የጠ/ሚ ኃይለማርያም የሱዳን ጉብኝት
ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 20 2005ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትናንት ከፕሬዚዳንት አልበሽር ጋር ከተነጋገሩ በኋላ ዛሬ ከደቡብ ሱዳን አቻቸው ጋር ለመወያየት ወደ ጁባ መጓዛቸዉም ተገልጿል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት በሁለቱም ሱዳኖች መካከል የሰፈነውን ችግር የመፍታት አካል መሆኑ ቢገለፅም፤ የሁለቱ ሱዳኖች አለመረጋጋት በኢትዮጵያ ጸጥታ ላይ ተጽዕኖ እንዳለውም ተመልክቷል።
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ትናንት ከሰሜን ሱዳን አቻቻው ፕሬዚዳንት አልበሽር ጋር ተገናኝተው ተነጋግረዋል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉዞ ዓላማ በሁለቱ ሱዳኖች መካከል በአዲስ አበባ የተደረሰው ስምምነት ተፈጻሚነት እንዲያገኝ ግፊት ለማድረግ መሆኑ ተገልጿል። ከዓመት በፊት የተካሄደውን የሱዳን ህዝበ ውሳኔ ተከትሎ በሁለቱ ሱዳኖች መካከል የተከሰተው አለመግባባት መፍትሔ እንዲያገኝ ኢትዮጵያ ጥረት ስታደርግ ነበር ይላሉ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃለ አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፥ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉዞም የዚህ ጥረት አካል ነው።
ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ጋር ከተነገጋገሩ በኋላ የሱዳኑ መሪ አልበሽር ከደቡብ ሱዳን አቻቸው ሳልቫ ኪር ጋር ለመነጋገር ዝግጁ መሆናቸውን መግለጻቸውን የሮይተርስ ዘገባ አመልክቷል። የፕሬዚዳንቱን ንግግር ተከትሎ ምናልባት ሱዳንና ደቡብ ሱዳን በመስከረሙ ስምምነት መሰረት በመካከላቸው ያለውን ልዩነት አስወግደው ተቋርጦ የነበረውን የዘይት ምርት አቅርቦት ይጀምራሉ ተብሎ ይገመታል።
ሆኖም ግን በአዲስ አበባ በተደረሰው ስምምነት መሠረት ሱዳንና ደቡብ ሱዳን በሁለቱ ሀገራት ድንበሮች ላይ የሰፈሩ ወታደሮቻቸውን አላስነሱም። ከጦር እንቅስቃሴ ነጻ የሆነ ቀጠናን ማቋቋም ለዘይት ምርት መጀመር አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታ መሆኑ ይነገራል። በቀን 350,000 በርሜል ዘይት ታመርት የነበረ ደቡብ ሱዳን፣ ከሱዳን ጋር በተፈጠረው የዘይት ማስተላለፊያ ቧምቧ ዋጋ አለመስማማት ምክንያት እየተገባደደ ባለው የፈረንጆች ዓመት ጥር ወር ምርቱን አቋርጣ ነበር። ደቡብ ሱዳንም የዘይት ምርቷን በዓመቱ መጨረሻ ለማስጀመር አቅዳ እንደ ነበር ይታወሳል።
ከሁለት ሳምንታት በፊት የአፍሪቃ ህብረትና የምዕራብ ሀገራት ተወካዮች አልበሽርና ሳልቫ ኪር በመካከላቸው የተፈጠሩ አለመግባባትን ለመፍታት በአፋጣኝ ተገናኝው እንዲመክሩ ጥሪ አቅርበውላቸዋል። በዚህም መሠረት ሁለቱም ሱዳኖች ተወካዮች በመጪው የፈረንጆች ዓመት ጥር ወር አጋማሽ ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ መነጋገር እንዲጀምሩ ታቅዷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከአልበሽር ጋር ከተነጋገሩ በኃላ ዛሬ ወደ ጁባ ተጉዘዋል። በዚያም ከፕረዚዳንት ሳልቫ ኪር ጋር ይነጋገራሉ።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያ በሱዳንና ደቡብ ሱዳን ፖሊቲካ ውስጥ ጉልህ የአደራዳሪነት ሚና ስትጫወት ይታያል። በሁለቱ ሀገራት መካከል እየተካሄደ የነበረውን የፖሊቲካ ሽኩቻን ይፈታል ተብሎ በታመነው የመስከረሙ የአዲስ አበባ ድርድር፤ ኢትዮጵያ ዋና አደራዳሪ ነበረች። ምክንያቱም የሱዳንና ደቡብ ሱዳን የጸጥታ ሁኔታ በኢትዮጵያ ጸጥታ ላይ ተጽዕኖ ስላለው ነው ይላሉ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ።
ገመቹ በቀለ
ነጋሽ መሐመድ