ጀርመን ኤቦላን አስመልክቶ ያደረገችው ጥሪ
ማክሰኞ፣ መስከረም 13 2007ጀርመን የኤቦላን ተህዋሲ ለማስቆም እስካሁን 17 ሚሊዮን ዮሮ ረድታለች። ነገር ግን እንደ ሰደድ እሳት የሚዛመተውን ተህዋሲ ለመዋጋት ገንዘብ ብቻ በቂ እንዳልሆነ ግልፅ ነው። ታድያ የጀርመንመከላከያሚኒስትርኦዙላፎንዴርላይን ሰኞ ጠዋት የኤቦላ በሽታ ወደ ተከሰተባቸው አካባቢዎች መዝመት የሚሹ የጀርመን ጦር ባልደረባዎች በፍቃደኝነትመመዝገብእንደሚችሉ ሲያስታውቁ፤ ወታደር በፍቃደኝነት የሚዘምትበት ተግባር ግራ ያጋባቸው አልጠፉም። ለዛውም ሚኒስትሯ ወታደራቸውን ለማግባባት አንዳንድ ያመቻቹትን ቅድመ ሁኔታዎች ዘርዝረው ነው።
« በመጀመሪያ በስፍራው ምን እንደሚጠብቃቸው እና ምን አይነት የጤና ዋስትና እንደሚያገኙ መረጃ ያስፈልጋቸዋል፣ 2ኛ አጭር ስልጠና ያገኛሉ። በስፍራው የሚገኙ በርካታ ሀኪሞች እና የህክምና ባለሙያዎች የሚያውቁትን ስልጠና ይሰጣቸዋል።3ኛ ደግሞ በስፍራው አንድ ነገር ቢያጋጥማቸው ወደ ጀርመን ተመልሰው ክትትል እንደሚደረግላቸው ማወቅ ያስፈልጋቸዋል።»
እንዲያም ሆኖ ከጀርመን ወታደሮች በፍቃደኝነት መዝመት የሚፈልግ ከጠፋስ? በሙያቸው ሀኪም የሆኑት የጀርመን የመከላከያ ሚኒስትር፤ አደጋም ሆነ በበሽታው መያዝ ቢገጥማቸው ወዲያው ወደ ጀርመን የሚላኩ እና የሚታከሙ ከሆነ በፍቃደኝነት መሄድ የሚለውን ጥያቄ በአዎንታ ይመልሳሉ።ለጀርመን ጦር ወታደሮችም ይሁኑ ሲቪል ማህበረሰቡ የክፉ ቀን ቢመጣ እና በትዋህሲው ቢያዙ እንዴት ይሆን ይህን ሚኒስትሯ ዕውን ሊያደርጉ ያሰቡት።« በአሁኑ ሰዓት ለዚህ ለየት ያለ ተልዕኮ በዓለም ያልታየና እስከዛሬ ያልነበረንን ልዩ አዉሮፕላኖችና ሄሌኮፕተሮችን እያዘጋጀን ነዉ።ለዚህ ዝግጅት ደግሞ አራት ሳምንታት ያስፈልገናል።»
ከዚህም ሌላ በዚህ አራት ሳምንታት ውስጥ ጊዜያዊ ሀኪም ቤት በአካባቢው እንደሚሰራ እና በቂ የህክምና ባለሙያዎች ለማሰባሰብ እንደሚያስፈልግ ሚኒስትሯ አስረድተዋል። ለታቀደው ድጋፍ ጀርመን ምን ያህል ሰዎች ያስፈልጓት ይሆን? ሚኒስትር ፎን ዴር ላይን፤« ይህን ጥሪ ለጀርመን ጦር ካደረኩ በኋላ በሚቀጥሉት ቀናት የምናየው ይሆናል። ለግንዛቤ ያህል ለ50 የሀኪም ቤት አልጋዎች ወደ 100 የሚሆኑ የህክምና ባለሙያዎች ያስፈልጋሉ። በሽታው ወደ ሌላ እንዳይተላለፍ በሚደረገው ልብስ ውስጥ አንድ ሰው ከ አራት እስከ ለአምስት ሰዓት ያህል ነው ልቆይ የሚችለው። ከዛ ዕረፍት መውሰድ ይኖርበታል።በሌላ በኩል አንድ ክፍል ውስጥ የሚገቡ እና ተባብረው የሚሰሩ ሁለት ሰዎች ያስፈልጋሉ። በዚህ አጭር መግለጫ ነገሩ ምን ያህል ውስብስብ እንደሆነ መረዳት ይቻላል።»
በርግጥ ጉዳዩ ውስብስብ ሆኖ ይሆናል የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እስካሁን ጠንካራ ርምጃ ያልወሰደው፤ መፍትሄ ያሹት የላይቤሪያን ፕሬዚዳንት ኤለን ጆንሰን ሰርሌፍ ለጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል የርዳታ ጥያቄ የያዘ ደብዳቤ እስከመላክ ያደረሰው። የጀርመን ፌደራሊያዊ መንግሥት ባለስልጣን ሲወያዩ ቢቆዩም፤ ከፍቃደኛ ዘማቾች ጥያቄ ውጪ ሌላ መፍትሄ ያላቸውን ነገሮችን ይዞ አሁን መጥቷል። ከዮናይትድ ስቴትስ እና ፈረንሳይ ጋር በመተባበር ሴኔጋል ላይ በሚመሰርተው ጊዜያዊ ጣቢያ አማካይነት ርዳታው ይላካል።«ምግብ ፣ መድሀኒት እና ሌሎች የርዳታ ቁሳቁሶችን በሳምንት ውስጥ እስከ 100 ቶን ያህል ማመላለስ እንችላለን። ከሚቀጥለው ሳምንት መጨረሻ ጀምሮ ከአጋሮቻችን ጋር ዝግጁ ነን።
ልደት አበበ
አርያም ተክሌ