1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኬንያው ናይላብ እና ወጣት የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 19 2009

ናይሮቢ ኢንኩቤሽን ላብ ወይም ናይላብ የተሰኘው የኬንያው የሶፍትዌር ዝግጅት ማዕከል የተመሰረተው በጎርጎሮሳዊው 2010 ዓ.ም ነው። ማዕከሉ ከፍተኛ ማሕበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው የቴክኖሎጂ የፈጠራ ሥራዎችን ይደግፋል። የኬንያ የሶፍትዌር አዘጋጆች ለእለት ተለት ሕይወት ጠቀሜታ ያላቸው የፈጠራ ሥራዎቻቸውን በዚህ ማዕከል ያሻሽላሉ።

https://p.dw.com/p/2Uylh
Kenia Bloggers Association of Kenya
ምስል DW/J. Mielke

(AoM) Incubating startups in Kenya - MP3-Stereo

ስቲቭ ዋሊ ደስተኛ ሰው ነው። በናይሮቢ በተመጣጣኝ ዋጋ የመኖሪያ ቤት አግኝቷል። ይኽ ብቻ አይደለም። ለደላላ ሊከፍል የነበረውን ገንዘብ ማስቀረት ችሏል። ይክ ሁሉ  የሆነው ኬጃኸንት በተሰኘ አነስተኛ የሞባይል ማቀናበሪያ አማካኝነት ነው። ማቀናበሪያውን ከግል መጥፎ ገጠመኞቹ በኋላ የፈበረከው ጆሽዋ ሙታዋ ነው። 

«አነስተኛ እና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች የመኖሪያ ቤት የሚያገኙበት የተሻለ መንገድ ሊኖር ይገባል ብለን ተገነዘብን። ምክንያቱም በተለይ በናይሮቢ በርካታ አጭበርባሪ ደላሎች አሉ። ስለዚህ ሒደቱን የበለጠ ግልፅ ለማድረግ ወሰንን።»

የጆሽዋ ማቀናበሪያ የተሰናዳው  ለአዳዲስ ሥራ ፈጣሪዎች በሳም ጊቹሩ አማካኝነት በጎርጎሮሳዊው 2010 ዓ.ም. በተቋቋመው ናይላብ ውስጥ ነው። ጊቹሩ ምርጥ ኃሳብ ግን ደግሞ ጥቂት ገንዘብ ያላቸው የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል ብሎ ያምናል። 
 «ናይላብን የመሰረትንው ወጣቶች ተገልለው እየሰሩ መሆናቸውን በመታዘባችን ነው። ስለዚህ መጥተው በጋራ የሚሰሩበት፤በትብብር የሚፈጥሩበት እና በተናጠል የማያገኟቸውን ቁሳቁሶች የሚገለገሉበት ማዕከል አቋቋምን።»

ናይላብ በስድስት ወራት ውስጥ ሰዎች ኃሳባቸውን ወዳለቀለት ምርት እንዲቀይሩ ያግዛል። የመጀመሪው ትኩረት ኃሳቡ እንዴት በቴክኖሎጂ ተግባራዊ ይሆናል የሚለው ነው። ከዚያ የቡድኑ አባላት ያንን ምርት እንዴት ማስተዋወቅ እና መሸጥ ይቻላል በሚለው ላይ ትኩረታቸውን ያደርጋሉ። ያ ምርት አንዴ ለገበያ ከቀረበ ናይላብ ከትርፉ አስር በመቶ ድርሻ ይኖረዋል። 
«አንደኛው የገጠመን ፈተና የገንዘብ አቅማችንን ማሳደግ አለመቻላችን ነው። የእኛ እቅድ ሞምባሳ፤ኪሱሙ እና ኤልዶሬትን ወደመሳሰሉ መስፋፋት ነው። ለዚህ ደግሞ ወደ 5,000 ዶላር ገደማ ቢያስፈልገንም ያን ያክል ገንዘብ እስካሁን መሰብሰብ አልቻልንም።»  

ኬንያውያን አሁን አሁን በሥራ ቦታም ይሁን በመኖሪያ ቤታቸው ቅንጡ የእጅ ሥልኮችን አብዝተው መጠቀም ይዘዋል። ከ43 ሚሊዮን ኬንያውያን መካከል ቢያንስ 30 በመቶው የቅንጡ የእጅ ሥልኮች ተጠቃሚ ሆነዋል። በባንክ አገልግሎት ፤ አዲስ የፍቅር ጓደኛ ለመተዋወቅ እና ግብይት ለመፈጸም በመሰሉ ግልጋሎቶች ውስጥ የቅንጡ ስልኮች ማስተናበሪያዎች ከፍተኛ የገበያ እምቅ አቅም አላቸው። «የአዳዲስ ኩባንያ መስራቾች ብዙ ጊዜ በንግዱ ላይ ትኩረት አያደርጉም። ብዙዎቻችን ጥሩ አፕልኬሽኖች እናዘጋጃለን። ይሁንና ወደ ገንዘብ አንቀይረውም። ምርጥ ማስተናበሪያ ወይም አፕልኬሽን ያን ችግር ይፈታል ብለን እናምናለን።»
ምርጥ ማስተናበሪያ ወይም አፕልኬሽን ማዘጋጀት ግን ብቻውን በቂ አይደለም። የኬንያ መንግሥት ለጀማሪ ኩባንያዎች ድጋፍ የሚያደርጉ 30 ማዕከላትን በመገባደድ ላይ በሚገኘው የጎርጎሮሳዊው 2016 ዓ.ም. ለማዘጋጀት 1.6 ሚሊዮን ዶላር መድቦ ነበር። ጀማሪ ኩባንያዎቹ ከሚያገኙት ድጋፍ እና ስልጠና ባሻገር ወደ 3,288 ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ይሰጣቸዋል። 
«የገንዘብ ድጋፍ የማግኘት እድል ሊኖር ይገባል።  በዩናይትድ ስቴትስ ቢሆን ኖሮ ገንዘብ ለማሰባሰብ ቀላል በሆነ ነበር። ነገር ግን በኬንያ ሰዎች ጀማሪ ኩባንያዎችን ከሚያግዙ ይልቅ በቤት ግንባታ ላይ መዋዕለ-ንዋያቸውን ቢያፈሱ ይመርጣሉ።» አሁንም ቢሆን ጥሩ የፈጠራ ኃሳብን ምንም አይገታውም። ናይላብ አሁንም የጀማሪ ኩባንያዎችን ሥኬት በማፋጠን የቴክኖሎጂ አብዮቱን በቀዳሚነት የመምራት እቅድ አለው። በጊዜው ወዳለበትገንዘብ ገበያ  ይመጣል። 

ማይና ማቻሪያ/ እሸቴ በቀለ
አዜብ ታደሰ