1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የግሪክ ክስረትና የአውሮፓ ፈተና

ረቡዕ፣ ግንቦት 3 2003

የግሪክን ኤኮኖሚ ክፉኛ ያናጋው የበጀት ኪሣራ የኤውሮውን የጋራ ምንዛሪ ክልል እንደገና እየፈተነ ነው።

https://p.dw.com/p/RMy9
ምስል fotolia/DW

በተለይም የኤውሮው ምንዛሪ ዓባል ሃገራት የፊናንስ ሚኒስትሮች ባለፈው አርብ በሚስጥር ተገናኝተው በጉዳዩ መምከራቸው ከታወቀ ወዲህ ችግሩ የሰሞኑ ዋና መነጋገሪያ ርዕስ ሆኗል። በወቅቱ ሁለተኛ የዕርዳታ ከረጢት በመቋጠር ግሪክንና የጋራ ምንዛሪውንም ከውድቀት በማዳኑ ሃሣብ ሰፊ ክርክር እየተካሄደ ነው። በሌላ በኩል የግሪክ ከምንዛሪው ሕብረት መውጣት ለችግሩ እንደ አማራጭ መፍትሄ ሆኖ መቅረቡን የሚቀበል ማንም የለም። ይልቁንም የዜና ምንጮች እንደሚጠቁሙት ግሪክን ለማዳን በተሰጠው የመጀመሪያ የዕርዳታ ፓኬት ላይ አገሪቱን የተጫነውን ወለድ ለመቀነስና የሚመለስበትን ጊዜም ለማራዘም ሃሣብ መኖሩ አልቀረም።
የኤውሮው ምንዛሪ ክልል በዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ ሳቢያ ተራ በተራ ችግር ላይ እየወደቁ የመጡትን አየርላንድን፣ ፖርቱጋልንና ሌሎችንም ለማዳን ብዙ ሲጥር መቆየቱ ይታወቃል። በወቅቱም እንደገና በግሪክ ችግር ተወጥሮ ነው የሚገኘው። እርግጥ ብራስልስ ውስጥ በሽተኛዋን ግሪክን ማስታመም በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ክርክሩ ቢጦፍም መውጫውን በተመለከተ ቁልጭ ያለ መንገድ ገና ጎልቶ አይታይም። ግን ከወዲሁ ሁሉም ባለሥልጣናት ግሪክ ከኤውሮ ዞን የመውጣቷን ሃሣብ አጥብቀው ያስተባብላሉ። ከነዚሁ አንዱም የሕብረቱ ሸንጎ ፕሬዚደንት ሄርማን ፋን ሮምፑይ ናቸው።

“እርግጥ የግሪክ ከኤውሮ ዞን መወገድ ጨርሶ ጥያቄ ውስጥ አይገባም። ዕዳውን ሌላ መልክ ስለማስያዝ አይደለም የሚወራው። በወቅቱ ውይይት የሚደረገው ግሪክን ወደ ገበዮች ለመመለስና በዚያው እንደገና ገንዘብ ለማግኘት የሚያስችሉ ሁኔታዎችን በማስፈኑ ላይ ነው”

ሆኖም ግሪክ ቀደም ሲል እንደታቀደው ከመጪው ዓመት ጀምሯ በዝቅተኛ ወለድ ከመዋዕለ-ነዋይ ገበዮች ገንዘብ መበደር መቻሏ ከወቅቱ ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር ሲበዛ ያጠራጥራል። ስለዚህም ውስጥ ውስጡን ከወዲሁ እንደሚሰማው ከኤውሮው መንግሥታት ተጨማሪ አስቸኳይ ብድር ማግኘቷ የሚቀር አይመስልም። ብዙ ሳይርቅ ከአንድ ዓመት ገደማ በፊት ነበር ጀርመንንና ፈረንሣይን ጨምሮ አንዳንድ የኤውሮ አገሮች ለግሪክ 110 ሚሊያርድ ኤውሮ ለመስጠት ቃል የገቡት። የግሪክ መንግሥት ተጨማሪ የቁጠባ ዕርምጃ ለመውሰድ በመስማማቱም የኤውሮው ምንዛሪ ክልል ብድሩ የሚመለስበትን ጊዜ ወደ ሰባት ዓመታት ማራዘሙና የወለዱንም መጠን በአንድ ከመቶ ዝቅ ማድረጉ ይታወሣል። ግን አሁን እንደሚታየው ዕርምጃው ሁሉ ግሪክ በቂ መፈናፈና እንድታገኝ አላደረገም።

በወቅቱ የአውሮፓው ሕብረት ኮሚሢዮን የፊናንስ ጠበብት፣ የአውሮፓ ማዕከላዊ ባንክና የዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቋም የአይ.ኤም.ኤፍ. ወኪሎች አቴን ውስጥ በመገኘት ሁኔታውን ለመታዘብና ግሪክ የለውጥ መርኋን እንድትገፋበት ለማበረታታትም እየሞከሩ ነው። በፊታችን ወር የሚቀርበው የዚሁ ምርመራ ውጤት የግሪክ የወደፊት ሂደት ምን ሊመስል እንደሚችል ምላሽ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል። አሁን ከወዲሁ ሂደቱን እንዲህ ብሎ መናገሩ ግን የጀርመን የፊናንስ ሚኒስትር አፈ-ቀላጤ ማርቲን ኮትሃውስ ለጋዜጠኞች እንዳስረዱት አዳጋች ጉዳይ ነው።

“በዚህ ጉዳይ ላይ ምን፣ መቼና የት ብሎ ከወዲሁ ለማስላት መሞከሩ አይጠቅምም። አዝናለሁ፤ እዚህ ላይ በዕውነቱ ልለው የምችለው ነገር የለም”

እርግጥ የግሪክን የበጀት ይዞታ በማስተካከሉ ረገድ ችግር እንደሚኖር የጀርመን መንግሥት ከወዲሁ ጠንቅቆ የሚያውቀው ጉዳይ ነበር። የፊናንስ ሚኒስትሩ ቮልፍጋንግ ቮይብለ ባለፈው ሚያዚያ ወር የአውሮፓ ሕብረት የፊናንስ ሚኒስትሮች ስብሰባ እስከዚያው የቀረበው ዕርዳታ እንደማይበቃ ማመናቸው አይዘነጋም።

“ዕርዳታው በቂ መሆኑን ዛሬ እርግጠኛ ሆነን ለመናገር አንችልም። ነገር ግን በጥሩ ትብብር ለአዳዲስ ወይም አዲስ ለሚከሰቱ ችግሮች በጋራ መፍትሄ ለማቅረብ ብቁ መሆናችን ያስመሰከርነው ጉዳይ ነው”

ግሪክን ከኤውሮ ዞን ማስወጣቱ በወቅቱ በአውሮፓው ውል ላይ ይህን ጉዳይ የሚመለከት አንቀጽ ባለመኖሩ ብቻ ሣይሆን የጋራ ምንዛሪውን አስተማማኝነትም ጥያቄ ውስጥ የሚከት በመሆኑ ማነጋገሩ አልተመረጠም። ሃሣቡ እንዲነሣ የሚፈልግም የለም። በሌላ በኩል ዕዳውን በማስወገዱ ረገድ ውስጥ ውስጡን ጭብጥ ክርክር ነው የሚካሄደው። ለምሳሌ የካፒታል ባለቤቶች ለግሪክ ካበደሩት ገንዘብ የተወሰነውን ይተዉ የሚለው ሃሣብ ንግግር እየተደረገበት ነው። “ሄየር-ከት” ሲሉ በጸጉር ቆረጣ መስለውታል ሂደቱን የፊናንስ ጠበብት! ይህ፤ እንዲሁም የግሪክ መንግሥት ዕዳውን የሚመልስበትን ጊዜ ማራዘሙና ወለዱንም መቀነሱ ችግሩን ለመጋተር ይረዳል ተብሎ ነው የሚታመነው። በነገራችን ላይ የግሪክ አጠቃላይ ዕዳ ገና ከዛሬው ከአገሪቱ የኤኮኖሚ አቅም ወይም አጠቃላይ ብሄራዊ ምርት አንጻር 150 ከመቶ ይሆናል። ስለዚህም ዕዳው መቀነሱ በብራስልስ የአውሮፓ የፖሊሲ ጥናት ማዕከል ሃላፊ ዳኒየል ግሮስ እንደሚሉት የማይቀር የጊዜ ጉዳይ ነው።

“ይህን በተለያየ መንገድ ለማከናወን ይቻላል። እርግጥ በተቻለ መጠን በፍጥነት መደረጉ ግድ ነው። ይሁንና የዕዳ ቅነሣው አያያዝ ዘይቤም ወሣኝነት ይኖረዋል። የሚሽጋሸግ ብቻ ከሆነ ተመልሶ የሚመጣ ነገር ነው። ይህ ደግሞ ችግሩን መቋቋሙን የበለጠ ከባድ ያደርገዋል”

የዕርዳታው መራዘም እንደ አማራጭ ሆኖ መጠቀሱም አልቀረም። በሌላ በኩል ግሪክ ለመሆኑ ችግሩን በቁጥጥር ስር ለማዋል ትችላለች ወይ? ይህ ጥያቄ ሰሞኑን ተደጋግሞ ሲነሣ ተሰምቷል። በጀርመን የኮሜርስ ባንክ የምጣኔ-ሐብት ባለሙያ ዮርግ ክሬመር እንደሚሉት ስኬቱን የሚወስነው ችግሩን የመቋቋሙ ፍላጎት መጠን ነው።

“ጥያቄው ግሪክ ትፈልጋለች ወይ ነው። በመሠረቱ የማይቻል ነገር አይደለም። እንዲሆን ግን ግሪክ መንግሥታዊ ወጪዋን ከአሥር እስከ ሃያ በመቶ መቀነስ ይኖርባታል። አንድ በኪሣራ የተወጠረ የግል ተቋም ቢሆን ይህን ያደርገዋል። እንግዲህ የፖለቲካ ፍላጎት ጉዳይ ይሆናል ማለት ነው። ግን የግሪክ መንግሥት ሕልውናውን ስለሚያጣ ይህን ይፈቅደዋል ብዬ አላምንም። መንግሥታዊው ዕዳ ከአጠቃላዩ ብሄራዊ ምርት ፈጥኖ እንዳያድግ ለማድረግ ግሪኮች ካለፈው ዓመት ሶሥት ዕጅ የበለጠ መቆጠብ ይኖርባቸዋል። ይህ ደግሞ ከፖለቲካው አንጻር የማይጠበቅ ነገር ነው”

ይህ ካልሆነ የሚመረጠው መፍትሄ ምንድነው? የባንኩ ባለሙያ ዮርግ ክሬመር የማስትሪሽት ውል በአግባብ መከበር ችግሩን ለመፍታት ቁልፍ ሊሆን እንደሚችል ያምናሉ።

“ብዙ የጀርመን የኤኮኖሚ ጠበብት የሚከተለውን ሃሣብ ሰንዝረዋል። ይሄውም ወደ ማስትሪሽቱ ውል መንፈስ መመለስ የሚል ነው። አዎን፤ ምናልባት ግሪክን ለተወሰነ የሽግግር ጊዜ በመርዳቱ መቀጠል ይቻላል። ግን ከዚያ በኋላ ዕርዳታ እንደማይሰጥ ከአሁኑ ግዴታ አድርጎ ማስቀመጡም አስፈላጊ ነው። ይህም ባለገንዘቦች በመንግሥታት ድጎማ ላይ ተሥፋ እንዳይጥሉ ያደርጋል። ከዚህ ሌላ መሸጋገሪያ ዕርዳታ የሚያገኙ አገሮች ለምሳሌ ጀርመን እንዳደረገችው በሕገ መንግሥታቸው ውስጥ ከዛሬው የዕዳን መጠን የሚወስን አንቀጽ ማስፈር አለባቸው። ይህ ወደፊት ተመሳሳይ ችግሮች እንዳይፈጠሩ ይረዳል ብዬ አስባለሁ”

በጥቅሉ ግሪክን በመሳሰሉት የአውሮፓ አገሮች በተፈጠረው ከባድ የበጀት ኪሣራ የተነሣ በጋራ ምንዛሪው ላይ የተከተለው ግፊት ቀላል አይደለም። በዓለምአቀፍ ደረጃ ኤውሮ ዓመኔታን እያጣ እንዳይሄድ የዓባል መንግሥታቱ ስጋት እየጨመረም ነው የሄደው። የግሪክ ከኤውሮ ዞን መውጣት ወሬ ደግሞ እርግጥ ቢስተባበልም ሁኔታውን ያባብሰው እንደሆን እንጂ የተሻለ አያደርገውም። ጭጭምታው የግሪክን ሕዝብም እንዳስቆጣና ግራ እንዳጋባ ነው በአቴኑ የውጭና የአውሮፓ ፖሊሲ ጥናት ተቋም የኤኬኖሚ ተመራማሪ የሆኑት ጀርመናዊ የንስ ባስቲያን የሚናገሩት።

“እርግጥ ነው ነገሩ በግሪኮች ዘንድ የሚያናድድ፣ ተሥፋ የሚያስቆርጥና ይበልጥም ግራ የሚያጋባ ሆኖ ነው የታየው። ወሬው እርግጥ ወዲያው ተስተባብሏል። እና ግሪኮችም ለነገሩ ውዥምብር ላይ አልወደቁም። ቢቀር ኤውሮ ገንዘባቸውን ለማውጣት ወደ ባንክ ሲሮጡ አልታዩም”

ለማንኛውም ግሪክ ውስጥ ለሶሥተኛ ዓመት በተከታታይ የኤኮኖሚው ሁኔታ እየተባባሰ መምጣቱን ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት። መንግሥት የሚያስገባው ግብር ከዕቅዱ ያቆለቆለ ሆኖ ተገኝቷል። መዋዕለ-ነዋይም የሚያስፈልገውን ያህል አይደለም። ታዲያ ይህ ሁሉ ተደማምሮ የአቴኑን መንግሥት ችግር ቀላል አያደርገውም። የአውሮፓ ሕብረት ቀደም ሲል ወደ አቴን የላከው 110 ሚሊያርድ ኤውሮ እስካሁን መፍትሄን አላስከተለም። ይህም አገሪቱ ከናካቴው በሁለት እግሯ መቆም መቻሏን የሚያጠያይቅ ነው ያደረገው።

“የሚፈለገው ገንዘብ ብቻ ቢሆን ኖሮ ባልገደደ። ግን ችግሩ ይህ ብቻ ነው ብሎ ማሰቡ የዋህነት ነው። ግሪክ መዋቅራዊ ለውጥ ነው የሚያስፈልጋት። ይህ ደግሞ ዕዳን በመቀነስ ረገድ ብቻ አይደለም። ቅነሣው አንዴ ሊሣካ ይችላል። ግን አገሪቱ ጠቅላላውን ሕብረተሰብ ኤኮኖሚዋን ጨምሮ ሁሉንም መጠገን ይኖርባታል። ይህም እርግጥ ረጅም እስትንፋስን የሚጠይቅ ነገር ነው። እንግዲህ ግሪክ በአንድ ሌሊት ወይም ከአንዱ ዓመት ወደሌላው ከመሠረቷ ልትለወጥ አትችልም”

ከዚህ አንጻር ችግሩም፤ መፍትሄ ፍለጋውም ጊዜ የሚወስድ ነው የሚመስለው።

መሥፍን መኮንን

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ