የጀርመን ውህደትን የዘክረው ታላቁ ሩጫ
በቀበና አካባቢ የተካሄደው ውድድር
የጀርመን ውህደት 25ኛ አመት ክብረ በዓል መስከረም 22 ቀን 2008 ዓ.ም. በኢትዮጵያ በሩጫ ውድድር ተከብሯል በውድድሩ 3,000 ወጣቶችና 150 ወጣት ሯጮች ተካፍለዋል። ውድድሩ አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴ ከመሰረተው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ነበር።
አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴ ከውድድሩ ተሳታፊዎች ጋር
በሁለት የእድሜ ምድብ ተከፍሎ የተካሄደው ውድድር መነሻውን የጀርመን ኤምባሲ ከሚገኝበት ቀበና በማድረግ ወደ መገናኛና አቧሬ አደባባዮች የተከናወነ ነው።
የጦፈው የታዳጊዎች ፉክክር
በመድረኩ የተገኘው አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴ በውድድሩ የጀርመንን ውህደት በደመቀ መልኩ በከበሩ የተሰማውን ደስታ ገልጾ ለኢትዮጵያ ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት እንደሚጠቅምም አስረድቷል።
ውድድርና መዝናኛ
በክብር እንግድነት የተገኙት በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ዮአኺም ሽሚት በውድድሩ የተሳተፉት ታዳጊዎች የሁለቱን አገሮች መጻኢ ግንኙነትና መነሳሳት እንደሚወክሉ ተናግረዋል። አምባሳደሩ ጀርመን የኢትዮጵያ ስፖርቶችን በተለያዩ መንገዶች በማስተዋወቅ ላይ እንደምትገኝም ጠቁመዋል።
ወደ አሸናፊነት
አራት ኪሎ ሜትር የሚሸፍነውን ውድድር ካሸነፉት ታዳጊዎች አንዷ የ15 አመቷ ቤተልሄም ዘሪሁን ነበረች። ቤተልሄም ወደ ፊት በዓለም አቀፍ መድረኮች ኢትዮጵያን በመወከል ስኬታማ መሆን እንደምታልም ተናግራለች።
የበርሊን ማራቶን ተሳትፎ ግብዣ
የውድድሩ አሸናፊዎች በጎርጎሮሳዊው 2016 ዓ.ም. በሚደረገው የበርሊን ማራቶን የተሳትፎ ግብዣ ተበርክቶላቸዋል። ታዳጊዎቹ በበርሊን ማራቶን ለሚኖራቸው ተሳትፎ የሚያስፈልጋቸው ወጪ በሙሉ በሽልማቱ የሚሸፈን ይሆናል።
እንኳን ደስ አለህ!
የጀርመን ውህደት በአገሪቱ በየዓመቱ በብሄራዊ በዓልነት በድምቀት ይከበራል። በኢትዮጵያ በሩጫ ውድድር በተዘከረው በዚህ በዓል የኢትዮጵያ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አብዲሳ ያደታ ታድመዋል።
ከገንዘቤ ዲባባ ሽልማቷን የተቀበለችው ወጣት
በ3,000ና 5,000 ሜትር ክብርን የተጎናጸፈችው አትሌት ገንዘቤ ዲባባ በውድድሩ ከታደሙት መካከል ትገኝበታለች። ውድድሩ በመዘጋጀቱ ደስተኛ ነኝ ያለችው ገንዘቤ «ለታዳጊዎችና ለተተኪዎች እድል ይፈጥራል።» ስትል ተናግራለች።
ሽልማት ከአምባሳደሩ እጅ
ቅዳሜ መስከረም 22 የተከበረው በዓል ምስራቅና ምዕራብ ጀርመን በይፋ የተዋሃዱበት 25ኛ አመት ነው። በዓሉ በጀርመን የፍራንክፈርት ከተማ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በተገኙበት በድምቀት ተከብሯል። እንደ አዲስ አበባው የሩጫ ውድድር ሁሉ በመላው ዓለም በተለያዩ ዝግጅቶች ታስቧል።
አምባሳደር ዮአኺም ሽሚት
በውድድሩ መዝጊያ ንግግር ያደረጉት በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ዮአኺም ሽሚት «ከእናንተ ጋር ሩብ ምዕተ ዓመት ያስቆጠረውን የጀርመን ውህደት በዓል ስናከብር ቀኑ ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ ትገነዘቡታላችሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።» ሲሉ ተናግረዋል።