የጎርጎሮሳዊዉ ቀመር የገና በዓል
ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 16 2005በርካታ ተከታዮች ባሏት የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን መንበር ሮም የገና በዓልን እንደከዚህ በፊቱ እና እንደተለመደዉ የማክበሩ ሁኔታ መለወጡ ተሰምቷል። ይህንም ሆኖ ግን ዛሬም በዓሉ በእምነቱ ተከታዮች እና አባቶች ደምቆ በጴጥሮስ ወጳዉሎስ መንበር ቫቲካን ሥርዓቱ ሳይጓደል ምሽቱን ተከብሯል፤ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኑዲክት 16ኛም በየዓመቱ እንደሚያደርጉት በተለያዩ ቋንቋዎች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል። አሜሪካዉያን ለወትሮዉ ገናን ደመቅ አድርገዉ ማክበሩን ያዘወትሩ እንዳልነበር ዘንድሮ የዋጋ ንረቱና በቅርቡ በኒዉታዉን ከተማ ከ20 በላይ ህፃናት የተገደሉበት አጋጣሚ በዓላቸዉን ያቀዘቀዘዉ መስሏል። በእስራኤል ደግሞ በቤተልሄም፤ በናዝሬት፤ በሃይፋ ሃዳርና በገሊላ አካባቢዎች የእምነቱ ተከታይ የሆነዉ የሀገሬዉ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች በዚህ ወቅት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተወለደባት በሚታመንባት ምድር በመገኘት በዓሉን አክብረዋል። በቤተልሄሙ ስነ ስርዓት ላይ በ10 ሺህዎች የሚቆጠሩ ክርስቲያን ፍልስጤሞችና በአሉን ለማክበር ከመላው አለም የተሰባሰቡ ምዕመናን ተገኝተዋል ። በዚህ በጀርመንና በበርከታ የአዉሮጳ ሀገራት ብትን የሚለዉ በረዶ ሳይወርድ ቅዝቃዜዉም ሳይጠና ግን በዝናብ ማለዳዉ ጀምሮ ረፈድ ሲል ጸሃይ ፍንትዉ ብላ ወጥታለች። ምንም እንኳ ነጩን ገና ማየት ባይችሉም የገና በዓል ግን የወትሮ ወጉን አላጣም፤ ትናንት ከቀትር በኋላ አንስቶ እረጭ ያለዉ አዉድ በዓሉ በርግጥም የሰላምና የደስታ ሌሊት መሆኑን እንደዜማዉ አመላክቷል። ከሮማ ቫቲካን፤ ከእስራኤል ናዝሬት፤ ራዲዮ ጣቢያችን ከሚገኝበት ቦን ጀርመን እንዲሁም ከዋሽንግተን ዲሲ የተጠናቀሩ ዘገባዎችን ያድምጡ።
ተኽለእግዚ ገብረኢየሱስ
ግርማዉ አሻግሬ
ገመቹ በቀለ
አበበ ፈለቀ
ሸዋዬ ለገሠ