1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዶናልድ ትራምፕ "ስለሚያወሩት ነገር አያውቁም" የቀድሞው ጠቅላይ ምኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 14 2013

የጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጽህፈት ቤት ዛሬ ቅዳሜ ይፋ ያደረገው መግለጫ "ኢትዮጵያ ፍትኃዊ ላልሆነ ሥምምነት እጅ እንድትሰጥ የሚገፋፉ ጠበኛ ማስፈራሪያዎች ያዘሉ አልፎ አልፎ የሚወጡ መግለጫዎች አሁንም ብዙ ናቸው" ብሏል።  

https://p.dw.com/p/3kNh6
Äthiopien Grand-Ethiopian-Renaissance-Talsperre
ምስል AFP/Maxar Tech

ኢትዮጵያ በማስፈራሪያ በታላቁ የኅዳሴ ግድብ ጉዳይ ከሱዳን እና ከግብጽ የገባችበትን ልዩነት ለመፍታት መሞከር "የተሳሳተ፣ ፍሬ አልባ እና ዓለም አቀፍ ሕግጋትን በግልፅ የሚጥስ" እንደሆነ አስታወቀች።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ግብጽ "ግድቡን ታፈነዳለች" ካሉ በኋላ የጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ ኢትዮጵያ ወደ ጠብ ጫሪነት እንደማትገባ ነገር ግን በቅኝ ግዛት ዘመን የተፈረሙ ሥምምነቶች ላይ መሠረት ያደረገ መብትም እንደማትቀበል አስታውቋል።

የጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ የአሜሪካውን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕም ሆነ የትኛውንም አገር ስም አልጠቀሰም።

"ኢትዮጵያ ፍትኃዊ ላልሆነ ሥምምነት እጅ እንድትሰጥ የሚገፋፉ ጠበኛ ማስፈራሪያዎች ያዘሉ አልፎ አልፎ የሚወጡ መግለጫዎች አሁንም ብዙ ናቸው" ያለው የጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጽህፈት ቤት "በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ላይ የሚሰነዘሩ እነዚህ ማስፈራሪያዎች የተሳሳቱ፣ ፍሬ አልባ እና ዓለም አቀፍ ሕግጋትን በግልጽ የሚጥሱ ናቸው" በማለት ነቅፏል።   

"ኢትዮጵያ ወደ ጠብ ጫሪነት አትገባም" ያለው ይኸው መግለጫ እንዳለው አገሪቱ "ሙሉ በሙሉ በቅኝ ግዛት ሥምምነቶች ላይ የተመሠረተ መብት አትቀበልም።"

መግለጫው የወጣው የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ግድቡን በተመለከተ አስተያየት ከሰጡ በኋላ ነው። ዶናልድ ትራምፕ ግብጾች "ግድቡን ያፈርሱታል” የሚል አስተያየት ከጽህፈት ቤታቸው የሰጡት ከሱዳኑ ጠቅላይ ምኒስትር ዐብደላ ሐምዶክ እና ከእስራኤሉ ጠቅላይ ምኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ትናንት በስልክ በተነጋገሩበት ወቅት ነበር።

የፕሬዝዳንቱ አስተያየት በርካታ ኢትዮጵያውያንን አስቆጥቷል። የቀድሞው ጠቅላይ ምኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የዶናልድ ትራምፕን አስተያየት "ግድየለሽ" ብለውታል። ኃይለማርያም "ስለሚያወሩት ነገር አያውቁም። ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን በእንዲህ አይነት ኃላፊነት የጎደለው አስተያየት ሥጋት አይገባቸውም" ሲሉ ትራምፕን ነቅፈዋል።

የምጣኔ ሐብት ባለሙያ እና ባለወረቱ ዘመዴነህ ንጋቱ በበኩላቸው ዶናልድ ትራምፕ በጉዳዩ "ገለልተኛ ሆነው በቆዩ ነበር" የሚል አስተያየት በግል የትዊተር ገፃቸው አስፍረዋል።

የአሜሪካ ኮንግረስ አባል የሆኑት ጃሰን ክሮው ፕሬዝዳንቱ "መረጃ ሳይኖራቸው" ስለ ታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ የሰጡት አስተያየት "ግድየለሽ" ብለውታል። ኢትዮጵያ የአሜሪካ የረዥም ጊዜ አጋር መሆኗን ያስታወሱት ክሮው "ዘላቂ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሔ" ለማበጀት አሜሪካ "ሐቀኛ አሸማጋይ" እንድትሆን እና "ትርጉም አልባ" ያሉትን የእርዳታ ዕቀባም እንድታቆም አሳስበዋል።

እሸቴ በቀለ