ግብፅ ተቃዉሞ ከሙባረክ እስከ ሙርሲ
ዓርብ፣ ጥር 17 2005
የግብፅ ሕዝብ የፕሬዝዳት ሆስኒ ሙባረክን አምባገነናዊ ሥርዓት በመቃወም ታላቅ ሕዝባዊ ሠልፍ የጀመረበት ሁለተኛ ዓመት ዛሬ ተከብሯል።ግብፆች «የቁጣ ዕለት» ባሉት በዚያ በጎርጎሮሳዉያኑ ጥር 25 ቀን 2011 የጀመሩት የአደባባይ ትግል ከሰላሳ-ዓመት በላይ የፀናዉን ጨቋኝ ሥርዓት በገረሠሠ ድል ተጠናቅቋል።ሠልፍ ተቃዉሞዉ ግን ደረጃና ዓለማዉ ይለያይ እንጂ ዛሬም እንደቀጠለ ነዉ።ባለፉት ሁለት ዓመታት የተቃዉሞ ማዕከል ከሆነዉ ከካይሮዉ ተሕሪር አደባባይ ያልተለየዉ ወጣት ኢብራሒም ከንደሪያን እንደሚለዉ አብዮቱ እንደቀጠለ ነዉ።የዶቸ ቬለዉ ማቲያስ ዛይለር ወጣት ኢብራሒምን አነጋግሮ ያዘጋጀዉን ዘገባ ነጋሽ መሐመድ አጠናቅሮታል።
ያ! የታላቅ ሕዝባዊ አብዮት፥ ትልቅ ማዕከል፥ ያ! ሕዝብ ካበረ የታንክ፥ መድፍ፥ የመትረየስ ጠመንጃ ጋጋታ እንደባይበግረዉ የተመሠከረበት አደባባይ መሰንበቻዉንም ዝግ ነዉ። በእሾሐማ ሾቦ ታጥሯል።አሸዋ የተሞሉ የላስቲክ ከረጢቶች ተደርድረዉበታል።ድንኳኖች፥ ነጫጭ ድንኳኖች ተተክለዉበታል።
ተሕሪር፥ ነፃነት አደባባይ፥ የሕዝባዊ አመፅ አብነት።ሠሞኑን ዳግም በሕዝባዊ አመፁ ተምሳሌት «ያሸበረቀበት»፥ በግጭት የተተራመሰበት ሠበብ ምክንያት ሁለት ነዉ።የሕዝባዊዉ ቀጣ ሁለተኛ ዓመት ዝክር-አንድ፥የፕሬዝዳት መሐመድ ሙርሲን አስተዳደርን መቃወም-ሁለት።
የሐያ-ስድስት ዓመቱ ወጣት ኢብራሒም ከንደሪያን ከአሌሳንደሪያ ካይሮ-የገባዉ ተሕሪር በሕዝባዊዉ ቁጣ መንተክተክ በመጀመረ- በሳልስቱ ነበር።ጥር-ሃያ ሥምንት ሁለት ሺሕ አሥራ-አንድ እንደ ጎሮጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር።ከያኔ-እስካሁን ከተሕሪር አደባባይ አልተለየም።ያኔ-በተቃዉሞ ሠልፈኛዉ ላይ የተፈፀመዉን ግፍ የዛሬ ከሚሆነዉ እኩል ያስታዉሰዋል፥-ወጣቱ።
«ፖሊሶቹ ማድረግ የሚችሉትን ሁሉ በሕዝቡ ላይ አድርገዋል።የፕላስቲክ ጥይት ተኩሰዋል።አሠለቃሽ ጢስ ረጭተዋል።ገዳይ ጥይት ተኩሰዋል።ሌላዉ ቀርቶ መኪኖቻቸዉን በሰልፈኛዉ ላይ ነድተዋል።»
ወጣቱ እያየ ሁለት ሠልፈኞች በፖሊስ መኪኖች ተደፈለቁ።በመቶ የሚቆጠሩ የእድሜ አቾቹ ተገደሉ።ሕዝባዊ ቁጣዉ ግን ናረ-እንጂ አልረገበም።አምባገነኑ ሥርዓት ተገረሠሠ-እንጂ አልቀጠለም።የካቲት አሥራ-አንድ።የሙባረክ ሥርዓት ፍፃሜ ታወጀ።ታላቅ ሕዝባዊ ድል።
#ሙባረክን የተኩት ወታደራዊ ጄኔራሎች ድሉን ከሕዝቡ እንዳይነጥቁ፥ ሕዝባዊ አብዮቱን ለራሳቸዉ ጥቅም እንዳያዉሉት ለመከላከል አብዮተኛዉ ለሌላ፥ ሠልፍ፥ ለሌላ ትግል መታደም፥ ሌላ መስዋዕትነት መክፈል ግድ ነበረበት።እነ ኢብራሒም አዲሱን አገዛዝ-ባዲስ እልሕ ሲጋፈጡ ሌሎች ብዙ መቶ አጋሮቻቸዉን አጡ።እሱ አልሞትም። ከሞት በመለስ ያለዉን ግፍ ግን ቀመሳት።ተሕሪር አደባባይ ተያዘ። እስር ቤት ተወረወረ።
«ደበደቡን፥ በጣም ደበደቡን።ክንዴን ሠበሩት።አቅሌን እስክስት ድረስ ገረፉኝ።ሌሎቹ መጡና ዳግም እንደምደበደብ ምናልባትም እንደምገደል ሲዝቱብኝ አቅሌን ገዛሁ።»
ሕዝባዊዉ አብዮት ግን ማርሻል ተንታዊንም ከቋመጡለት ወንበር አሽቀነጠራቸዉ።መርጫ መደረጉ፥ ተንታዊ የመሯቸዉ ጄኔራሎች ከሥልጣን መወገዳቸዉ በርግጥ ታላቅ ለዉጥ፥ ዳግማዊ ታላቅ ድልም ነዉ።በምርጫ ሥልጣን የያዙት ፕሬዝዳት መሐመድ ሙርሲና የቀድሞ ፓርቲያቸዉ ሙስሊም ወንድማማቾች ግን ለአብዮተኛዉ ጥያቄ ተገቢዉን መልስ አልሰጡም።እንዲያዉም ኢብራሒም እንደሚለዉ ሸሪዓ-ቀመስ ሕገ-መንግሥት አስፀድቀዉ ሕዝቡን ከፋፍለዉታል።የችግረኛዉን ሕዝብ ኑሮም ይበልጥ አክፍተዉበታል።
«ምንም የለወጡት ነገር የለም።ማንንም አይሰሙም።ሰዎች እየተቸገሩ፥ እየሞቱም ነዉ።ሰዉ መብላትና መኖር ይፈልጋል።»
አንድ-ተስፋ ግን አለዉ-ኢብራሒም።የሕዝቡ ችግር እየበረታ፥ እየጠከረ ሲሔድ፥ ብሶት በሚወልደዉ ምሬት-ሙስሊም ወንድማማቾችን ልክ-እንደ ሙባረክ ሁሉ ከፋችሁኝ-ከረፋችሁን፥ በቃችሁኝ ይላል የሚል-የእምነት ያክል የጠነከረ-ተስፋ።
«ጥሩዉ ነገር (,ሙስሊም ወንድማማቾ) እራሳቸዉ ወደ ዉድቀት መጓዛቸዉ ነዉ።ሙባራክ በራሳቸዉ ጥፋት እንደጠፉ ሁሉ እነዚሕም የሚወድቁበትን ጥፋት-እየፈፀሙ ነዉ።ይሕ አወንታዊ ነዉ።እንደሚመስለኝ አሁን አብዮቱን የሚመራ (ሐይል) የሚፈለግበት ወቅት ነዉ።»
አብዮቱ መሪ-ማግኘት ማጣቱ ላሁኑ አለየም።የሙርሲን አስተዳደር ከመቃወም ጋር የታላቁን ቁጣ-ሁለተኛ ዓመት ለመዘከር ተሕሪር አደባባይ የተሰለፈዉ ሕዝብ ግን ዘንድሮም፥ ለዉጥ እየጠየቀ፥ ከፀጥታ አስከባሪዎች ጋር እየተጋጨም ነዉ።
ነጋሽ መሐመድ
ሸዋዬ ለገሠ