ያየለው የሶሪያ ዓመፅ
ሰኞ፣ ሐምሌ 16 2004የቃታር ጠቅላይ ሚኒስትር ሼክ ሀመድ ቢን ያሲም አል ታኒ ዛሬ እንዳስታወቁት፤ የአረብ ሊጋ አል አሳድ ስልጣናቸውን ባስቸኳያ እንዲለቁ ጠይቋል። እንደ አልጃዚራ ዘገባ አል በአሳድ ላይ ጉዳት ሳይደርስ አገራቸውን ለቀው የሚወጡበትን መንገድ ሊጋው እንደሚያመቻች አል ታኒ ገልፀዋል። ሚኒስትሩ አክለውም የሶሪያን ስደተኞች ለመርዳት ሊጋው 100 ሚሊዮን ዶላር ዝግጁ ማድረጉን፣ እንዲሁም ልዩ የሶርያ ልዑክ ኮፊ አናን ንግግራቸውን ስልጣኑን ወደፊት ከሚረከበው የሽግግር መንግስት ላይ እንዲያተኩሩ አሳስበዋል።
እንደ ተቃዋሚ ወገኖች ገለፃ፤ የመንግስት ወታደሮች ደማስቆስ ውስጥ የመኖሪያ አካባቢዎችን ጭምር ሲያጠቁ ሰንብተዋል።
በሰሜን ሶሪያ በምትገኘው ሁለተኛ ትልቅ ከተማ አሌፖ በመንግሥትና በተቃዋሚዎች መካከል ትናንት ከባድ ውጊያ ሲካሄድ ቆይቷል። ፍልሚያው ባየል ቁጥር አገር እየለቀቀ ወደ ጎረቤት አገሮች ቱርክ እና ኢራን የሚሰደደው ዜጋ በጣሙን ጨምሯል። የድንበር መሸጋገሪያ ባብ ኤል ሳላም በአማፂያኑ እጅ መሆኑ ተነግሯል። አንድ የኢንተርኔት ቪዲዮ በድንበር አካባቢ ስላለው ግጭት ሲያሳይ፤
« የመሸጋገሪያ ድንበር ባብ ኤል ሳላምን ከከበብን በኋላ ከአሳድ ሰዎች ነፃ አድርገናል። ከከባድ ሽንፈት በኋላ ሸሽተዋል። ይኼው እኔ ባብ ኤል ሳላም መተላለፊያ ከሶሪያ ነፃ አውጭ ወታደር ወንድሞቼ ጋ ቆሜያለሁ። ይህ ህንፃ ከቱርክ ጋ ይለየናል። እግዚያንሄር ፍቃዱ ከሆነ አሌፖን ነፃ አውጥተን አቃጣሪዎቹን ለመሸኘት ወደ ፕሬዘዳንቱ ቤተ መንግስት እናመራለን፤ ።»
የመንግስት ወታደሮች ይህንኑ የድንበር መሸጋገሪያ ቆይተው ከአየር እንደደበደቡ ተገልጿል። ከኢራን ጋ በሚያዋስነው ድንበርም እንደዚሁ ጦርነት እንደሚካሄድ ነው የሚነገረው፤« ሶርያ ውስጥከቀጠለው ውጊያ በኋላ እጅግ ብዙ ሰዎች እየተመለሱ ነው። ባለፈው ሀሙስ ብቻ 3000 ሰዎች ከጦርነት ሸሽተው መጥተዋል። ይህም በድንበር አካባቢ የሚካሄደውን ስራ ከባድ አድርጎታል። ይሁንና በትራንስፖርት ሚኔስቴር ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ከድንበሩ ወደ ባግዳድ ልንወስዳቸው ችለናል።»
ይላሉ የድንበሩ ከተማ ከንቲባ አብደልሚኒም ካላፍ ። የሶሪያ የተቃዋሚ ብሔራዊ ምክር ቤት እንደገለፀው ከቱርክ መንግስት ጋ የድንበር ቁጥጥሩን በተመለከተ ውይይት ተጀምሯል። የብሔራዊ ምክር ቤት ቃል አቀባይ አብዱል ባሴት ሳኤዳ፤
« የድንበር መተላለፊውን ሙሉ ቁጥጥር ገና በትክክል ማጣራት ይኖርብናል፤ በዚያ ስላለው ሁኔታ ለመናገር ። ስለዚሁ ጉዳይ ከቱርክ መንግስት እና ከሶሪያ ነፃ አውጭ ጦር ጋ እንመክራለን። ምክንያቱም ቱርክ ኋላፊነት አለባትና። በመሠረቱ በድንበሩ የሚታየውን ሁኔታ ለማስተካከል የሚያስችሉ ውሳኔዎች መወሰድ አለባቸው ።»
የሶሪያ የመንግስት ቴሌቪዥን ከቀናት በኋላ ትናንት ለመጀመሪያ ጊዜ አሳድን በቴሌቪዥን አሳይቷል። ዛሬ የአውሮፓ ህብረት ብራስልስ ውስጥ ባደረገው ውይይት በሶርያ መንግሥት ላይ ማዕቀቡን ለማጠናከር ወስኗል። ይህ በዚህ እንዳለ፣ የሶሪያ መንግስት ከውጭ አገሮች ጥቃት ከተሰነዘረበት በኬሚካል መሳሪያዎች እንደሚጠቀም ገልጿል።
ልደት አበበ
አርያም ተክሌ