የግብፅ ፖለቲካዊ ዉዝግብ
ማክሰኞ፣ ሐምሌ 3 2004
አዲሱ የግብፅ ፕሬዝዳት መሐመድ ሙርሲ ባለፈዉ ዕሁድ ባሳለፉት ትዕዛዝ መሠረት ባለፈዉ ሰኔ ተበትኖ የነበረዉ የግብፅ ምክር ቤት ዛሬ ተሰብስቧል።የግብፅ ጦር፥ ምክር ቤቱን የበተነዉ የሐገሪቱ ሕገ-መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ምክር ቤቱን «ሕገ-ወጥ ነዉ» ብሎ በመወሰኑ ነበር።ፕሬዝዳት ሙርሲ ምክር ቤቱ ዳግም እንዲሰየም ያሳለፉትን ዉሳኔም ወታደራዊዉ ምክር ቤትና ፍርድ ቤቱ ተቃዉመዉታል።የሙርሲ ዉሳኔ፥ የጦር ሐይሉና የሕገ-መንግሥታዊዉ ፍርድ ቤት ተቃዉሞ ወትሮም ያልተረጋጋዉን የግብፅን ፖለቲካዊ ቀዉስ እንዳያባብሰዉ አስግቷል።ነጋሽ መሐመድ ሐንስ-ሚሻኤል ኤሕል ከካይሮ በዘገበዉ ላይ ተመስርቶ የግብፅን ዉዝግብ ባጭሩ ይቃኛል።
የፕሬዝዳት መሐመድ ሙርሲ አዋጅ፥ቃል አቀባያቸዉ ባለፈዉ ዕሁድ እንዳነበበዉ።«ፕሬዝዳንቱ ባሳለፉት ዉሳኔ መሠረት፥-አንደኛ፥-ባለፈዉ ሰኔ አስራ-አምስት ምክር ቤቱ እንዲበተን የተላለፈዉ ዉሳኔ ተሽሯል።ሁለተኛ፥-የተመረጠዉ ምክር ቤት መጋቢት ሰላሳ፥ ሁለት ሺሕ አስራ-አንድ በፀደቀዉ ሕገ-መንግሥት መሠረት ተሰይሞ ሐላፊነቱን መወጣት አለበት።ሰወስተኛ፥-ሕዝቡ አዲስ ሕገ-መንግሥት ባፀደቀ በስልሳ ቀናት ዉስጥ የአዲስ ምክር ቤት አባላት ምርጫ ይደረጋል።»
በዚሕ አዋጅ መሠረት የግብፅ ሕግ-መምሪያ ምክር ቤት እንደራሴዎች ዛሬ ተሰበሰቡ።እንደራሴዎቹ ባጠገቡ እያለፉ ከትልቁ አዳራሽ ሲገቡ ያየዉ ባለ ኪዮስክ «እስካሁን ሠላም ነዉ» አለዉ ኪዮስኩ አጠገብ ቆሞ የእንደራሴዎቹን መሰብሰብ ለሚከታተለዉ ጋዜጠኛ «ነገ ግን እንደ ዛሬ አይቀጥልም።»
በርግጥም በአብዛኛዉ የሙስሊም ወንድማማቾች አባላት የሆኑት እንደራሴዎች የፕሬዝዳንታቸዉን ትዕዛዝ አክብረዉ ተራ-በተራ ከምክር ቤቱ አዳራሽ ሲገቡ የተተናኮላቸዉ ሐይል የለም።
የግብፅ ጦር ሐይል ጠቅላይ ምክር ቤት አዛዥ ፊልድ ማርሻል መሐመድ ሁሴይን ተንታዊና ፕሬዝዳንት ዶክተር ኢንጂነር መሐመድ ሙርሲ አዋጁ በወጣ ማግስት ትናንት እንደ ጥሩ ወዳጅ ጎን ለጎን ተቀምጦ ወታደራዊ ትርዒት ሲመለከቱ ያያቸዉ የዉጪ ታዛቢ በጣሙን አፍሪቃ-አረቡ በግብፆች መቻቻል ትንሽም ቢሆን መቅናቱ አልቀረም።
አብዛኛዉ ግብፃዊ ግን ልክ እንደ ባለኪዮስኩ ሁለቱ ግዙፎቹ የገጠሙትን ሽኩቻ መጨረሻ ለማየት-እንደ ጓጓ፥ እንደሰጋ ዛሬን አመሸ።በሕዝብ አመፅ ከሥልጣን የተወገዱት ፕሬዝዳንት ሆስኒ ሙባረክ የሾሟቸዉ የግብፅ ሕገ-መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ዳኞች፥ ግብፅን ከሐምሳ አመታት በላይ የገዛዉ ጦር ሐይልንና ከሰማንያ አራት-አመት በላይ በተቃዋሚነት የታገለዉን ሐይማኖታዊ ፓርቲ የሚወክሉትን ጠንካሮች ሽኩቻ እያጋግሙት ነዉ።
ፍርድ ቤቱ የሙርሲን ፕሬዝዳንታዊ አዋጅ ትናንት ዉድቅ አድርጎታል።የፍርድ ቤቱ ዳኛ ኢብራሒም ደርዊሽ ጦሩ የፕሬዝዳንቱን አዋጅ ለመቀልበስ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል።
«ዉሳኔዉ የወታደራዊዉን ምክር ቤት ሥልጣን የሚጋፋና ምክር ቤቱን የሚቃረን ነዉ።ምክንያቱም ሕግ የማስከበሩ ሕገ-መንግሥታዊ ሐላፊነት የወታደራዊ ምክር ቤት ነዉ።ሥለዚሕ ወታደራዊዉ ምክር ቤት ሕልዉናዉንና ሥልጣኑን ማስከበር አለበት።ከሁሉም በላይ ዉሳኔዉ የግብፅ ሕግን የሚዳፈር ነዉ።ወታደራዊዉ ምክር ቤትና የግብፅ ሕግ ጥበቃ ካልተደረገላቸዉ ሕልዉናቸዉን ያጣሉ።»
ወታደራዊዉ ምክር ቤት ትናንት ባስቸኳይ ተሰብስቦ ከተነጋገረ በሕዋላ በቃል አቀባዩ በኩል የፕሬዝዳንቱን አዋጅ እንደማይቀበለዉ አስታዉቋል።መግጫዉ ግን የተፈራዉን ያክል ጠንካራ አልነበረም።የጄኔራሎቹን ልብ-ግን የሚያዉቅ ቀርቶ የሚገምትም ማግኘት ከባድ ነዉ።
ነጋሽ መሐመድ
ሸዋዬ ለገሠ