የጀርመን የምክር ቤት አባል በዚምባብዌ
ሰኞ፣ ሚያዝያ 22 2004የጀርመን ምክር ቤት የደቡባዊ አፍሪቃ የልማት ማህበረሰብ የወዳጅነት ቡድን ኋላፊ እሽቴፈን ሊቢሽ እንደተናገሩት በዝምባዌ ትክክለኛ እና ነፃ ምርጫ እንዲካሄድ የደቡብ አፍሪቃው ፕሬዚደንት ጃኮብ ዙማ በፕሬዚደንት ሮበርት ሙጋቤ ላይ ጫና ማድረግ እንደሚገባቸው አሳሰቡ።
የጀርመን ምክር ቤት የደቡባዊ አፍሪቃ የልማት ማህበረሰብ የወዳጅነት ቡድን ልዑካን መሪ እሽቴፈን ሊቢሽ የጀርመን ምክር ቤት የውጭ ጉዳዮች ኮሜቴ አባልም ናቸው። ጀርመንን የደቡብ አፍሪቃ ችግር የተንሰራፋባቸው ሀገሮች ሁኔታ እንዳሳሰባት አስታውቀዋል። ሊቢሽ እንዳሉት በአህጉሪቷ በአጠቃላይ ዲሞክራሲ እንዲሰፍን የአፍሪቃ መሪዎች ትልቅ ሚና መጫወት እንደሚኖርባቸው፣ የአለም አቀፉ የፖለቲካ ስምምነት በምህፃሩ GPA በተግባር ላይ እንዲውል በተለይ የደቡብ አፍሪቃው ፕሬዚደንት ጃኮብ ዙማ ተጠያቂ ናቸው ብለዋል። ይህን ስምምነት የዝምባዌ ባለስልጣናት እኢአ 2009 ዓም በዝምባዌ ስልጣንን ለተለያዩ ወገኖች ያከፋፈለ መንግስት እንዲመሰረት ሲባል ፈርመዋል። እንደ ሊቢሽ የደቡብ አፍሪቃው ፕሬዚደንት ጃኮብ ዙማ ፤ የዝምባዌ ባልደረባቸው ሮበርት ሙጋቤን መቆጣጠር ይችላሉ። « አቶ ዙማ በሳዴክ ስር ዝምባዌን በተመለከተው የአለም አቀፉ የፖለቲካው ስምምነት ተግባራዊ የሚሆንበትን መንገድ የመፈለግ ኃላፊነት አለባቸው። እንደሚመስለኝ ባለፊት ወራት ሲፈፅሙት ከነበረው በላይ መስራት አለባቸው። በቅርቡ በአዲሱ ህገ መንግስት ላይ ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድና ትክክለኛ እና ነፃ ምርጫ የሚካሄድበት ቀን እንዲቆረጥ ጫና ማድረግ የሚኖርባቸው ይመስለኛል። ያንን ነው ዝምባዊያን ማግኘት ያለባቸው። ይህ መብት በብዙ የአለማችን ሀገሮች አለ። የዝምባዌ ህዝብ ለትክክለኛ እና ነፃ ምርጫ እራሱ መወሰን መቻል አለበት።»
የመጨረሻው የዝምባዌ ምርጫ የተካሄደው እኢአ በ2008 ነው። ምርጫው አመፅ እና ግፅት ያየለበት እንዲሁም የጠቅላይ ሚኒስትር ሞርገን እስቫንጋሪ ፓርቲ 200 አባላትን ህይወት ያስከፈለ ነበር። በመጨረሻም ፕሬዚዳንት ሙጋቤ ምርጫውን ማሸነፋቸውን አስታወቁ። ውጤቱን ያልተቀበለው ሳዴክ ጥምር መንግስት እንዲመሰረት ግፊቱን አጠናከረ። የሳዴክ አባል አገራት መሪዎች ቀጣዩ የዝምባዌ ምርጫ አዲሱ ህገ መንግስት ስራ ላይ ከዋለ በኋላ ምርጫ እንዲካሄድ መረለጋቸውን ሲያስታውቁ ይህን መልስ ነው ከፕሬዚዳንት ሙጋቤ ያገኙት።« በዚህ አመት ምርጫዎች ማካሄድ ይኖርብናል። ምርጫዎቹ ህገ መንግስት ኖረም አልኖረም መካሄድ ይኖርባቸዋል። ችግሩ ምን እንደሆነ ለ ሳዴክ እናሳውቃለን። ሳዴክ እርባነ ቢስ ሙከራ እንድናደርግ ሊነግረን አይችልም።»
እሽቴፈን ሊቢሽ ለዝምባዌ አዲስ ህገ መንግስት የመንደፍ ሂደቱ የተሳካ እንዲሁን የደቡብ አፍሪቃው ፕሬዚደንት ጃኮብ ዙማ እንዲያረጋግጡ ይፈልጋሉ። የአካባቢው ባለስልጣናት ዙማ ጥንካሬ በሌለው የዝምባዌ መንግስት ተጣማሪዎችን እንዲሸመግሉ ጠይቀዋል። ዝምባዌን ከጎበኙ በኋላ የጀርመን የምክር ቤት ልኡክ ወደ ጎረቤት አገር ዛምቢያ ነው ያመሩት። በዛምቢያ ደግሞ ተቃራኒ ሁኔታ ነው ያስተዋሉት።
«በዛምቢያ ያለ አንዳች ግጭት የስልጣን ሽግግር ተካሂዷል። ይህ ለአፍሪቃ አህጉር ጥሩ ምሳሌ ይሆናል ብለን እናስባለን። እንዲሁ ለሳዴክ ክፍሎችም ለውጥ ያለ ግጭት ሊካሄድ እንደሚችል ያሳያል።»
እሽቴፈን ሊቢሽ በምሳሌነት ያነሱት ባለፈው አመት መስከረም ወር በዛምቢያ የተካሄደውን ምርጫ ነበር። በዚሁ ምርጫ ማይክል ሳታ ፕሬዚዳንት ሩጲያ ባንዳን በምርጫ አሸንፈው ስልጣን ይዘዋል። በርካታ የአለም አቀፍ ድርጅቶች ምርጫው የህዝቡን ፍላጎት ያንፀባረቀ እንደነበር ተናግረዋል።
ልደት አበበ
ሂሩት መለስ