1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ድብቁ የኢንተርኔት ዓለም

Mantegaftot Sileshiረቡዕ፣ ሐምሌ 20 2008

ሰሞኑን በጀርመን ሀገር የሙኒክ ከተማ አንድ የጀርመን እና የኢራን ዜግነት ያለው ወጣት ግድያ የፈጸመበትን ሽጉጥ የገዛው ከድብቅ የኢንተርኔት ዓለም ዳርክ ኔት ውስጥ ነው። ድብቅ የኢንተርኔት ዓለም ሕገ-ወጥ አጥፊ ለሆኑ ነገሮች የመዋሉን ያኽል በጨቋኝ መንግስታት ድምጻቸው ለሚታፈንባቸውም ዜጎች አቋራጭ የመገናኛ መንገድ በማሳየትም አገልግሎት ይሰጣል።

https://p.dw.com/p/1JWIK
Symbolbild Datenschutz
ምስል picture-alliance/dpa

ድብቁ የኢንተርኔት ዓለም

ሐምሌ 16 ቀን፣ 2008 ዓም፤ ዴቪድ ዓሊ ሶምቦሊ በጀርመኗ የሙኒክ ከተማ ውስጥ ዘጠኝ ሰዎችን ተኩሶ በመግደል በመጨረሻ እራሱን አጠፋ። የሰሞኑ አቢይ ዜና። ጦር መሣሪያ ዝውውር ጥብቅ በሆነባት ጀርመን የ18 ዓመቱ ጀርመናዊ ኢራናዊ ወጣት ነፍሰ-ገዳይ ሽጉጡን ከወዴት አገኘው? ፖሊስ ምርመራውን በየአቅጣጫው እያጣደፈ መሆኑን አስታወቀ። አፍታም ሳይቆይ ለግድያ የተጠቀመበትን ሽጉጥ የገዛው ሕገ-ወጥ ጦር መሣሪያ በድብቅ ከሚሸጥበት ድብቅ የኢንተርኔት ዓለም (darknet) ገበያ መሆኑን ደረስኩበት አለ። ለመሆኑ ዳርክ ኔት ምንድን ነው? የኢንተርኔት ድብቅ ዓለም (deep web) መድረክስ?

መደበኛው የኢንተርኔት ዓለም ግንኙነት እምብዛም ዙራዙር የሌለው ቀጥተኛ ነው። መሠረታዊ በሆነው የኢንተርኔት የግንኙነት ሒደት አንድ መልእክት ወደ ተቀባዩ ሲላክ ላኪውም ተቀባዩም፣ አስፈላጊ ከሆነም ሦስተኛ ወገን መልእክቱን ሊመለከቱ ይችላሉ። አንዳንድ ጊዜ ግን በተለያዩ ምክንያቶች ላኪ እና ተቀባይ ሳይተያዩ መልእክቱ ላይም ሦስተኛ ወገን ሳያጮልቅ መልእክታቸውን መላላክ የሚሹበት አጋጣሚ ይኖራል። አጋጣሚው ቀናም መጥፎም ሊሆን ይችላል። የሙኒኩ ገዳይ ጥቃት የፈጸመበትን ሽጉጥ የገዛበት ዳርክኔት የተሰኘው የኢንተርኔት ድብቅ ዓለም የመገበያያ መድረክ ምን እንደሆነ በዘርፉ ጥናት ያከናወነው የብሪታንያው ጋዜጠኛ ጂሚ ባርትሌት ያብራራል።

«ዳርክኔት ገበያ ማንነት የማይገለጥበት የመገበያያ መድረክ ነው። ቶር የተሰኘውን ድርዓለማቀፍ ማሰሻ በመጠቀም ግብይቱን የሚያከናውኑ በሺህዎች የሚቆጠሩ ገበያዎች አሉ። በመድረኩ ማንኛውንም ነገር ይገዛሉ፤ ይሸጣሉ። ልክ እንደ አማዞን አለያም ኢቤይ የኢንተርኔት ገበያዎች አይነት ናቸው። እጅግ ተፎካካሪ እና በስፋት የሚንቀሳቀሱ የኢንተርኔት ንግድ የሚከወንባቸው ገበያዎች ናቸው። ከእነዚህ ገበያዎች በየዓመቱ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩት አደንዛዥ ዕጽ ይገበያዩበታል። አልፎ አልፎ ደግሞ ጦር መሣሪያዎች ግዢ እና ሽያችም ይፈጸምባቸዋል። ምን ያህል ስለመሆናቸው ዱካቸውን ለመከተል እጅግ ያዳግታሉ»

በመደበኛው የኢንተርኔት አለያም በዕውኑ ዓለም በቀላሉ የማይገኙ ነገሮችን ለመግዛት ሰዎች ቢትኮይን የተሰኘውን ድብቅ የሒሳብ መክፈያ በመጠቀም ወደነዚህ ድብቅ የግብይት መድረኮች ብቅ ይላሉ። እናም ግዢ እና ሽያጮቹ የሚከወኑት ልክ እንደ አማዞን እና ኢቤይ ነው። ልዩነቱ በድብቅ የኢንተርኔት ዓለም የገበያተኞች አድራሻ እና ማንነት የማይታወቅ መሆኑ ነው።

በእርግጥ ይላል ብሪታንያዊው ጋዜጠኛ፦ እነዚህ በድብቅ የኢንተርኔት ግንኙነት የሚፈጸምባቸው መድረኮች ቀና የሆነ ውም ነገር አላቸው። ለአብነት ያኽል በጨቋኝ መንግሥታት ክትትል የሚደረግባቸው ግለሰቦች አለያም ሴንሰርሺፕ በሚፈጸምባቸው ሃገራት ሰዎች መልእክታቸውን ያለከልካይ ለማስተላለፍ ይጠቀሙበታል። እንዳልካቸው ኃይለሚካኤል አሜሪካን ሀገር በኦሬገን ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት እና ኮሙኒኬሽን የ3ኛ ዓመት ዶክትሬት ተማሪ ነው። ስለድብቅ የኢንተርኔት ዓለም ምንነት እንዲህ ያብራራል።

ከዞን ዘጠኝ መሥራቾች አንዱ የሆነው እንዳልካቸው ኃይለ ሚካኤል መደበኛው የኢንተርኔት ዓለምን በሰፊ አውራ ጎዳና ብንመስለው ድብቅ የኢንርኔት ዓለም የማይታወቁ አለያም የማይታዩ አቋራጮች ተደርገው ሊወሰዱ ይችላሉ ሲልም አክሏል። ወደ ድብቁ የኢንተርኔት ዓለም ሰዎች የሚገቡባቸውን ምክንያቶችም መጥፎም ቀናም እንደሆኑ ያብራራል።

በብዛት ዜና ላይ የምንሰማው ወንጀለኞች አለያም ሕግ መተላለፍ የሚፈልጉ ሰዎች ሲጠቀሙበት ስለሆነ ነው እንጂ፤ ከወንጀል ነጻ የሆኑ መልካም ነገሮችም በድብቁ የኢንተርኔት ዓለም ይከወናሉ ብሏል።

በድብቅ የኢንተርኔት ዓለም ውስጥ በጣም በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ገጾች እና ድረ-ገጽ ማሰሻዎች እንደሚገኙ ይጠቀሳል። ለአብነት ያህል ፍሪ ኔት፣ አይ ቱ ፒ፣ ጆን ዶ፣ እንዲሁም ቶር ይገኙበታል። ቶር የድረ-ገጽ ማሰሻ ምንድን ነው?

ቶር ድረ-ገጽ ማሰሻ (Tor) ኢንተርኔት ውስጥ ሲታይ በቁመት የተገመሰ የሽንኩርት ቅርጽ መልክ ነው ያለው። ይህ ድረ-ገጽ ማሰሻ የኢንተርኔት መጠቀሚያ አድራሻን (IP) ይሸሽጋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

Symbolbild Internet Hacker Sicherheit Computer www Passwort
ምስል Fotolia/Yong Hian Lim
Symbolbild Darknet
ምስል Fotolia/Amir Kaljikovic

አርያም ተክሌ