የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና ጉዳይ
ረቡዕ፣ ሰኔ 8 2008
ይህንንም ተከትሎ የሚንስቴር መሥርያ ቤቱ ፈተናዉን ከሰኔ 27 እስከ 30 2008 ዓ/ም ለመስጠት አቅዶ እንደነበር በመግለጫዎቹ አስታዉቋል። ይሁን እንጅ ፈተናዉ የሚጀመርበት ቀን የራመዳን ፆም ፍቺ በዓል ላይ ስለሚደረብ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የፈተናዉ ጊዜ እንዲራዘም ለትምህርት ሚኒስቴር ባቀረበዉ ጥያቄ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ከሃምሌ 4 እስከ 7 2008 ድረስ እንዲሰጥ መወሰኑን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ያቀረበዉን ጥያቄ ይዘት በተመለከተ የምክር ቤቱ ምክትል ፕሬዝደንት ሼኺ ኡመር ኢማም ተማሪዎቹ ፆሙን እያሰቡ የሚፈተኑት ፈተና ጥሩ ዉጤት አያመጣም በሚል ሰብብ መሆኑን ለዶቼ ቬሌ ተናግረዋል።
የፈተናዉ ጊዜ በድጋሚ የተለወጠዉ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አቀረበ በተባለዉ ጥያቄ እንዳልሆነ ግን በድምጻችን ይሰማ እና በኦሮሞ መብት ተሟጋቾች መሆኑን የፖለትካ ተንታኝ እና የኦሮሞ መብት ተሟጋች አቶ ጀዋር መሐመድ ይናገራሉ።
አሁንም ለፈተናዉ የተሰጠዉ ቀነ ገደብ በቂ ባለመሆኑ ለሦስተኛ ግዜ እንዲራዘም ግፊት የማድረግ እቅደ እንደነበራቸዉ ያመለከቱት አቶ ጀዋር መሀመድ ይህኛዉን ሃሳባቸዉን የቀየሩበት ምክንያትም ተማሪዎቹ እና ፈታኞቹ ላይ የበለጠ ጉዳት እንዳይደርስ ታስቦ መሆኑ ገልጸዋል።
የተራዘመዉ የፈተናዉ ጊዜ በቂም ባይሆን በኦሮሚያ ክልል ያሉት ተማሪዎች ፈተናዉን እንዲፈተኑ የመከሩት አቶ ጀዋር መምህራንም ሆኑ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለተፈታኞቹ የማካካሻ ትምህርት አስቀድመዉ እንዲሰጡም አሳስበዋል።
ከኢትዮጵያ ትምህርት ሚኒስቴር የበለጠ መረጃ ለማገኘት ያደረግነዉ ጥረት አልተሳካም።
መርጋ ዮናስ
ሸዋዬ ለገሠ