የጥምቀት በዓል አከባበር በተለያዩ ከተሞች
ዓርብ፣ ጥር 11 2010በዓሉ እንደወትሮው ሁሉ ከትናንት ጥር 10 ቀን ማለትም ከከተራ በዓል ጀምሮ ታቦታት ከየ አድባራቱ ወጥተው በየተዘጋጀላቸዉ ማደሪያ በማረፍ በሕዝበ ክርስቲያኑ፤ በካህናት ማኅሌት እንዲሁም ወረብ ታጅበው ስብሃተ እግዚአብሔር ሲደርስ መዋሉንም ያነጋገርናቸው ምዕመናን ያስረዳሉ። አዲስ አበባ ላይ ታቦታትን ከጃንሜዳ አጅበው ሲመለሱ መንገድ እንደሆኑ ካገኘናቸው የበዓሉ ተሳታፊዎች አንዳንዶቹ ለበዓል የወጣው ሕዝብ ካለፈው ዓመት ቀንሶ ማየታቸውን ይናገራሉ። ለሌሎቹ ደግሞ ከወትሮው ለየት ብሎ በዓሉ የደመቀ ነበር።
በበዓሉ ላይ ካነጋገርናቸዉ መካከል በጠቅላይ ቤተክህነት የልማት እና ተራድኦ ኮሚሽን መምሪያ፤መምህር አስቻለዉ ካሴ ፤ የዘንድሮው የጥምቀት በዓል ከወትሮው ለየት ባለ የመገናኛ ብዙሃንን ሽፋን ማግኘቱን ገልጸው፤ የወጣቱ ተሳትፎ ለየት ማለቱን ዘርዝረዋል።
በአዲስ አበባዉ ጥምቀተ ባህር የተገኘው ሕዝብ ቁጥር የቀነሰው ምናልባት ወደጎንደር ለበዓሉ ብዙ ሰው ተጎዞ ይሆናል የሚለውን የበዓሉን ታዳሚዎች ግምት በመያዝ ወደ ጎንደር ደወልን። ታቦት አጅቦ ሲመለስ ያገኘነው የከተማዋ ነዋሪ የሆነዉ ወጣት ዳዊት፤ ከአምናዉ የበለጠ ሕዝብ ለበዓሉ ጎንደር ከተማ መገኘቱን አመክቷል። በዓሉ ባህር ከተማም ደምቆ መከበሩን ከስፍራዉ ያነጋገርነዉ ዲያቆን ሙሉቀን ብርሃኑ በአጭሩ ገልጾልናል። የበዓሉ ተሳታፊዎች የጥምቀትን በዓል በማዕዳሰስ ቅርስነት በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ስለሚደረገዉ ጥረትም የሚሰማቸዉን አካፍለዉናል።
ሸዋዬ ለገሠ
ነጋሽ መሐመድ