ጸረ-ሙባረክ ሰልፈኞችና ፖሊሶች ተጋጩ
ቅዳሜ፣ ኅዳር 20 2007ሰዎቹ የሞቱት ፖሊስ አደባባዩ ላይ የተሰበሰቡትን ሰልፈኞች በአስለቃሽ ጢስ እና በውሃ ለመበተን በተንቀሳቀሰበት ወቅት መሆኑም ተገልጿል። ሠልፈኞቹ አደባባይ የወጡት፥ የ86 ዓመቱ የቀድሞው የግብፅ ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክ በሥልጣን ዘመናቸው ተቃውመዋቸው አደባባይ የወጡ 800 ሠልፈኞችን አስገድለዋል በሚል ተከፍቶባቸው ከነበረው ክስ በፍርድ ቤት በነፃ መሰናበታቸውን ለመቃወም ነበር ተብሏል።
በቀድሞው የግብፅ ፕሬዚደንት ሆስኒ ሙባረክ ላይ ተክፍቶ የነበረው የፍርድ ችሎት ቅዳሜ ዕለት ሙባረክን ነጻ ቢያሰናብትም የ86 ዓመቱ ሙባረክ ለጊዜው በእስር ቤት እንደሚቆዩ ታውቋል። የቀድሞው መሪ ከ800 በላይ ለሚቆጠሩ ተቃዋሚ ሰልፈኞች ሕይወት መጥፋት ተጠያቂ ተብለው ነበር ክስ የተመሰረተባቸው። ችሎቱ ከሦስት አስርተ ዓመታት በላይ ግብፅን ያስተዳደሩት ሙባረክን ጨምሮ፥ የቀድሞው የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሃቢብ አል- አድሊ፣ ጋማል እና አላ የተባሉትን የሙባረክ ሁለት ወንድ ልጆች እና ሌሎች ተከሳሾችንም ነፃ አድርጓል። አቃቤ-ሕጉ ሙባረክ በሞት እንዲቀጡ በተደጋጋሚ ጠይቆ ነበር። እኤአ በ2011 ዓም ሙባረክን ከሥልጣን መንበራቸው ለማንሳት በተቀሰቀሰዉ ንቅናቄ በጊዜው የነበረው መንግሥት ተቃዋሚዎች ላይ ከፍተኛ የኃይል ርምጃ መውሰዱ ይታወሳል፤ ይሁንና ሆስኒ ሙባረክ ከተወነጀሉበት ክስ ነፃ መሆናቸዉን እና «ምንም አይነት ግደሉ የሚል ትዕዛዝ» አለማስተላለፍቸዉን በተደጋጋሚ ሲናገሩ መቆየታቸዉ ይታወቃል። ሙባረክ በ2012 ዓም በተካሄደው ችሎት የሞት ፍርድ ተበይኖባቸው፤ ባቀረቡት ይግባኝ መሰረት፤ በቂ ማስረጃ ባለመቅረቡ ነው የሞት ፍርዱ ተሽሮላቸው አዲስ ችሎት ተክፍቶ የነበረው።