1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«ፌስቡክ» መገናኛ መረብ እና ማህበረሰባችን

ሰኞ፣ የካቲት 3 2006

በያዝነዉ ሳምንት ማክሰኞ ፊስቡክ የመገናኛ መረብ ከተመሰረተ 10ኛ ዓመቱን ደፈነ። በፊስ ቡክ ፤ህዝባዊ ቅስቀሳ፤ በፌስቡክ አብዮት፤ በፌስቡክ መማመር፤ በፊስ ብክ ትዉዉቅ፤ እንዲሁም በፌስቡክ ስድድብ ሌላም ሌላም ይታያል። በአሁኑ ግዜ የኢንተርኔት አገልግሎት የማግኘት እድሉ ያላቸዉ፤ የፊስ ቡክ መረብን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተጠቃሚ ናቸዉ።

https://p.dw.com/p/1B3nM
Facebook Like Logo Button
ምስል picture alliance/AP Photo

በዘመናችን የድረ- መረብ አገልግሎት ተስፋፍቶ ዓለም ከጠበበችበት ግዜ ጀምሮ ፤የብዙሃን መገናኛም ያንኑ ያህል ቤት ድረስ አንኳክቶ መረጃ መድረስ ጀምሮአል። የፌስቡክ ተጠቃሚዎች መረቡን በአግባቡ ይጠቀሙበታልን? እንደ አብዛኞች ተጠቃሚዎች አስተያየት፤ ፊስቡክ ብዙ መረጃዎችን በፈጣን አገልግሎት ለተጠቃሚ ሲያዳርስ የዛያኑ ያህል፤ አንዳንድ ተጠቃሚዎች የቤት ዓመላቸዉን የሚያወጡበት የድረ-መገናኛ ነዉ።

US Soldat in Afghanistan Archiv 2011
ምስል Bay IsmoyoAFP/Getty Images

የዛሪ ሶስት ዓመት ግድም፤ በቱኒዝያና በግብፅ የታየዉ ህዝባዊ አብዮት፤ በተለይ በወጣቱ ዘንድ መረጃ ከመቅፅበት በመለዋወጥ፤ ህዝብ ለለዉጥ በአንድነት ኢንዲነሳሳ የረዳዉ የመገናኛ መረብ ቢኖር የፊስቡክ ነዉ። በፌስቡክ፤ በርካታ ዕዉቀቶችና በፅሑፍ ፈጠራዎችን መለዋወጥ እንደሚቻለዉ ሁሉ ብዙ ፀያፍ የሆኑ መልክቶችም ሲሰራጩባቸዉ ይታያል ። በኢትዮጵያ ታዋቂ የሆነዉ ጦማሪ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፤ በገፁ ላይ ባስቀመጠዉ ጽሑፉ ፤ « ምንም እንኳ የኛ ሙሽራ ኩሪባቸዉ በእንጊሊዝኛ አናግሪያቸዉ እያልን፤ ስንዘፍን ብንኖርም የእንግሊዘኛ ችሎታችን ለአቅም ስድብ የሚሆን ባለመሆኑ፤ ተገላግለናል» ሲል በፊስ ቡክ ላይ የሚታየዉን አንዳንድ አስነዋሪ የስድብ ጉዳይ በዝርዝር አስቀምጦታአል። ይህን የድረ መገናኛ እርሶ እንዴት ይጠቀሙበታል? ኦስሎ፤ ኖርዌይ ነዋሪ የሆኑት አንጋፋዉ ጋዜጠኛ አበራ ለማ እንደሚሉት፤ አጠቃቀሙን ላወቀበት ጥሩ የመገናኛ ዘዴ ነዉ። አጠቃቀሙን ግን በጥንቃቄ ልናቅበት ይገባል።

እንደ ጦማሪ ዳንኤል ክብረት ገለፃ « የቤት ዓመል ገበያ ይወጣል ነበር የሚባለዉ፤ አሁን አሁን እርሱ ተቀየሮ ፤ የቤት ዓመል በኢንተርኔት ይወጣል ነዉ። ስንቱ ተሳዳቢ፤ ስንቱ ተራጋሚ ስንቱ ተደባዳቢ፤ በኢሜል፤ በብሎግ፤ በፊስቡክ እንዲሁም በትዊተር መገናኛ መረቦች ሲዥጎደጎድ ይታያል። እናም ይላል በጽሁፉ ዓለማችን በኢንተርኔት ሽምቅ ተሳዳቢዎችን አፍርታለች። በሌላ በኩል ዲያቆን ፍሪዉ ሰይፉ በበኩላቸዉ ዓለማችን ይላሉ፤ ዓለማችን በመረጃ እየተጥለቀለች ባለችበት ዘመን፤ የፊስ ቡክ ተጠቃሚ አይደለሁም፤ ፊስቡክ አሰስ ገሰሱን ስለሚሰበስብ፤ ከጥቅሙ ጉዳቱ አመዝኖ አግንቸዋለሁ ሲሉ ተናግረዋል።

በምዕራቡ ዓለም በፊስ ቡክ እዉነተኛ ስማቸዉን የማይፅፉ፤ ተሰዉረዉ የሌሎችን ፎቶ አልያም ስዕል እንደ መለያ የሚለጥፉ እና ወንጀል የፈፀሙ አንዳንድ ሰዎች፤ በወንጀል መያዛቸዉ የመገናኛ ብዙሃን በይፋ ሲገለፅ አልፎ አልፎ ይደመጣል። በዚህም ምክንያት እዚህ ጀርመን ወላጆች ልጆቻቸዉን የፊስ ቡክ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚፈቅዱላቸዉ፤ ልጆቹ ራሳቸዉን የገዙ ሲመስላቸዉ፤ ከተወሰነ ዓመት በኃላ እና ያም በወላጆች ቁጥጥር ብቻ ነዉ። አንጋፋዉ ጋዜጠኛ አበራ ለማ፤ ፊስ ቡክ ጥሩ ፅንሰ ሃሳብ ያዘለ ሃሳብ መቀያየርያ፤ የስነ-ግጥምና የስነ-ፅሁፍ መለዋወጫ፤ አዲስ ዜና መስምያ መድረክ ነዉ ይህንንም መድረክ፤ ጥሩ መገልገያቸዉ ያደረጉ ጥቂቶች እንዳልሆኑ ገልፀዋል።

በዩናይትድ ስቴትስ ነዋሪ የሆኑትና፤ ኢትዮጵያዉያን ገጣምያንን በፊስ ቡክ ገፁ በማሰባሰባቸዉ የሚታወቁት «ኢትዮጵያን ፖየትሪ» የተሰኘዉ የፊስቡክ ገፅ መስራች አቶ አቶ ሳምሶን ደምሴ ተፈራ፤ እንደሚሉት ፊስቡክን፤ በብልሃት ከተጠቀሙበት እጅግ ጠቃሚ የሚሰጥ የብዙሃን መገናኛ ነዉ። ዲያቆን ፍሪዉ ሰይፉ፤ እንደሚሉት ግን የፊስ ቡክ ጥቅም ስራ ከማስፈታት እና የስራ ፍላጎትን ከማሽመድመድ በቀር የሚሰጠዉ ፋይዳ የለም ሲሉ ተናግረዋል። አንጋፋዉ ጋዜጠኛ አበራ ለማም ቢሆን የዲያቆን ፍሪዉ ሰይፉን ሃሳብ ይጋራሉ፤ እንዲያም ቢሆን እርግፍ አድርጎ መተዉ ሳይሆን መርጦ መጠቀም መቻልን ማወቅ አለብን ነዉ።

Deutsche Welle 100.000. Facebook Fan
ምስል DW

ፊስ ቡክ ማህበራዊ ድረገፅ የተመሰረተበትን 10 ኛ ዓመት በማስመልከት፤ አጠቃቀሙ ላይ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል ያሉን የለቱን እንግዶቼን ለሰጡን ቃለ ምልልስ በጣብያዉ ስም አመሰግናለሁ። አድማጮች ዶቼ ቬለ የአማርኛዉ ስርጭት ክፍል ዶቼ ቬሌ አምሃሪክ በሚል ስም አድማጮቼን በፊስቡክ ማሰባሰቡን ያዉቁ ኖርዋል። በፊስቡኩ ቋንቋ ላይክ አድርጉን፤ ማለትም የመረቡ አባል ሆናችሁ በየለቱ በገፁ ላይ የምንለጥፋቸዉን አበይት ዜናዎች እንድትከታተሉ፤ እንጋብዛለን ሙሉ ቅንብሩን የድምጽ ማድመጫ ምስሉን በመጫን ያድምጡ።

አዜብ ታደሰ

ተክሌ የኋላ