1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጁልየስ ኔሬሬ የታንዛንያ አባት

ረቡዕ፣ ጥር 30 2010

በአፍሪቃ የነጻነት ትግል ውስጥ ስማቸው ከሚነሳ ጥቂቶች መካከል ጁልየስ ካምባራጅ ኔሬሬ አንዱ ናቸው፤ በቀድሞ መጠሪያዋ የታንጋኒካ የአሁኗ የታንዛንያ የመጀመሪያው ፕሬዝዳንት።

https://p.dw.com/p/2r8yj
Julius Nyerere, 1. Präsident Tansanias, Porträt
ምስል Comic Republic

የታንዛንያ አባት

በአፍሪቃ የነጻነት ትግል ውስጥ ስማቸው ከሚነሳ ጥቂቶች መካከል ጁልየስ ካምባራጅ ኔሬሬ አንዱ ናቸው፤ በቀድሞ መጠሪያዋ የታንጋኒካ የአሁኗ የታንዛንያ የመጀመሪያው ፕሬዝዳንት ኔሬሬ በጎርጎሮሳዊው 1961 ዓም ከብሪታንያ ቅኝ አገዛዝ ነጻ የወጣችውን ታንጋኒካን እንዲሁም ከሦስት ዓመት በኋላ ታንጋኒካ እና ዛንዚባር ተዋህደው የመሰረቷትን ታንዛንያን በአጠቃላይ ለ23 ዓመታት መርተዋል። በሥልጣን ዘመናቸው ያራመዱት ሶሻሊስታዊ መርህ ከሀገሪቱ ኤኮኖሚ አመዛኙን ማድቀቁ ቢነገርም አሁንም በታንዛንያ ብሔራዊ ጀግና ተብለው ይወዳሳሉ። ጀምስ ማሀንዶ ያዘጋጀውን ኂሩት መለሰ አጠናቅራዋለች።

በያኔው የብሪታንያዋ ቅኝ ግዛት ታንጋኒካ ውስጥ በምትገኘው ቡትያማ በተሰኘችው መንደር በጎርጎሮሳዊው 1922 አንድ ህጻን ልጅ ወደዚህች ዓለም መጣ። 
በዝናባማ ቀን የተወለደው ይህ ህጻን ዛናኪ የተባለው ህዝብ መሪ ልጅ ነበር። በእንስቷ የዝናብ መንፈስ መጠሪያ ካምባራጅ ተባለ። የሀገሪቱን ህዝብ ራዕይ ያነገበው ተስፋም የሰነቀው የካምባራጅ ስም በመላ ሀገሪቱ ገነነ ፤በአፍሪቃም ተጽእኖ ማድረግ ያዘ። ወጣቱ ካምባራጅ ወይም ጁልየስ ኔሬሬ ጎበዝ ተማሪ ነበር። በዚህ የተፈጥሮ ስጦታው ከመንግሥት ባገኘው የነጻ ትምሕርት እድል ጥሩ ውጤት ያላቸው ተማሪዎች በሚማሩበት ትምህርት ቤት የሁለተኛ ደረጃ ትምሕርቱን አጠናቀቀ። ከዚያም በዩጋንዳ ዋና ከተማ ካምፓላ በሚገኘው የማካራሬ ኮሌጅ ከፍተኛ ትምሕርቱን ተከታትሎ ወደ ሐገሩ ከተመለሰ በኋላ በመምህርነት ለዓመትት አገልግሏል። ኔሬሬ በአዛውንት እድሜያቸው ጭምር በኪስዋሂሊ «ምዋሊሙ» ማለትም መምህር የክብር መጠሪያቸው ነበር። በ1949 የነጻ ትምሕርት እድል አግኝተው በሄዱበት በስኮትላንዱ የኤደንብራህ ዩኒቨርስቲ በምጣኔ ሀብት እና በታሪክ ትምሕርት ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ይዘው ወደ ሀገራቸው ከተመለሱም በኋላም በመምህርነቱ ቢቀጥሉም ብዙ አልገፉበትም። ኔሬሬ ይበልጡን ወደ ፖለቲካው ተስበው ደም ባልፈሰሰበት ትግል ታንጋኒካ ነጻነትዋን እንድትጎናጸፍ አበቁ። በጎርጎሮሳው ታህሳስ 1961 ከብሪታንያ ቅኝ አገዛዝ ነጻ የወጣችው ታንጋኒካ የመጀመሪያው ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኑ ። ከአንድ ዓመት በኋላም በፕሬዝዳንትነት ተመረጡ። ያኔ ስለ ታንጋኒካ የወደፊት እቅድ ሲጠየቁ ይህን መወሰን የኔ ድርሻ አይደለም ሲሉ ነበር የመለሱት። « ማለት ያለብኝ እኔ አላቅድም፤እኔ እንደማስበው የሚታቀደው በራሱ በታንጋኒካ ህዝብ ነው።»
ኔሬሬ በጎርጎሮሳዊው 1964 ታንዛንያን ለመመሥረት ያበቃው የዛንዚባር ደሴቶች እና የታናጋኒካ ውህደት ዋነኛው ተዋናይ ነበሩ። ውህደቱ እውን እንደሆነም የታንዛኒያ ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ።
ሥልጣን ግን ኔሬሬን አልቀየራቸውም። እንደቀድሞው ለታገሉለት እና ቆርጠው ለተነሱበት ለሀገራቸው ደህንነት መሥራት ቀጠሉ። በታንዛንያ ዋና ከተማ ዳሬሰላም በሚገኘው የኔሬሬ ቤተ መዘክር ረዳት ሃላፊ ቪክቶሪያ ባቼ ኔሬሬ ከህዝቡ አጠገብ ያልተለዩ መሪ እንደነበሩ ይመሰክራሉ። «ህዝብ ይወዳሉ። አያገሉም። እንደማንኛውም ተራ ሰው ነው የኖሩት። ዶማ ይዘው ፣ ከሌሎች ጋር በሀገር ግንባታ ሲሳቱፉ የሚታዩባቸው ፎቶግራፎች አሉ።»
ኔሬሬ ለብሔራዊ አንድነት ግንባታ ይረዳ ዘንድ ከእንግሊዘኛ ይልቅ ኪስዋሂሊ ብሔራዊ ቋንቋ እንዲሆን ያበረታቱ ነበር። ሆኖም ምናልባትም ከሁሉም በላይ የኔሬሬ መታወሻ ኡጃማ የተባለው የህብረት እርሻን መሠረት ያደረገው የአፍሪቃ ሶሻሊዝም መርሃቸው ነው። ኡጃማ የኪስዋሂሊ ቃል ሲሆን ትርጉሙ ቤተሰባዊነት ማለት ነው። ኡጃማ ሰዎች በሰፈራ መንደሮች እንዲሰባሰቡ በህብረት እርሻም እንዲሰማሩ የሚያደርግ አሠራር ነበር። ይህ መርህ ከፍተኛ ተቃውሞ ሲገጥመው ኔሬሬ ህዝቡ ካለፈቃዱ ወደ ሌላ አካባቢ እንዲዛወር እና በህብረት እንዲሰራ አስገደዱ።ከቻይናው ማኦ ሴቱንግ ጋር የጠበቀ ግንኙነት የነበራቸው የኔሬሬ ታንዛንያ በ1980 ዎቹ የእርሻ ምርቷ አሽቆለቆለ። የታንዛንያን ኤኮኖሚ ማሳደጉ ያልተሳካለት ኡጃማ ለሀገሪቱ እንደማይሰራ ግልጽ ሆነ። 
ያም ሆኖ ኔሬሬ በሙስናም ይሁን በሌሎች የግል ቅሌቶች ሳይነካኩ እስከ መጨረሻው የዘለቁ መሪ እንደነበሩ የታሪክ ምሁሩ ሰይድ ሞሐመድ ያስረዳሉ። «አንድ ነገር እነግራችኋለሁ። በጥናቴ ላይ የጠየቅኩዋቸው ሁሉ የሚናገሩት ሙዋሊሙ ልዩ መሆናቸውን ነው። ሙሰኛ ያልሆኑ ለገንዘብ እና ሀብት ደንታ የሌላቸው ሰው እንደነበሩ።»
የታንዛንያ አባት የሚባሉት ኔሬሬ በጎርጎሮሳዊው 1985 ነበር በገዛ ፈቃዳቸው ሥልጣናቸውን የለቀቁት። ሀገራቸውን ከዓለማችን ድሆች ተርታ በማሰለፍ፣ከልማት ወደ ኋላ በማስቀረት እና የውጭ እርዳታ ጥገኛ በማድረግ የሚወቀሱት ኔሬሬ ከሥልጣን ሲወርዱ ሲከተሉት ለቆዩት የኤኮኖሚ መርህ በይፋ ይቅርታ ጠይቀዋል። ይሁን እና በኔሬሬ ዘመነ ሥልጣን በታንዛንያ የህጻናት ሞት መቀነሱን የሆስፒታሎች ቁጥር መጨመሩን እና ትምህርት መስፋፋቱን እርሳቸውን የተኩት አሊ ሀሰን ምዉኒ መስክረውላቸዋል። ኔሬሬ በ1999 ዓም ከዚህ ዓለም በሞት ቢለዩም በማያጠያይቅ ጽናታቸው ሁሌም በክብር ይታወሳሉ።
ጀምስ ማሀንዶ /ኂሩት መለሰ

Julius Nyerere, 1. Präsident Tansanias feiert Unabhängigkeit seines Landes
ምስል Comic Republic
DW Videostill Projekt African Roots | Julius Nyerere, Tansania
ምስል Comic Republic

ነጋሽ መሀመድ

 ይህ ዘገባ አፍሪካዊ ሥረ-መሠረት በሚል ከጌርዳ ሔንክል ተቋም ጋር በመተባበር የሚቀርብ ልዩ ዝግጅት አንድ አካል ነው።

 This report is part of African Roots, a project realized in cooperation with the Gerda Henkel foundation.