1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጊኒ መፈንቅለ መንግስትና የአፍሪቃ ዕዉነት

ሰኞ፣ ጳጉሜን 1 2013

በ2008 ሻለቃ ሞሳ ካማራ፣ በ2013 ፊልድ ማርሻል አብዱል ፈታሕ አል ሲሲ፣ በ2019 ጄኔራል አሕመድ አዋድ ኢብን አዉፍ (ኋላ በጄኔራል አብዱል ፈታሕ አል ቡርሃን ተቀይረዋል)፣ በመሐሉ በ2020 ኮሎኔል አሲማ ጎይታ፣ በ2001 ኮሎኔል ማማዲ ዶዉምቦያ።አፍሪቃ ወደ 1970ዎቹና 80ዎቹ የመፈንቅለ መንግስት ዘመን እየተመለሰች ይሆን?

https://p.dw.com/p/3zzeo
Guinea | Fernsehansprache Mamady Doumbouya
ምስል Radio Television Guineenne/AP Photo/picture alliance

አፍሪቃ ወደ 1970ዎቹ ና 80ዎቹ እየተመለሰች ይሆን?

060921

ዓለም ይቸኩላል።ወይም የሚቸኩል ይመስላል።አፍሪቃ ደግሞ ሥራ-ምግባር ሲሆን ከብዙዉ ዓለም ዘግየት፣ ፖለቲካ፣ ስሜት ወሬ ሲሆን ግን ከሚቸኩለዉ ዓለም ፈጠን-ጠደፍ ይላል።ወይም ይመስላል።ኃምሌ 2013 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) መፈንቅለ መንግስት ነበር።ካይሮ ላይ።የመፈንቅለ መንግስቱ ሴራ፣ ዉጤት፣አስተጋብኦቱ አስተንትኖ ሳያበቃ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ጋቦንና ኢትዮጵያ በከሸፈ፣ሱዳን በተሳካ መፈንቅለ መንግስት ተናጡ፣ ወይም ተለወጡ።አፍሪቃ ይጣደፋል፣ ሲጣደፍ ትናንት የሆነዉን ወይም ነገ የሚሆነዉን፣ ዛሬ በሆነዉ ጋርዶ፣ አሁን ላይ  ሲንደፋደፍ ኮሎኔል አሲሚ ጎይታ የመሯቸዉ የማሊ ወታደሮች በዘጠኝ ወር ሁለቴ ባደረጉት መፈንቅለ መንግስት የባማኮን ቤተ መንግሥት ተቆጣጠሩ።ትናንት፣ ኮናክሪ-ጊኒ ሌላ መፈንቅለ መንግስት ተደረገ።ሌላ ጥድፊያ።የጊኒ መፈንቅለ መንግስት መነሻ፣የዓለም ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ማጣቀሺያ፣ የአፍሪቃ ዕዉነት መድረሻችን ነዉ።

ዓለም ይቸኩላል።በርግጥ ዘመኑም-የሚያስቸኩል የቴክኖሎጂ ዘመን ነዉ።የቴክኖሎጂዉ ዋና ባለቤቶች፣ ሐብታሞች፣ የሚቸኩለዉ ዓለም 7ቱ መሪዎች ባለፈዉ ሰኔ ኢንግላንድ-ብሪታንያ ዉስጥ ተሰብስበዉ ነበር።ለፕሬዝደንት ጆ ባይደን የእንኳን ደሕና መጡ፣ለመራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ስንብት፣ ለንግሥት ኤልሳቤት ደግሞ ለቅሶ መድረስ፣ ለቦሪስ ጆንሰን የሊቀመንበርነት ብቃት መመዘኛ የመሰለዉ ያ ጉባኤ፣ ሰዉ ከኮቪድ 19ኝ ጋር በገጠመዉ ትግል አስተማማኝ ድል የመጨበጫዉ ዋዜማም መስሎ፣ በአብዛኛዉ አስደሳች ነበር።

Guinea Conakry | Militärputsch: Bewohner feiern Militäreinheiten
ምስል Souleymane Camara/REUTERS

መሪዎቹም በአካል ሲሰበሰቡ ከሁለት ዓመት በኋላ የመጀመሪያቸዉ በመሆኑ፣ ያዩ እንደዘገቡት ከመሰብሰቢያቸዉ ካርቢስ ባሕርዳርቻ ዉበት፣ለብ፣ነፈስ ካለዉ ዓየር ተስማሚነት ጋር ተዳምሮ አዕምሮን ለቀቅ፣ሰዉነትን መቸት፣ዘና ያደረገ ጉባኤም ነበር።

አፍቓኒስታን የሰፈረዉ የአሜሪካ ጦር እስከ መስከረም ባለዉ ጊዜ ወደ ሐገሩ እንደሚመለስ ፕሬዝደንት ባይደን ያስታወቁት የሰኔዉ ጉባኤ ከመደረጉ ከሁለት ወራት በፊት ነበር።ሚያዚያ።የማሊዉ ኮሎኔል አሳሚ ጎይታ ለሁለተኛ ጊዜ ባደረጉት መፈንቅለ መንግስት የሐገሪቱን የመሪነት ስልጣን የጠቀለሉትም ሚያዚያ ነበር።ከቡድን ሰባት አባል ሐገራት ቢያንስ ሶስቱ ማሊ ዉስጥ ወታደር አስፍረዋል።የቡድን ሰባት አባል ሐገራት መሪዎች በሰኔዉ ጉባኤያቸዉ ማሊን አላነሱም።አፍቓኒስታን ጦር ያላዘመተ የቡድን ሰባት አባል ሐገር የለም።

ሰባቱ መሪዎች በሰኔዉ ጉባኤያቸዉ ማብቂያ ባወጡት የአቋም መግለጫ ከዘረዘሯቸዉ 70 ነጥቦች ቻይና፣ ዩክሬን፣ ቤሎሩስና ኢትዮጵያ ቀደም-ቀደም ባሉ ስፍራዎች ተጠቅሰዋል።አፍቓኒስታንም ተጠቅሳለች ግን 57ኛ ተራ ቁጥር ላይ።በሁለተኛ ወሩ ነሐሴ ታሊባን ካቡልን ሲቆጣጠር ግን የዓለም መሪዎች አፍቓኒስታን-ታሊባንን የድፍን ዓለም የማዐልት-ወሌት «መዝሙር» አደረጉት።

የግብፅ ሕዝብ በብዙ ሺሕ ዘመን ታሪኩ በ2012 ለመጀመሪያ ጊዜ በሰጠዉ ድምፅ መሪዉን መረጠ።መሐመድ ሙርሲ ኢሳ አል አያትን።ባመቱ፣ ፊልድ ማርሻል አብዱል ፈታሕ አል-ሲሲ እሳቸዉን የሾሙ-የሸለሟቸዉን፣ ሕዝብ የመረጣቸዉን  ሙርሲን አስረዉ ሥልጣኑን ጠቅልለዉ ያዙ።ኃምሌ 2013።

Guinea Conakry | Videostill von mutmaßlicher Festnahme von Guineas Präsident Alpha Conde durch Militäreinheiten
ምስል AFP

የአፍሪቃ ሕብረት ያዉ ሕገ-ደንቡ በሚያዘዉ መሠረት የአል-ሲሲ ወታደራዊ ሁንታ የሚገዛትን ግብፅን ከአባልነት አገደ።አል ሲሲ ሥልጣን በያዙ በ8ኛ ወሩ መጋቢት ላይ 4ኛዉ የአፍሪቃ ሕብረትና የአዉሮጳ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ብራስልስ ዉስጥ ተደረገ።የዚምባቡዌዉ ፕሬዝደንት ሮበርት ሙጋቤን ጨምሮ ሶስት የአፍሪቃ ሐገራት መሪዎች ለጉባኤዉ አልተጋበዙም ነበር።የተሰጠዉ ምክንያት ሕዝባቸዉን የሚጨቁኑ ወይም የአዉሮጳ ሕብረት ማዕቀብ የጣለባቸዉ የሚል ነበር።

የአፍሪቃ ሕብረት ማዕቀብ የጣለባት የግብፅ ወታደራዊ ገዢ አብዱል ፈታሕ አል ሲሲ ግን ለጉባኤዉ ሳይሆን «ለሌላ ምክክር» በሚል ወደ ብራስልስ ተጠሩ።በጉባኤዉ እንዲካፈሉ ከተጋበዙ የአፍሪቃ ሐገራት መሪዎች ቀድመዉ ብራስልስ ከገቡት አንዱ የአፍሪቃ ሕብረት፣ ግብፅን ሲያግድ የሕብረቱ የወቅቱ ሊቀመንበር የነበሩት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ነበሩ።

አዉሮጳ ለጥቅሙ ይቸኩላል።አፍሪቃ ጥቅም-ሕግ፣ክብሩን አሳልፎ ለመስጠት ይጣደፋል።ኃያሉ ዓለም ኮቪድ 19ኝ ያለዉ ወረርሺኝ ያደረሰበትን ጉዳት፣ መከላከያ ብልሐት፣ መነሻዉን ለማወቅ ሲቸኩል፣ የአል ሲሲን ስልት-ድርጊት የተከተሉት ኮሎኔል አሲሚ ጎይታ የምዕራብ አፍሪቃዊቱን ደሐ ሐገር የማሊን የመሪነት ሥልጣን ጠቅልለዉ ያዙ።

የሚቸኩለዉ ዓለም፣ለፖለቲካዉ የሚጣደፈዉ አፍሪቃም የማሊን ወታደራዊ ሁንታ አዉግዟል።ማዕቀብም ጥሏልም።ኮሎኔሉ ግን ምናልባት በመፈንቅለ መንግስት የያዙትን ስልጣን አል ሲሲ እንዳደረጉት ሁሉ በምርጫ ለማፀደቅ፣ ምናልባትም አረንጓዴ መለዮአቸዉን በሱፍ ከራቫት ቀይረዉ ለመግዛት እያዘገሙ ነዉ።አፍሪቃ አይደሉም ለድርጊት-ምግባር ያዘግማሉ።

የዓለም ኃያላን ዓለምን አፍቓኒስታን ላይ ሲራያኩቱት፣ ሌላዋ ምዕራብ አፍሪቃዊት ሐገር ጊኒ በሌላ መፈንቅለ መንግስት ተናጠች።ትናንት።

 «ከሰዓት በኋላ ነዉ።እየበላን ነበር።ጥቂት የተኩስ ድምፅ ሰማን።ባልደረቦቼ በሙሉ ፈርተዉ ነበር።ጓደኛዬ ቤተ-መንግስቱ አጠገብ አለዉ ሆቴል ዉስጥ ነበር።ከጠዋቱ ጀምሮ ተኩስ ሲሰማ እንደነበር ነገረኝ።ያመፁ ወታደሮች ሆቴሉን መበርበራቸዉን፣ እዚያ የተሸሸገ ሚንስትር እንደሚፈልጉ ማስታወቃቸዉን ነገረኝ።ግን የተጎዳ አልነበረም።»ትላለች።ኮናክሪ የነበረችዉ ቻይናዊት።

Putschversuch in Guinea - Militäreinheiten auf der Straße gefeiert
ምስል Cellou Binani/AFP/Getty Images

ኮሎኔል ማማዲ ዶዉምቦያ የመሯቸዉ የቤተ-መንግስት ጠባቂ ወታደሮች አብዛኞቹን ሚንስትሮች ከያሉበት እየለቀሙ አሰሩ።ፕሬዝደንት አልፋ ኮንዴ በእስከ ትናንት አንጋቾቻቸዉ ሲያዙ ሸሚዛቸዉን እንኳ ለመቆለፍ ጊዜ አላገኙም።

ትንሺቱ ግን የባሕር ዳርቻይቱ አፍሪቃዊት ሐገር ለአምባገነኖች አገዛዝና ለመፈንቅለ መንግስት እንግዳ አይደለችም።በ1958 ከፈረንሳይ ቅኝ አገዛዝ ነፃ ከወጣችበት ጊዜ ጀምሮ እስከ 2008 ድረስ በነበረዉ 50 ዘመን ከጥቂት ወራት በስተቀር ጊኒን የገዙት ሁለት ሰዎች ናቸዉ።አሕመድ ሴኩ ቱሬ እና ላንሳና ኮንቴ።

ኮንቴ ወታደር ነበሩ።ሁለቱም ስልጣን የያዙት ተመርጠዉ አይደለም።ሁለቱም ስልጣን የለቀቁት ሲሞቱ ነዉ።ኮንቴ በ2008 እንደሞቱ ሻለቃ ሞሳ ዳዲስ ካማራ በመፈንቅለ መንግስት የመሪነቱን ስልጣን ያዙ።በሁለተኛ ዓመቱ በተደረገ ምርጫ ለረጅም ጊዜ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ የነበሩት አልፋ ኮንዴ አሸነፉ።በሕዝብ ድምፅ የተመረጡ የመጀመሪያዉ የጊኒ ፕሬዝደንት ሆኑም።

በ2015 በተደረገዉ ምርጫም በድጋሚ ተመረጡ።የሐገሪቱ ሕገ-መንግስት በሚደነግገዉ መሠረት ኮንዴ ለሶስተኛ ዘመነ-ስልጣን መወዳደር አይችሉም።አፍሪቃ አይደሉ።አምና 82 ዓመታቸዉ ነበር።የዕድሜያቸዉ መግፋት፣ ለአመታት ቀዳሚዎቻቸዉን የማዉገዛቸዉ ሞራል፣ የሕገ-መንግስቱ ደንብም አላገዳቸዉም።አፍሪቃ አይደሉ።ዛሬ ላይ ሲጣደፉ ትናንትን ረሱት፣ ነገንም ጋረዱት።

«ሕጉ እኔን አይመለከትም» አሉ።እምና በተደረገዉ ምርጫ ለሶስተኛ ዘመነ-ሥልጣን «አሸነፉ» አሰኙ።ርዕሠ-ብሔሩ የጣሱትን ሕገ-መንግስት አንጋቻቸዉ የሚያከብርበት ምን ምክንያት አለ?።ኮሎኔል ማማዲ ዶዉምቦያ የ83 ዓመቱን ፕሬዝደንት በሕግም-በዉድም አለቅም ካሉት ወንበር በኃይል አስለቀቋቸዉ።ሕገ-መንግሥቱንም አገዱ።

«ሕገ-መንግስቱን አግደናል።ምክንያቱም ባሁኑ ወቅት ለሁሉም የጊኒ ዜጋ የሚሆን ሕገ-መንግሥት አብረን እናረቅቃለን።እንተባበራለን።የአራቱ ግዛቶች፣ዉጪ ያሉት የጊኒ ተወላጆች ሁላችንም በጋራ ለዚች ሐገር የሚጠቅም ሕገ-መንግሥት እንቀርፃለን።ፖለቲካዊ ሕይወትን የግል ማድረጊያዊ ጊዜ አበቃ።ከእንግዲሕ አንድ ሰዉ ፖለቲካዉን እንዲቆጣጠር አንፈቅም።ፖለቲካ የሁሉም ሕዝብ ነዉ።እስካሁን ያልነበረ ሥርዓት መዘርጋት አለብን።ይሕን ደግሞ በጋራ ማድረግ አለብን።ሁላችንም ጊኒን እየወደድናት፣ ብዙ ሰዎች ያለምንም ምክንያት ሞተዋል። ቆስለዋል።አልቅሰዋል።»

Cornwall G7 Treffen Joe Biden und Angela Merkel
ምስል Jack Hill/REUTERS

አፍሪቃ፣-በ2008 ሻለቃ ሞሳ ካማራ፣ በ2013 ፊልድ ማርሻል አብዱል ፈታሕ አል ሲሲ፣ በ2019 ጄኔራል አሕመድ አዋድ ኢብን አዉፍ (ኋላ በጄኔራል አብዱል ፈታሕ አል ቡርሃን ተቀይረዋል)፣ በመሐሉ ብዙ የከሸፉ መፈንቅለ መንግስቶች፣ በ2020 ኮሎኔል አሲማ ጎይታ፣ በ2001 ኮሎኔል ማማዲ ዶዉምቦያ።አፍሪቃ ወደ 1970ዎቹና 80ዎቹ የመፈንቅለ መንግስት ዘመን እየተመለሰች ይሆን? ጋናዊዉ የፖለቲካ ተንታኝ ኮጂ አሳንቴ «አዎ» ነዉ መልሳቸዉ።

«በመጪው ታኅሣስ ወር ኤኮዋስ ምርጫ እና መልካም አስተዳደርን አስመልክቶ የደረሰበት ስምምነት 20 ዓመት ይደፍናል።ባለፉት አምስት ወራት የሆነውን በእርግጥም ስንመለከት፤ አሁን ጊኒ፣ ቀደም ሲል ደግሞ ማሊ፣ ቻድ፤ በዚያም ላይ ኒዠር ውስጥ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራም ነበር፤ እናም በዚህ አካባቢ የሚገኙ ሁሉ ሊያስተውሉት የሚገባው አንድ ወቅት ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ይደረግበት ወደነበረው የጭለማ ጊዜ እየተመለስን እንደሆነ ነው። በእርግጥም እዚያ ላይ ነው የምንገኘው።»

የጊኒ ወታደራዊ ሁንታ ከትናንት ማታ ጀምሮ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግጓል፤የክፍለ ሐገራት አስተዳዳሪዎችን ሽሯል፣የጊኒን ድንበሮች ዘግቷልም።

መፈንቅለ መንግስቱን ያዉ እንደተለመደዉ የተባበሩት መንሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ፣ የአፍሪቃ ሕብረት፣የምዕራብ አፍሪቃ የምጣኔ ሐብት ማሕበረሰብ (ECOWAS) የጊኒ የቀድሞ ቅኝ ገዢ ፈረንሳይ፣ ዩናይትድ ስቴትስና ሌሎችም ሐገራት አዉግዘዉታል።የኮናክሪ ወጣቶች ግን በጭፈራ-ፌስታ ነዉ የደገፉት።

«ደስታዉ ጫፍ ድረስ ነዉ-ወንድሜ።ተመልከት።በመላዉ ግዛት ተመሳሳይ ደስታ ነዉ።የጊኒ ሕዝብ ነፃ ነዉ።» አለ አንዱ-በአደባባይ በጭፈራዉ መሐል

Kombibild Mali Präsident Assimi Goita und Choguel Maiga

«ለጊኒ ወጣቶች ባጠቃላይ ድል ነዉ።በእዉነት በጣም ተደስተናል።ለጊኒ ጦር፣ ለልዩ ኃይሉ፣ ለሁሉም  ያደረጋችሁት ጥሩ ነዉ እንላለን።ዛሬ ሁሉም ነፃ ነዉ።» ሌለኛዉ ቀጠለ።

ኮንዴ ስልጣን ላይ በነበሩባቸዉ 11 ዓመታት የማዕድን በተለይ የብረት፣የወርቅና የአልማዝ ዋጋ በማሻቀቡ የጊኒ ምጣኔ ሐብት በእጅጉ አድጓል።ከዕድገቱ አብዛኛዉ ተጠቃሚ ግን አንድም ፓሪስ የሚኖሩት፣አለያም ኮንዴ ቤተ-መንግሥት ገባ ወጣ የሚሉት እንጂ ዛሬ ባደባባይ የሚጨፍረዉ ወጣት አይደለም።

ጨፈራዉ ጥድፊያ-ይሁን አይሁን አናዉቅም።አፍሪቃ ይሁን ሌላዉ ዓለም  የፖለቲካ ሥርዓት በተለወጠ ቁጥር በተለይ በኃይል ሲቀየር የሚያዝንና የሚጎዳ  እንዳለ ሁሉ የሚቦርቅም እጅግ ነዉ።የትናንቱ ተረስቷል።የነገዉም አይታወቅም።«ዛሬ ከተስማማሕ ለሞተ ትናንት ወይም ላልተወለደ ነገ ምን አስጨነቀሕ» እንዳለዉ ፈላስፋዉ ይሆን?የጊኒ የተለየ አይደለም።

ነጋሽ መሐመድ 

አዜብ ታደሰ