ጥበብ በጠርሙስ
እሑድ፣ ጥቅምት 25 2011ዳዊት ተፈራ የጠርሙስ ጥበብ ባለሙያ ነው። በፊልም ላይ የመርከቦችን ቅርጽ በማየት ለመስራት እንደተነሳሳ ይናገራል። በረጅም ብረት በመታገዝ ወደ ጠርሙሱ የውስጠኛው ክፍል የሚገጥማቸውን ዕቃዎች ያስገባል። በተፈለገበት ቦታ በማስቀመጥ ቅርጹን ነፍስ ይዘራበታል። ጥንቃቄ የሚጠይቅና በትዕግስት የሚሰራ እርጋታና ጥሞናን ሰጥቶ የሚሰራ ነው። እያንዳንዱ ጥንቃቄ የጎደላት እንቅስቃሴ ስራውን እንዲበላሽ ያደርገዋል ይላል ዳዊት። የወዳደቁ ጥሬ ዕቃዎችም ይጠቀማል። ጨርቅ፣ ፌስታል፣ እንጨት፣ ክር፣ ጅብሰም፣ ብረት የመሳሰሉት የጥበቡ መጠቀሚያዎቹ ናቸው። ጥበቡ በብዙ መንገድ ይገለጻል። ሁሉም ነገር ከአርት ተነስቶ ነው ወደ እውነታው የሚመጣው ይለናል። አንድ የጠርሙስ ውስጥ ጥበብን ቅርጽ ለመስራት እንደቅርጹ ሁኔታ የሚወሰን ቢሆንም እስከአንድ ወር እንደሚፈጅበት ገልጾአል። ጥበብን ለነፍሴ እንደሚሏት የጥበብ ሰዎች ይሰራል እንጂ በሙያው የካሜራ ባለሙያ ነው።
በዚህ ጥበብ ጠርሙሶች ለእርሱ መልዕክት ያስተላልፍልኛል ይላል። በእኔ በኩል ጥረት እያደረኩ ነው። እየሰራሁ ለህዝብ እያቀረብኩ ነው። ሌሎችም እንዲሰሩ አድርጊያለሁ። ተጨማሪ ሌላ ስራ ካልተሰራ በዚህ የአርት ሙያ መኖር አስቸጋሪ እንደሚሆን ይናገራል። አቶ ቅዱስ ማርቆስ ይባላሉ። የጥበብ አድናቂ ናቸው።ጥበብን ከማድነቅ ቀድሞ እንዴት ሰራው የሚለው ነገር የበለጠ አመራምሯቸዋል። ከውጭ ሆኖ ለመስራት የሚከብድ ያሉትን የዳዊትን ትዕግስቱንም ጥበቡንም አድንቀዋል። እስከዛሬ ካዩትም የዳዊት የተለየባቸው እንደሆነ በጠርሙስ ቀዳዳ እየገጣጠመ መስራት መቻል ከመደነቅም አልፈው አስጨናቂ እንደሆነባቸው ተናግረዋል። እያሱ ሲሳይ ሰአሊና የስዕል አስተማሪም ነው። ሰዎች አርትን ይገልጽልኛል በሚሉት ሀሳባቸውን ይገልጻሉ። እሱ የሚጠቀምበት መንገድ ሀሳቡን የሚገልጽለት ሆኖ ስላገኘው ተጠቅሞበታል። የጥበብ አሰራር ዘዴውም እንደወደደው፤ ጥሞናን የሚፈልግ፣ አድካሚ እና ጥንቃቄ የሚፈልግ ሆኖ አግኝቶታል።
የጠርሙስ ውስጥ ጥበብ በብዙዎች ዘንድ ያልታየና ያልተሰራበት ነው። ፈጠራው ለረጅም ጊዜ ትኩረት ሰጥቶ መስራት የሚፈልግ ስራ ነው። የበለጠ የሚያግዘው ሰው ቢያገኝ ጥበብን ሊያሳድገው ይችላል እንደባለሙያው እያሱ አስተያየት።
ነጃት ኢብራሂም
አዜብ ታደሰ