት ተመልሶ በአገሪቱ ስልጣን የሚኖረዉ? በአገሪቱ የመንግስት ስርዓት አለመኖር ህዝቡ የራሱን ፍትህ እንዲፈልግ ያስገድደዋል ባይ ናቸዉ ፕሬዝዳንቱ።
ወንጀል የፈጸሙ ሰዎች ማጣራት ከተካሄደ በኋላ በነፃ ይለቀቃሉ፤ ያን የሚመለከተዉ ሰላማዊ ዜጋ በጣም ከማዘኑ በላይ ፍትህ ባለመኖሩ ሰዎች ያለምንም ስጋት ተደጋጋሚ የወንጀል ተግባር ሲፈፅሙ ይታያል ይላል በአገሪቱ የሚገኝ አንድ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድን።
በዚህም ሳቢያ በርካታ የአገሪቱ ዜጎች ወደጎረቤት አገራት በተለይም ወደታንዛንያ ለመሰደድ ተገደዋል።
ሆኖም እነዚህ ስደተኞች በተሰደዱበት አገርም የተመቻቸዉ ነገር የለም፤ እንደዉም በቅርቡ በታንዛንያ ከሚገኙ ስደተኞች መካከል ሁለት ቤተሰቦች ወደ ቡሩንዲ እንዲመለሱ በፍርድ ቤት ተወስኖባቸዋል።
በአካባቢዉ ለእርዳታ ተግባር የተሰማሩት የተባበሩት መንግስታት ድርጅቶች ሰራተኞች እንደሚሉት ዉሳኔዉ የሰዎቹን ህይወት አደጋ ላይ የሚጥል አደገኛ ዉሳኔ ነዉ።
በአገሪቱና በአማፅያኑ መካከል አሩሻ ላይ በተደረሰዉ ስምምነት መሰረት በፊት በወንጀል ተግባር ተሳትፍ የነበራቸዉ ሰዎች የመንግስት ባለስልጣናት የመሆን እድል አግኝተዋል።
በአገሪቱ ፓርላማም ወንጀል የፈፀመን ሰዉ በሞት ሊያስቀጣ የሚያስችል የህግ አንቀፅ እንዲያፀድቅ ረቂቅ ህግ ቀርቦለታል።
ምንም እንኳን በአገሪቱ የወንጀል ተግባር በመበራከቱ ጠንከር ያለ ህግ ቢያስፈልግም ወንጀልንም የመቆጣጠሪያ በርካታ ዘዴ እያለ የሞት ዉሳኔን እንደመፍትሄ መዉሰድ አግባብ አይደለም የሚሉ ወገኖች አሉ።
ያም ሆነ ይህ የተፈጥሮ የማዕድናት ሃብት ለሌላትና 40 በመቶ የሚሆነዉ ምጣኔ ሃብቷ በእርዳታ ላይ ለተመሰረተዉ ለዚች አገር ሰላም አስፍኖ በልማት የሚያራምዳት የተጠናከረ ማዕከላዊ መንግስት ያስፈልጋታል።
በአብዛኛዉ ምጣኔ ሃብቷ በእርሻ ላይ የተመሰረተዉ ቡሩንዲ ከአለም የሙዝ አምራች አገሮች መካከል 5ኛ ስትሆን ቡናና ጥጥም ግንባር ቀደም የዉጪ ምንዛሪ የሚያስገኙላት ምርቶቿ ነበሩ።