ዳግም የጅምላ ጭፍጨፋ በቄሌም ወለጋ
ማክሰኞ፣ ሰኔ 28 2014በትናንትናው እለት በኦሮሚያ ክልል ቀለም ወለጋ ዞን ሃዋ ገላን ወረዳ ለምለም ቀበሌ በታጣቂዎች ንጹሃን ዜጎች ላይ የተወሰደውን እርምጃ የተመለከቱ አስተያየታቸዉን ሰጥተዋል፡፡ ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸውን ከመግለጽ የተቆጠቡት አስተያየት ሰጪ በየቤቱ በጅምላ ከተገደሉት ሌላ ታግተው በታጣቂዎች የተወሰዱም አሉ፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ የሰባት ሰፈራ ጣቢያ ነዋሪዎች አከባቢውን ለቀው መቻራ በተባለች የአከባቢው አነስተኛ ከተማ ተጠልለው እንደሚገኙ የገለጹት አስተያየት ሰጪ ዛቻ እና ማስፈራሪያው “ኦነግ ሸነ” ካሉት የታጠቀ ቡድን ይደርሳቸው እንደነበር ገልጸዋልም፡፡ ግድያውም የአማራ ብሔር ላይ ያነጣጠረ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
የአከባቢው ማህበረሰብ ሰፈራውን ለቀው በመውጣቱ ትናንት መከላከያ ደርሶ የሟቾች አስከረን ጠብቆ ማደሩን እና ዛሬ ሟቾችን በጅምላ መቃብር ከቀበሩ መካከል መሆናቸውን የገለጹት እኚው አስተያየት ሰጪ እስካሁን ከ170 በላይ መቀበራቸውንም ተናግረዋል፡፡
ሌላው አስተያየት ሰጪ በፊናቸው የሟቾችን ቁጥር 300 ያደርሳሉ፡፡
የመንግስት ኮሚዩኒለኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶ/ር ለገሰ ቱሉ የተፈጸመውን የጅምላ ግድያ አረጋግጠው ለግድያውም መንግስት ሸነ በሚል በሽብርተኝነት የፈረጀውን የአ.ነ.ጦ. ተጠያቂ አድርገዋል፡፡
ዶ/ር ለገሰ የጉዳት መጠኑም እየተጠራ ነው ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህምድ የጸጥታ አካላት ከሚያደርሱበት ዱላ የፈረጠጠው የሸኔ ቡድን ቄለም ወለጋ ዞን ውስጥ የሚገኙ ዜጎች ላይ ጭፍጨፋ ፈጽመዋል ማለታቸውን ተከትሎ በቲዊተር ምላሽ የሰጡት የኦ.ነ.ጦ ቃል አቀባይ ኦዳ ተርቢ ግድያውን የስርዓቱ ሚሊሾች የፈጸሙት ነው በማለት መንግስትን በተጠያቂነት ከሰዋል።።
ስዩም ጌቱ
ነጋሽ መሐመድ
ማንተጋፍቶት ስለሺ