1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ደቡብ አፍሪቃ፤ ጦር መሣሪያና የወንጀል መስፋፋት፣

ሐሙስ፣ የካቲት 27 2006

ኦስካር ፒስቶሪየስ የተባለው ደቡብ አፍሪቃዊ የአካል ጉዳተኛ ታዋቂ አትሌት አምና «ቅዱስ ቫለታይን» በተሰኘው ዕለት ፈቅረኛውን ሌባ እቤቱ የገባ ስለመሰለው ተኮሶ በስህተተ ገደላት ከተባለ ወዲህ፣ ሰሞኑን የችሎት ሂደት ከተጀመረ ዛሬ 4 ኛ ቀኑን ይዟል። መገናኛ ብዙኀን

https://p.dw.com/p/1BLQN
ምስል Reuters

ለዚህ ችሎት ትል ግምት በሰጡበት ወቅት፤ የሀገሪቱ አንዱ ዐቢይ ማኅበራዊ ችግር በማነጋገር ልይ ይገኛል ። ይህም የጦር መሣሪያ በህጋዊና ህገ ወጥ በሆነ መንገድ በብዙ ዜጎች እጅ የሚገኝ በመሆኑ ነው። በዚህ ላይ በሀገሪቱ በየዕለቱ የሚፈጸመው የሰዎች ሕይወት ጭምር የሚጠፋበት ወንጀል እንደቀጠለ ነው። ተክሌ የኋላ ፣ የሁከትና የዕርቀ ሰላም ማዕከል የተሰኘውን ተቋም ዋና ሥራ አስኪያጅ በማነጋገር ተከታዩን ዘገባ አጠናቅሯል።

ደቡብ አፍሪቃ በዴሞክራሲ ጎዳና ላይ የምትገኝ ፤ በኤኮኖሚም የክፍለ ዓለሙ መሪ ሀገር መሆኑ እሙን ነው። ይሁንና በብዙኀኑ ዜጎችና በጥቂት ሃብታሞች መካከል ያለው የኑሮ ደረጃ ልዩነት ገና አልጠበበም። ወንጀል የበዛበት አንዱ ምክንያት፤ የሃብታምና የድሃ ልዩነት መስፋት ሳይሆን እንዳልቀረ ይነገራል። ሰሞኑን የኦስካር ፒስተርየስ ችሎት መያዝ እንደተጀመረ ፣ በሀገሪቱ የተስፋፋው የጦር መሣሪያ ጉዳይም ማነጋገር ይዟል። የፒስቶሪዬስ ጉዳይ በሀገሪቱ ውስጥ ስላለው የተዛመተ የኃይል እርምጃና ወንጀል የፈጸሙ ተገቢውን ቅጣት ስለማያገኙበት ሁኔታ ፣ የሁከትና የዕርቀ ሰላም ተቋም ምን ይላል ? ዋና ሥራ አስኪያጅ ፣ ወ/ት ደልፊን ሴሩማጋ--

Mandela Trauerfeier Johannesburg 10.12.2013
ምስል Reuters

«በሁለቱም መካከል ልዩነት መኖሩን ለመግለጽ እወዳለሁ። ዘወትር የሚያጋጥመው የኃዕል እርምጃ ራሱን የቻለ ታሪክ ያለው ነው። ጥፋት ያጠፋ ለፍርድ ሳይቀርብ የሚኖርበት ሁኔታ ደግሞ ሌላ የተለየ ጉዳይ ነው። ሁከትን በተመለከተ አንድ ሰው የሌላውን ንብረት ለመዝረፍ ሲል ወይም በቤተሰብ መካከል በሚፈጠር አምባጓሮ በጥይት የሰው ሕይወት የሚጠፋበት ድርጊት ቢያስደነግጥም እንግዳ ነገር ግን አይደለም።

ሕብረተሰቡን በሰፊው ያስደነገጠው ሌላው ጉዳይ ምንድን ነው ---አንድ ታዋቂ የደቡብ አፍሪቃ ዜጋ ማኅበረሰቡ በልዩ አድናቂትና አክብሮት የሚመ ለከተው ሰው ፤ ሌላ ሰው ገደለ መባሉና አሁን ለፍርድ መቅረቡ ነው። »

በደቡብ አፍሪቃ ግድያ መስፋፋቱ ለሀገሪቱ ከባድ ችግር ነው። ይሁንና ይህ ቀደም ባሉት ጊዜያትም የነበረና አሁንም ሊወገድ ያልቻለ የማኅበራዊ ዕድገት ጠንቅ መሆኑን ነው ወ/ት ደልፊን ሴሩማጋ የገለጡት። ጣፋት እያጠፉ ሳይቀጡ የመታለፉ ጉዳይ እንዴት ይታያል? እንዲህ ያብራራሉ--

«ሌላው ጉዳይ ጥፋት አጥፍተው፣ ሰዎች ሳይቀጡ የሚታለፉበት ሁኔታ አይኖርም። ዋናው ዳኛ ፣ ህዝቡ ፤ በፍርዱ ሂደት በታዛቢነት እንዲገኝ መፍቀዳቸው፤ የሀገሪቱ የፍርድና ፍትኅ አያያዝ ከሕብረተሰቡ በኩል አመኔታ እንዲጣልበት ለማድረግ ነው። በደቡብ አፍሪቃ የታወቁና የተከበሩ ሰዎች ፤ ከሕግ በታች እንጂ ከሕግ በላይ አይደሉም። ሁለቱንም ጉዳዮች በጥሞና መገንዘብ ያሻል። የሕግና ፍትኅ ሥርዓቱን እናውቃለን። እርሱም ተግባሩን፣ እንደሚያከናውን እንገነዘባለን። በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ ሰዎች፣ ለየት ያለ የላቀ ግምት ለሚሰጣቸው ሰዎች በሁሉም ረገድ ለአነርሱ የሚበጅ የላቀ ነገር ይደረግላቸዋል የሚል ቅሬታ ያሰማሉ፤ ግን በዚህ የተለየ የፍርድ ሂደት፣ ሥራውን በትክክልና በተሟላ ሁኔታ ማካሄድ የሚያስችል ሥርዓት መኖሩን ነው ሊያሳዩን የፈለጉ። እርግጠኛ ነኝ፣ ሁሉም የተስተካከለ አያያዝና ብይን ነው የሚያገኘው።»

12.2013 DW Liveübertragung Trauerfeier Nelson Mandela Portrait

የሁከትና የዕርቀ ሰላም ማዕከል ዋና ሥራ አስኪያጅ ወ/ት ደልፊን ሴሩማጋ እንዳሉት፤ ኦስካር ፒስተሪየስ ጥብቅ የጸጥታ ቁጥጥር በሚደረግበት ቅጥር ግቢ ውስጥ እየኖረም ነው ጦር መሣሪያ የያዘው። ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ በሕጋዊ ፈቃድ ጦር መሣሪያ መያዝ ይቻላልና ብዙዎች የጦር መሳሪያ ባለቤቶች መሆናቸው ይታወቃል። በሕገ-ወጥ መንገድ የታስፋፋ ጦር መሣሪያም አለ። በየቤቱ ሰው ጦር መሣሪያ የሚይዘው ፖሊስ በተሻለ ሁኔታ ፀጥታ ማስከበር አይችልም ከሚል ሥጋትም ሆነ ግንዛቤ ነው። የሰሞኑ የፒስተርየስ የፍርድ ቤት የችሎት ሂደት መጪውን ምርጫና የ ANC ን የቅሌት ተግባራት ያሥረሳ ይሆን?

«አይመስለኝም፤ ምክንያቱም ደቡብ አፍሪቃ አዲስ ዴሞካራሲ የገነባች ሀገር ሆና ነው የምትታየው። በዚህም ሳቢያ ህዝቡ ባለው የመምረጥ መብት በትክክል ማንን እንደሚመርጥ ነው የሚያሰላስለው። የፒስተርየስን ጉዳይ በጥሞና የሚከታተል የፍርድና ፍትኅ ሥርዓት የመኖሩን ያህል ፣ ሕዝቡ ስለመጪው ምርጫም በመነጋገር ላይ ነው።»

ደቡብ አፍሪቃ ፣ ማዲባ(የተከበሩ ኔልሰን ማንዴላ) ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ በኋላ እርሳቸውን የመሰለ አርአያ መተካት አይቻላት ይሆን?!

Nelson Mandela Statue enthüllt
ምስል Reuters

«እኔ በግሌ የአሁኖቹን መሪዎች ከማዲባ ጋር አላነጻጽራቸውም። ማዲባ በራሳቸው መለኪያ ብቻ የሚመዘኑ ሰው ናቸው። ለቆሙበት ዓላማ ሁሉ ዝና ያተረፉ ሰው ናቸው። በግለሰብ ልዕልና ከታዬ ፣ በዓለም መድረክ የታወቁት ሰው ፣ አሁን ስለሌሉ ያን ኩራት እናጣለን። የእርሳቸው አለመኖር ትልቅ እጦት ነው። ከእርሳቸው ጋር የምናነጻጸረው፣ በምንም ዓይነት የለንም።»

ተክሌ የኋላ

ልደት አበበ

ኂሩት መለሰ