የጀርመን ጦር ከኩንዱዝ መውጣትና ስጋቱ
ማክሰኞ፣ ጥቅምት 12 2006የጀርመን ወታደሮች ላለፉት 10 ዓመታት ለሰላም ተልዕኮ የዘመቱባትን ሰሜናዊ አፍጋኒስታን የሚትገኘዋን ኩንዱዝን ባለፈው ቅዳሜ ሙሉ በሙሉ ለቀው ወጥተዋል ። ጀርመን የኩንዱዝን እዝ በይፋ ለአፍጋኒስታን የፀጥታ ኃይሎች ያስረከበችው ከ 2 ሳምንት በፊት የጀርመን መከላከያ ሚኒስትር ቶማስ ደ ሜዝየር እና የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጊዶ ቬስተር ቬለ በተገኙበት ስነ ሰርዓት ላይ ነበር ። መከላከያ ሚኒስትር ደ ሜዝየር ሃላፊነቱን የተረከቡት የአፍጋን ኃይሎች የኩንዱዝን ፀጥታ ያስጠብቃሉ የሚል ተስፋ እንዳላቸው በወቅቱ አስታውቀው ነበር ። የጀርመን ጦር ኩንዱዝን ለቆ ወጣ ማለት ደግሞ ደሜዝየር እንዳሉት እስከነአካቴው ይረሳታል ማለት ግን አይደለም ።
« የጀርመን ጦር ዛሬ ከኩንዱዝ ቢወጣም ኩንዱዝን መቼም አንረሳትም ። የጀርመን ወታደሮች እንደ ኩንዱዝ የጎላ ተሳትፎ ያደረጉበት ቦታ የለም ። በኩንዱዝ ገንብተናል ፣ ተዋግተናል አልቅሰናል ተፅናንተናል ሞተናል ወድቀናል »
ኩንዱዝ ውስጥ ብቻ በተካሄዱ ውጊያዎችና በደረሱ ግጭቶች 20 የጀርመን ወታደሮች ተገድለዋል ። በአጠቃላይ አፍጋኒስታን ውስጥ በግዳጅ ላይ ሳሉ የሞቱ የጀርመን ወታደሮች ቁጥር 35 ይደርሳል ። ከ2ተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ጀርመን ይህን ያህል ወታደር ተገድሎባት አያውቅም ። 19 ደግሞ በተለያዩ አደጋዎችና የራሳቸውን ህይወት በማጥፋት እዚያው አፍጋኒስታን ሞተዋል ። የጀርመን ወታደሮች ኩንዱዝ 10 ዓመት እንደመቆየታቸው ነዋሪዎቿ ለምደዋቸዋል ።
ምንም እንኳን ወታደሮቹ የከተማይቱን ጥበቃ ለአፍጋኒስታን ኃይሎች አስረክበው የሚሄዱ ቢሆንም ኩንዱዝን ለቀው መውጣታቸው ለነዋሪዎቿ ከተማይቱን መንግሥትንና አፍጋኒስታን የሰፈሩ ዓለም ዓቀፍ ኃይሎችን ለሚወጉት ለታሊባን አጋልጦ እንደመስጠት ነው የተቆጠረው ። በዚህ ስጋት ምክንያት አንዳንድ ነጋዴዎች ሱቆቻቸውን መዝጋት የጀመሩ ሲሆን አንዳንዶች ደግሞ ወደ ጀርመን ለመሰደድ እየሞከሩ ነው ። ፊኡላህ ሳህል ሰሜን አፍጋኒስታን የምትገኘው የኩንዱዝ ነዋሪ ነው ። ሁሌም ከፍርሃት ጋር የሚኖረው ሳፊኡላህ «አሁን ቢያገኙኝ ደጃፌ ላይ ሊገድሉኝ ይችላሉ » ይላል ። ሳፊኡላህ ሊገድሉኝ ይችላሉ የሚለው የጀርመን ጦር ኩንዱዝን ለቆ ሲወጣ እንደገና ያንሰራራሉ ተብለው የሚፈሩትን ሰርጎ ገቦችና ታሊባኖችን ነው ። ሳፊኡላህ ሳህል አፍጋኒስታን ለዘመተው የጀርመን ጦር እየተከፈላቸው ከሚሰሩ አፍጋናውያን አንዱ ነው ። ታሊባኖች እንደ ፊኡላህ አፍጋኒስታን ውስጥ ለጀርመኖች የሚያገለግል ማንኛውንም ሰው እንደ አገር ከሃዲ ነው የሚቆጥሩት ። እጎአ ከ 2006 ዓም አንስቶ ለጀርመኖች የሚሰራው ሳፊኡላህ እንደሚለው ታሊባኖችና ሌሎችም ሰርጎ ገቦች ለጀርመን ጦር የሚሰሩ አፍጋናውያን ይሰልላሉ ጥቃትም ያደርሱባቸዋል ። በዚህ የተነሳም በበኩሉ ከፍተኛ ጥንቃቄ ነው የሚያደርገው ።
«ኩንዱዝ ውስጥ ያን ያህል ብዙም ጥቃት በማይደርስበት በከተማዋ ማዕከል ብቻ ነው የምንቀሳቀሰው ። ከከተማ ለመውጣት ግን አልተማመንም ። ከከተማይቱ ወጣ ያሉ ቀበሌዎችም አደገኛ ናቸው ። አማፅያኑ ኩንዱዝ ውስጥ ለጀርመኖች የሚሰሩ አፍጋናውያንን ይሰልላሉ አደጋም ይጥሉባቸዋል ። እኔን ቢያገኙኝ ምናልባትም ደጃፌ ላይ ይገድሉኝ ነበር ። ሆኖም ሁሌም በመጠንቀቅ ለቤተሰቦቼ እንኳን የት እንደምሄድ ነግሬያቸው አላውቅም ። ያም ሆኖ ከፍርሃት ጋር ነው የምኖረው »
እንደ ሳህል ሁሉ አፍጋኒስታን ለዘመተው የጀርመን ጦር የሚሰሩ አፋጋናውያን ቁጥር ወደ 1500 ይደርሳል ። እነዚህ አፋጋውያንም በዋነኛነት ለጀርመን ጦር በአስተርጓሚነት በሾፌርነት በምግብ አብሳይነት እና በፀጥታ አስከባሪነት ነበር የሚሰሩት ። የጀርመን መንግሥት ከመካከላቸው አፍጋኒስታን ቢቆዩ ለአደጋ ይጋለጣሉ ተብሎ የሚታሰቡትን ሰራተኞች ለመርዳት ቃል ገብቷል ። የጀርመን የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሃንስ ፔተር ዲትርሽ ቃል እንደገቡት መንግሥታቸው ማንንም ለአደጋ አጋልጦ አይሰጥም ። አፍጋናዊያኑ ሰራተኞች የጀርመንን ጦር በመርዳታቸው ምክንያት ለችግር የሚዳረጉ ከሆነ ወደ ጀርመን እንዲመጡ እንደሚደረግ ነው ሚኒስትሩ ያስታወቁት ። ይሁንና የጀርመን የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ የፀጥታ ጉዳዮች ቃል አቀባይ ኦሚድ ኑሪፑር መንግሥት ጉዳዩን የያዘበትን መንገድ ይተቻሉ ።
« ብዙ ነገሮች በተሳሳተ መንገድ እየተከናወኑ ነው ። በመጀመሪያ ደረጃ ከለላ ሲሊሰጣቸው የሚገባ ሰዎችን የመቀበል ብዙ ምልክት አይታይም ። ሁሉም ከለለላ አያስፈልጋቸውም ሆኖም የሚያስፈልጋቸውን መውሰድ ይገባል ። በነገራችን ላይ ቤተሰቦቻቸውንም እንዲሁ ። የምንነጋገረው በቁጥር ጥቂት ስለሆኑ ሰዎች ነው ። በአፍ መሸንገል ብቻ ውጤት አያመጣም ። ሰዎች አደጋ ላይ የሚገኙትን ሰዎች መቀበል እንዳለብን በግልፅ ሊታወቅ ይገባል ። »
የጀርመን ፌደራል መንግሥት የእያንዳንዱን ጉዳይ በየተራ ይመረምራል ። ወደ ጀርመን መምጣት የሚፈልጉ መጀመሪያ ማመልከቻ ማስገባትና ራሳቸውም ሆነ ቤተሰባቸው ለአደጋ መጋለጣቸውን እዚያ ለሚገኑ አለቆቻቸው ማሳመን ይኖርባቸዋል ። ኑሪፐር እንደሚሉት ይህን መሰሉ ጥርጣሬ የተሞላበት አሠራሩ ጊዜ የሚወስድና የተንዛዛም ነው ። ብርጋድየር ጀነራል ሚሸል ፌተር ወደ ጀርመን መሄድ የሚገባቸውንና እዚያ መቅረት የሚችሉትን የሚወስነው ኮሚቴ ሃላፊ ናቸው ። በተለይ ጦሩ ኩንዱዝን ለቆ ሲሄድ ሥራ ላጡት በሌላ አካባቢ በሚገኙ ክፍት የሥራ ቦታዎች የማሰማራት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ይናገራል
«በዚህ ኮሚቴ ውስጥ የውጭ የሃገር ውስጥ ጉዳይ ና የመከላከያ ሚኒስቴር ተወካዮችም ይገኛሉ ። በአጠቃላይ እነዚህን በሃገር ውስጥ ይሰሩልን የነበሩ ሰዎችን ማቆየት መቻል አለመቻላችንን የመገምገም ግብ አለን ። በኩንዱዝም ይህን አድርገናል ። በኩንዱዝ ስራቸውን ያጡ ሰዎች አሉ ። እነዚህ ሰዎች በሌሎች አካባቢዎች ለምሳሌ በማሳር ኢሻሪፍ ክፍት የሥራ ቦታዎች እንዲፈለግላቸው ይደረጋል »
አፍጋኒስታን ውስጥ ለጀርመን ጦር ሲሰሩ የቆዩ ጦር ጋር ይሰሩ ከነበሩት መካከል አፍጋኒስታን ውስጥ አሁን የጀርመን ጦር አካባቢውን ለቆ ሲወጣ የደፈጣ ተዋጊዎችና የታሊባን ኃይሎች ሰለባ መሆናችን አይቀርም የሚለው ስጋታቸው ጨምሯል ። በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም እንዲሁ ፍርሃት ነግሶባቸዋል ። ዶቼቬለ ያነጋገራቸው አብዱላህ ራሶሊ ያለ ጀርመን መከላከያ ሠራዊት ሥራችንን ማስፋፋት አንችልም ነው ያሉት ። በርሳቸው አስተያየት ከኩንዱዝ ወጣ ብለው በሚገኙ ቀበሌዎች ታሊባኖች የበላይነቱን እንደያዙ ነው ። በነዚህ አካባቢዎች የታጠቁ የወንጀለኞች ቡድኖች ይንቀሳቀሳሉ ። የጀርመን የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደሚናገረው እስካሁን 289 አፍጋናውያን ለህይወታቸው እንደሚሰጉ ማመልከቻ አስገብተዋል ። ከመካከላቸው የ275 ቱ ጉዳይ ታይቷል ከነዚህም 173 ቱ በእጅጉ ለአደጋ የተጋለጡ መሆናቸው ታውቋል ። ከነዚህም 23 ቱና ቤተሰቦቻቸውን ጀርመን እንደምትቀበል ቃል ተገብቶላቸዋል ። የተቀሩት 150ው ደግሞ በቅርቡ ወደ የጀርመን መንግሥት እንደሚቀበላቸው የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል ። ሰዎቹ ባለቤቶቻቸውንና ልጆቻቸውንም ይዘው ወደ ጀርመን መምጣት ይችላሉ ። ምንም እንኳን የጀርመን ወታደሮች ኩንዱዝን ለቀው መውጣት ብዙዎችን ቢያሰጋም ፀጥታው ሊሻሻል ይችላል ብለው ተስፋ የሚያደርጉ አልጠፉም ። ከነዚህ አንዱ ኩንዱዝ የሚገኝ የባህልና ስነ ፅሁፍ ተቋም ሃላፊ ናቸው ። በርሳቸው አስተያየት የጀርመን ወታደሮች ሲወጡ ለውጭ ጦር ጥላቻ ያላቸው ኃይሎች ውጊያ ሊቆሙ ይችላሉ ።
ሂሩት መለሰ
አርያም ተክሌ