1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ድሬደዋ ነፃ የንግድ ቀጠና ሆነች

ሰኞ፣ ነሐሴ 9 2014

ነፃ የንግድ ቀጠናን መመስረት "ኢትዮጵያ ከተኛችባቸው ዘርፎች አንዱ» ያሉት ጠ/ሚ ዐቢይ በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ነበሩ ያሏቸው የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ ተሳታፊ እንዲሆኑ ጠይቀዋል። ዐቢይ በድሬደዋ ለመጀመሪያው ጊዜ ተግባራዊ የሆነው ነፃ የንግድ ቀጠና ውጤታማ ከሆነ በሌሎች አካባቢዎችም ተመሳሳይ ቀጠናዎች እንደሚከፈቱ ጠቁመዋል።

https://p.dw.com/p/4FYk0
Äthiopien | Eröffnung Freihandelszone in Dire Dawa
ምስል Mesay Tekelu/DW

ድሬደዋ ነፃ የንግድ ቀጠና ሆነች

ድሬደዋን ነፃ የንግድ ቀጠና የሚያደርገው አዲስ አሰራር በይፋ ተጀመረ። የአስራሩን መጀመር ይፋ ያደረጉትየኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ፣ነፃ የንግድ ቀጠና "ኢትዮጵያ ተጠቃሚ ሳትሆን ከተኛችባቸው ዘርፎች አንዱ" ሱሲሉ ገልጸውታል። በተጀመረው ነፃ የንግድ ቀጠናም በተለይ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ቀዳሚው ተጠቃሚ ለመሆን እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።
በሀገሪቱ የመጀመሪያ የሆነው የድሬደዋ ነፃ የንግድ ቀጠና ውጤታማ ከሆነ ተመሳሳይ ቀጠናዎች በሌሎች አካባቢዎች ይመሰረታሉ ተብሏል። ነፃ የንግድ ቀጠናን መመስረትን "ኢትዮጵያ ከተኛችባቸው ዘርፎች አንዱ" በሚል የጠቀሱት ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ቆይተዋል ያሏቸው የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች አሁን በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ ተሳታፊ እንዲሆኑ ጠይቀዋል።ጠቅላይ ሚንስትሩ በድሬደዋ ለመጀመሪያው ጊዜ ተግባራዊ በሆነው ነፃ የንግድ ቀጠና የሚወጡ ሕጎች ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚወጡ ሕጎች ቀለል ያሉ መሆናቸውን ገልፀው ፤ ውጤታማ ከሆነ በሌሎች አካባቢዎች ተመሳሳይ ቀጠናዎች እንደሚከፈቱ ጠቁመዋል።
የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚንስቴር ሚንስትር ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ በበኩላቸው የነፃ ንግድ ቀጠና መስፋፋት ሀገሪቱን ከተደጋጋሚ የሎጅስቲክስ ወጭዎች ማዳንን ጨምሮ በርካታ ጠቀሜታዎች እንዳሉት አብራርተዋል።የድሬደዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር የነፃ ንግድ ቀጠናው ሥራ መጀመር ለረጅም አመታት "በማንቀላፋት" ውስጥ ቆይታለች ላሏት ድሬደዋ፣ መነቃቃት የሚፈጥር መሆኑን ጠቅሰው ለውጤታማነቱ አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።ነፃ የንግድ ቀጠናውን በይፋ ለማስጀመር በድሬደዋ በተካሄደው መርሀ ግብር ላይ ጠቅላይ ሚንስትር አቢይ አህመድን ጨምሮ በርካታ እንግዶች ተገኝተዋል።

Äthiopien | Eröffnung Freihandelszone in Dire Dawa
ምስል Mesay Tekelu/DW

መሳይ ተክሉ

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ