ጥንቃቄ የሚሻው የአእምሮ ጤንነት
ማክሰኞ፣ ጥቅምት 4 2012
የዓለም የጤና ድርጅት የአእምሮ ጤና ቀን በመላው ዓለም ባለፈው ሐሙስ ሲታሰብ ራስን ማጥፋት ወይም ሲውሳይድን ዋና መነጋገሪያ እንዲሆን አቅርቧል። በየትኛውም ጊዜ እና ቦታ ሊፈፀም የሚችለውን ይህን ድርጊት ማስቆም እንደሚቻልም ጠቁሟል። ራስ ደህና አለች የምትባል አንዲት ፍጥረት አለች። ይህ ማለት የግልን ደህንነት ብቻ ሳይሆን ቅድሚያ መላ አካልን የሚዘውረው አእምሮ ጤንነቱ መጠበቅ እንደሚገባም ማመላከቻ ነው። የራስን ሕይወት በራስ እጅ ለመቅጠፍ የመወሰኑ መንስኤ ምንም ይሁን ምን ቅድሚያ ሌሎች አውቀውት ቢሆን ለመከላከል እንደሚቻል የአእምሮ ጤና ሀኪሞች ያምናሉ። እንዲህ ወዳለው ርምጃ የሚያደርሰው ከባድ ድብርት ሀኪሞቹ እንደሚሉት ዲፕረሽን ደግሞ በወጣቶች ላይ መጉላቱ ሌላው አነጋጋሪ ጉዳይ ሆኗል። የወጣቶች ምድር በሆነችው ኢትዮጵያ ከድህነቱ ጋር የፍላጎቶች አለሟላት ወደዚህ የሚመራ ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
በየዓመቱ በመላው ዓለም የ800 ሺህ ሰዎች ሕይወት በዚህ መንገድ እንደሚቀጠፍ የዓለም የጤና ድርጅት ያመለክታል። በየ40 ሰከንዱ ደግሞ አንድ ሰው። ድርጅቱ ባለፈው ሐሙስ ይህን ያነሳበት ዋናው ምክንያት ችግሩ እጅግ ስር የሰደደ ሆኖ ሳለ ችላ መባሉን መሠረት በማድረግ ሰዎች ከአእምሮ ጤንነት ጋር በማያያዝ እንዲነጋገሩበት እና ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማድረግ እንደሚገባ አሳስቧል። ለመሆኑ ራስን የማጥፋት ድርጊት ከአእምሮ ጤንነት ጋር ምን ያገናኘዋል? በአዲስ አበባ ዮንቨርስቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ የአዕምሮ ህክምና ትምህርት ክፍል መምህር እና ሀኪም የሆኑት ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ኃይለኛ የአእምሮ ህመም ራስን ለማጥፋት ሊያደርስ እንደሚችል ነው ያመለከቱት። የድብርት ስሜት ማለትም ዲፕረሽን ከፍተኛ ደረጃ ሲደርስ ወደዚህ ድርጊት ሊያመራ እንደሚችል በመጥቀስም በዝርዝር ያስረዳሉ።
የአእምሮ ሀኪም እና ባለሙያው እንደሚሉት አንዳንድ ሰዎች ድብርቱ የሚፈጥርባቸውን ጫና ለመገላገል ብለው ወደሱስ የሚገቡበት አጋጣሚ አለ። ያ ደግሞ ሌላ ተጨማሪ አባባሽ ሊሆንባቸው ይችላል። ወጣቶች ምንም እንኳን የመጪው ኃላፊነት ተረካቢ ትውልድ መሆናቸው ቢታወቅም ከ15 እስከ 29 ዓመት በሚሆናቸው ወጣቶች ዘንድ ሕይወታቸውን ሊቀጥፍ ከሚችሉ ዋነኛ ምክንያቶች በሁለተኛ ደረጃ የሚገኘው ራስን ማጥፋት መሆኑ ተደርሶበታል። ይህ ጉዳይ ኢትዮጵያም ላይ ተመሳሳይ እንደሆነ ነው ከፕሮፌሰር መስፍን ገለጻ መረዳት የሚቻለው።
ውሎ አድሮ ወደሌላ ሊገፋፋ እንደሚችል በሚታመነው ድብርት ወይም ዲፕረሽን የተጠቁ ወጣቶች ለየት ያለ ባሕሪ እንደሚያሳዩ ነው የአእምሮ ሀኪም እና መምህሩ የሚያሳስቡት። ወላጆችም ሆኑ መምህራን ልብ ሊሉት እንደሚገባም ያሳስባሉ። የድብርቱ ስሜት የተባባሰባቸውን ሰዎች ጠጋ ብሎ መጠየቅ ማወያየቱ በሀገራችን እጅግም ያልተለመደ እና ሊያባብስ ይችላል የሚል አስተሳሰብ ቢኖርም ያንን አልፎ በችግር ውስጥ ያሉት ወገኖች ማነጋገሩ አደጋውን ለመቀነስ እንደሚረዳም ነው ባለሙያው ያስገነዘቡት። የድብርት ስሜት ያጋጠማቸው ሰዎች ሊያደርጉት ይገባል ያሉትን ዋና መፍትሄም እንዲህ ይመክራሉ.
ራስን የማጥፋቱ ጠላፊ ፈተና ማንንም ሰው የትም ቦታ ሊያጋጥመው እንደሚችል ነው የስነልቡና እና የአእምሮ ህክምና ባለሙያዎች የሚናገሩት። ግን ደግሞ ለመከላከል እንደሚቻልም አስረግጠው ይገልጻሉ። የዓለም የጤና ድርጅት መንግሥታት ራስን የማጥፋት ድርጊት እንዳይፈፀም በብሔራዊ ደረጃ መከላከል የሚያስችል ስልት እንዲኖራቸውም ይመክራል። ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ በበኩላቸው ከምንም በላይ ደግሞ በወጣቶች ጉዳይ ላይ የሚሠሩ አካላት የወጣቱ ችግር ምንድነው የሚለውን በትኩረት ሊሠሩበት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል። እያንዳንዱ ሰውም በቤተሰብ ደረጃ፣ በትምህርት ቤት፣ በሥራ ቦታም ሆነ በጓደኝነት በሚቀራረብባቸው መንገዶች ሁሉ የበኩላችንን በማድረግ እንዲህ ያለውን ጸጸት የሚያስከትል የሰዎች ውሳኔ ሊያስቀር እንደሚችል ይታመናል። ለሰጡን ሙያዊ ማብራሪያ ከፍተኛ የአእምሮ ህክምና ባለሙያውን በማመስገን ለዕለቱ ያልነውን በዚሁ አበቃን።
ሸዋዬ ለገሠ
አዜብ ታደሰ