1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን የውጭ ንግድ ይዞታ

ረቡዕ፣ ጥር 5 2002

በዓለም ላይ ቀደምቱ የነበረው የጀርመን የውጭ ንግድ በዓለምአቀፉ የፊናንስና የኤኮኖሚ ቀውስ የተነሣ በሰፊው አቆልቁሏል። ይህም በመስኩ “የዓለም ሻምፒዮን” ስትባል የቆየችው ጀርመን የመሪነት ቦታዋን እንድታጣ ነው ያደረገው።

https://p.dw.com/p/LV1V
የሃምቡርግ ወደብ
የሃምቡርግ ወደብምስል picture-alliance/ dpa

ያለፈውን 2009 ዓ.ም. አስመልክቶ በወቅቱ በቀረቡ መረጃዎች መሠረት የኤኮኖሚ ዕድገት መንኮራኩር የሆነችው ቻይና በውጩ ንግድ ጀርመንን አልፋ ተራምዳለች። የጀርመን የውጭ ንግድ ወደ ቀድሞ ጥንካሬው ለመመለስ ጥቂት ዓመታት መፍጀቱ ስለማይቀርም ቻይና ቢቀር ለተወሰነ ጊዜ ወይም ለዘለቄታው ግንባር ቀደም ሆና ልትቀጥል የምትችል ነው የሚመስለው። የጀርመን የውጭ ንግድ ሁኔታ ምን ይመስላል? የቻይና አይሎ መገኘትስ እንዴት ነው የሚታየው?

የጀርመን ኤኮኖሚ በዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ ሳቢያ ብርቱ ማቆልቆል ነው የደረሰበት። ለግንዛቤ ይህል በተለይ የጀርመንን ያህል በውጭ ገበዮች ላይ ጥገኛ የሆነ አገር የለም። ከአጠቃላዩ ብሄራዊ ምርት ግማሽ የሚሆነው በውጩ ንግድ ላይ ጥገኛ ነው። እናም በጤናማ የኤኮኖሚ ወቅቶች የአገሪቱ ጥቅም ምን ያህል ከፍተኛ እንደሆነ መገመቱ አያዳግትም። ጀርመን በ 2008 ዓ.ም. ብቻ አንድ ቢሊዮን ኤውሮ ገደማ የሚያወጣ ምርት ወደ ውጭ ለመላክ በቅታ ነበር። ሩቡ የአገሪቱ ሠራተኛ የተሰማራው በዚሁ ዘርፍ የምርት ተግባር ላይ ሲሆን ከሶሥት አንዱ ኤውሮ የሚገኘውም እንዲሁ ከውጩ ንግድ ነው። ጀርመንን በዓለምአቀፉ ንግድ ላይ በተለይም የኢንዱስትሪ ማምረቻ መኪናዎቿ፣ የንጥረ-ነገር ምርቶቿና ታዋቂ አውቶሞቢሎቿ ቁንጮ አድርገው አቆይተዋታል። እርግጥ በዓለምአቀፉ ንግድ ስኬታማ የሆኑት መለስተኛ ኩባንያዎችም ጭምር እንጂ ታላላቅ የኢንዱስትሪ ዘርፎች ብቻ አይደሉም።

የሆነው ሆኖ የጀርመን ኢንዱስትሪ ፌደራል ማሕበር በዘርፉ ባካሄደው መጠይቅ መሠረት በፊናንሱና በኤኮኖሚው ቀውስ ሂደት የውጩ ንግድ በመላው የምርት ዘርፎች ነው ያቆለቆለው። ይሄውም በዓመት 18 ከመቶ ገደማ ይጠጋል። ለማነጻጸር የጀርመን ኢንዱስትሪዎች የውጭ ንግድ ከቀውሱ በፊት ስምንት ከመቶ ዕድገት የታየበት ነበር። የኢንዱስትሪው ማሕበር ፕሬዚደንት ሃንስ-ፔተር-ካይትል እንደሚሉት የውጩ ንግድ በዚህ ዓመት በዝግታ ወይም በጥቂቱ የሚያገግም ሲሆን ወደነበረበት ለመመለስ ግን ብዙ ጊዜ መጠየቁ የማይቀር ነው። ከዘርፉ በኩል በዚህ በአዲሱ 2010 ዓ.ም. የአራት ከመቶ ዕድገት ይጠበቃል። ከቀውሱ በፊት ከነበረበት ደረጃ ግን ከ 2014 ወዲህ ይደረሳል ተብሎ አይታመንም። በወቅቱ የጀርመን የውጭ ንግድ ከተከታታይ ሰባት ዓመታት ግንባር ቀደምነት በኋላ “የዓለም ሻምፒዮን” የሚል ቅጽል መጠሪያውን ለቻይና አስረክቧል። 2009 በዚህ ረገድ የቻይና ዓመት ነበር።

መረጃዎችን ለመጥቀስ ያህል በ 2009 ዓ.ም. ጀርመን 734 ሚሊያርድ ኤውሮ የሚያወጣ ምርት ወደ ውጭ ስትሸጥ የቻይና ድርሻ በዚሁ ጊዜ በ 12 ሚሊያርድ የላቀ ሊሆን በቅቷል። ከሰባት ዓመታት መሪነት በኋላ ቀደምቱን ቦታ መልቀቁ ቀላል ነገር ባይሆንም አንዳንድ የጀርመን የንግድ ዘርፍ ተጠሪዎች ተበለጥን-አልተበለጥን ያን ያህል ዋጋ የለውም ባዮች ናቸው። ከነዚሁም መካከል በሻንግሃይ የጀርመን የንግድ ም/ቤት አመራር ዓባል ኡልሪሽ ሜደር ይገኙበታል።

“ፈጽሞ አስፈላጊ አይደለም። ቻይና 1,3 ሚሊያርድ ሕዝብ አላት። እኛ ደግሞ 80 ሚሊዮን ነን። ከዚሁ ሌላ ጀርመን ጽኑ የኤኮኖሚ ፖሊሲ ሲኖራት በእኔ አመለካከት በዓለም ላይ ከሁሉም የተረጋጋችው ናት። እናም ነገሩን አጨልሞ ማየት ጨርሶ አስፈላጊ አይመስለኝም። አሁን በንግዱ ስፋት አንደኛ ሆንን ሁለተኛ በመሠረቱ የረባ ሚና አይኖረውም”

ጀርመን አብዛኛውን የአገሪቱን ምርት የምትሸጠው ለአውሮፓ ሕብረት አገሮች ነው። የዚሁ ድርሻም 57 ከመቶ ገደማ ይጠጋል። አሥር በመቶው የጀርመን ኢንዱስትሪ ምርት ደግሞ ከሕብረቱ ውጭ ወደሆኑ ሰርቢያንና ኡክራኒያን ወደመሳሰሉት የምሥራቅና ደቡብ-ምሥራቅ አውሮፓ አገሮች የሚሄድ ሲሆን እነዚህም በዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ ክፉኛ የተጎዱት ናቸው። እነዚህ አገሮች ከዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቋም፣ ከአውሮፓ ሕብረትና ከዓለም ባንክ ያገኙት ዕርዳታ ፍቱንነት በዚህ ዓመትም ቀስተኛ እንደሚሆን ነው የሚጠበቀው። ሥራ-አጥነትና የብድር እጦት ችግሩን እንደሚያከብደው ይታመናል።

ከአውሮፓ ሌላ አሜሪካና እሢያም የጀርመን ኢንዱስትሪ ምርት ገበዮች ናቸው። ከጀርመን ኢንዱስትሪ ምርት አሥር ከመቶው ወደ አሜሪካ የሚላክ ቢሆንም የኤኮኖሚው ቀውስ ሁኔታውን እያከበደው መሄዱ አልቀረም። የአሜሪካ ኤኮኖሚ ባለፈው ዓመት ሶሥተኛ ሩብ ላይ ቀስ በቀስ ቢያገግምም በጥቅሉ በዓመቱ ሂደት ግን በሶሥት ከመቶ ገደማ ነበር ያቆለቆለው። ዕድገቱ በተለይ ከጠቅላላው የአገሪቱ ብሄራዊ ምርት ከሶሥት ከመቶ በላይ ከሚሆነው የኤኮኖሚ ማነቃቂያ ዕቅድ ወጪ የተገኘ ነበር። የአሜሪካ ሥራ-አጥ ቁጥርም ባለፈው ጥቅምት ወር ወደ 10,2 ከመቶ ከፍ ብሎ ታይቷል። ይሄውም ባለፉት 25 ዓመታት ከፍተኛው መሆኑ ነበር። ሁኔታው ለጀርመን የውጭ ንግድ ብዙም አመቺ አይደለም።
ጀርመን ለላቲን አሜሪካ አገሮች የምትሸጠው ምርት መጠን ደግሞ 2,4 ከመቶ ሲሆን አካባቢው ባለፉት ዓመታት ከፍተኛ ዕድገት የተመዘገበበት ነበር። ከቀውሱ በፊት በነበሩት አምሥት ዓመታት ውስጥ በአማካይ የስድሥት ከመቶ ዕድገት ታይቷል። ይሁንና የፊናንሱ ቀውስ በላቲን አሜሪካ ኤኮኖሚ ላይም ተጽዕኖ ማድረጉ አልቀረም። የአካባቢው አጠቃላይ ብሄራዊ ምርት በተገባደደው 2009 ዓ.ም. ከሁለት በመቶ በላይ ነው የወደቀው። የጀርመን ኢንዱስትሪ ፌደራል ማሕበር በቅርቡ ያወጣው ዘገባ እንዳመለከተው 13 ከመቶው የአገሪቱ ምርት የሚሸጠው በአዳጊው የእሢያ አካባቢ ገበዮች ላይ ነው። ከነዚሁ ዋነኛዋ ቻይና በቀውሱም ወቅት፤ ባለፉት ሁለት ዓመታት ዘጠኝ ከመቶ ገደማ የሚጠጋ ዕድገት ማድረጉ አልተሳናትም።
የአገሪቱ ኤኮኖሚ እንዳያቆለቁል በጣሙን የረዳው እርግጥ በኤኮኖሚ ማረጋጊያው ዕቅድ የወጣው ከጠቅላላው ብሄራዊ ምርት ስምንት በመቶ የሚሆን ግዙፍ ገንዘብ ነው። ጥረቱ ግቡን መትቷል ለማለት ይቻላል። ቻይናና መሰሎቿ ቀውሱን ከምዕራባውያኑ አገሮች በተሻለ ሁኔታ ነው የተቋቋሙት። በሌላዋ የእሢያ የኤኮኖሚ መንኮራኩር በሕንድም እንዲሁ በ 2009 አምሥት ከመቶ ዕድገት ታይቷል። እርግጥ ቻይናና ጀርመን በኤኮኖሚው ቀውስ ሂደት በአንድ ላይ 18 ከመቶ የውጭ ንግድ አቅማቸውን ቢያጡም ቻይና አሁንም፤ ወደፊትም ተፎካካሪ ብቻ ሳትሆን ማራኪ ገበያም ናት። የታላቁ የጀርመን ንጥረ-ነገር ኩባንያ የ BASF የእሢያ ዘርፍ ሃላፊ ማርቲን ብሩደርሙለር ከጥቂት ቀናት በፊት እንዳረጋገጡት!

“ለኛ ዋነኛዋ ገበያ ቻይና ናት። ገና ከዛሬው 50 በመቶ ገደማ የሚጠጋው የእሢያ የንጥረ-ነገር ምርት ገበያ የሚገኘው እዚህ ነው። የቻይና ድርሻ በሚቀጥሉት ዓመታትም እንደገና ያድጋል። ገበያው ካለፉት ዓመታት ዕድገት አንጻርም ቢሆን በአገሪቱ ከፍተኛ ዕርምጃ የታየበት ነበር። ከዚህ አንጻር በቻይናና በሕንድ መካከል ያለው ልዩነት ይሰፋ እንደሆን እንጂ የሚጠብ አይሆንም”

በጀርመን የውጭ ንግድ መካከለኛ ምሥራቅና አፍሪቃ ደግሞ ሶሥት ከመቶውን ድርሻ ይይዛሉ። መጠኑ ከሌሎቹ የዓለም አካባቢዎች ሲነጻጸር ዝቅ ያለ ቢሆንም እነዚሁ ሃገራት በመጪዎቹ ዓመታት የበለጠ ትኩረት እንደሚሰጣቸው ነው የዘርፉ ተጠሪዎች የሚናገሩት። በዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ ሳቢያ ባለፈው ዓመት የጥሬ ዕቃ ዋጋ ቢወድቅም አካባቢው ጥቂትም ቢሆን ዕድገት ለማስመዝገብ ችሏል። ሆኖም ጀርመን በ 2008 ሁለት በመቶ ምርቷን ወደ አፍሪቃ ስትልክ በጥቅሉ ይሄው በተከታዩ ዓመት በ 16 ከመቶ ነው ያቆለቆለው። ለጀርመን ዋነኛዋ የንግድ ዒላማ ለሆነችው ለደቡብ አፍሪቃ ብቻ የሚቀርበው ምርትና አገልግሎት እንዲያውም በ 28 ከመቶ ቀንሷል።
ይህ የጀርመን የውጭ ንግድ ማቆልቆል የሚያሳየው የደቡብ አፍሪቃን የኤኮኖሚ ዕድገት ችግርም ነው። ባለፈው ዓመት እንደሆነው ሁሉ በዚህ ዓመትም በደቡብ አፍሪቃ የሚጠበቀው ዕድገት ቢበዛ በሁለት ከመቶ የተወሰነ እንደሚሆን ነው የሚገመተው። ይህ ሁሉ ተደምሮ ለጀርመን የውጭ ንግድ መጪዎቹ ዓመታት ቀላል የሚሆኑ አይመስልም። እርግጥ የጀርመን ኢንዱስትሪ የውጭ ንግድ በዚህ በአዲሱ ዓመት ስድሥት ከመቶ ዕድገት ሊያሳይ እንደሚችል የዘርፉ ተጠሪዎች ማመናቸው አልቀረም። የአገሪቱ ኤኮኖሚም ሁለት በመቶ ዕድገት እንደሚያሳይ ነው የተተነበየው። ይሁን እንጂ ያለፈው ዓመት የትንበያ ውጣ-ውረድ ሲታሰብ ግን አስተማማኝ ነገር መጠበቁ በጣሙን ያዳግታል። እናም እንደ ጀርመን የሙያ ማሕበራት ፌደሬሺን ተጠሪ እንደ ሚሻኤል ዞመር ሁሉ ተጠራጣሪዎቹ ጥቂቶች አይደሉም።

“የአገሪቱ የምጣኔ-ሐብት ምርምር ተቋማት ከቀዉሱ በፊት፣ በቀውሱ ወቅትና በሂደቱ ያደረጉትን ትንበያ በሎተሪ ትክክለኛ ከመሆኑ ዕድል ጋር ስለማመሳስል የተባለውን መቀበሉ ይከብደኛል”

ለማንኛውም የንግዱ በቀድሞው መጠን መልሶ ማበብ በጠቅላላው የዓለም ኤኮኖሚ መነቃቃት ላይ ጥገኛ እንደሚሆን አንድና ሁለት የለውም። ይህ ደግሞ በምን ፍጥነት እንደሚከሰት ቀድሞ መናገሩ ለጊዜው የሚከብድ ነው። በሌላ በኩል በዓለም ላይ የንግዱን ቀደምትነት የያዘችው ቻይና የምዕራቡ ኢንዱስትሪዎች የዕቃ መጣያ ወይም ማምረቻ ስፍራ የመሆን ገጽታዋን ለመቀየር ብርቱ ዕርምጃ ማድረጓን ቀጥላለች። በከፍተኛ ቴክኖሎጂ ምርቶችን ለማውጣት በያዘችው ጥረት ከአሁኑ ታላቅ ዕርምጃ ማድረጓን ዛሬ ቀደምቱ አገሮች ራሳቸው ይመሰክራሉ። እንግዲህ ትራንስ-አትላንቲኩ የአውሮፓና የአሜሪካ የቴክኖሎጂ ልዕልናም የማይናቅ ተፎካካሪ እያደገበት ነው። ምናልባት የቻይና የውጭ ንግድ የበላይነት ጸንቶ መቀጥልም እንዲሁ!

መስፍን መኮንን/DW

አርያም ተክሌ