1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን ተጣማሪ መንግሥት ውዝግብ

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 23 2008

ጦርነትና ጭቆና ከሃገራቸው ያፈናቀላቸው በሺህዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች በየቀኑ ወደ አውሮፓ መጉረፋቸው ቀጥሏል ። የብዙዎቹ ምርጫም ጀርመን ናት ። ሆኖም በሥልጣን ላይ ያለው የጀርመን ተጣማሪ መንግሥት ፓርቲዎች ፣ ተገን ጠያቂዎች በብዛት ወደ ሃገሪቱ በሚገቡበት መንገድ ላይ መስማማት አልቻሉም ።

https://p.dw.com/p/1Gyrs
Berlin Bundeskanzleramt Seehofer Gabriel Merkel Koalition OVERLAY
ምስል picture-alliance/dpa/W. Kumm

ከቅርብ ወራት ወዲህና አሁንም ወደ አውሮፓ የመጣውና የሚመጣው ተገን ጠያቂ ቁጥር እጅግ እየጨመረ ነው ።ብዙዎቹም በአደገኛ የባህር ጉዞ ነው ወደ አውሮፓ የሚሰደዱት ። ምንም እንኳን የኃይለኛው ክረምት መግቢያ በተቃረበበት በዚህ ወቅት ላይ በአነስተኛ ጀልባዎች የባህር ጉዞ ባይደፈርም የአውሮፓ ድንበር ይዘጋል በሚል ፍራቻ ህይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠው በባህር የሚሰደዱት ቁጥር በብዙ በእጥፍ አድጓል ። ከአውሮፓ በኤኮኖሚ እድገት ግንባር ቀደሙን ስፍራ የምትይዘው ጀርመን ከቅርብ ወራት ወዲህ ደግሞ የበርካታ ስደተኞችና ተገን ጠያቂዎች መድረሻ በመሆን ከክፍለ ዓለሙ አንደኛውን ቦታ አግኝታለች ። ካለፉት 3 ወራት አንስቶ እስከ ጎርጎሮሳዊው 2015 መጨረሻ ድረስ ጀርመን ይገባል ተብሎ የሚጠበቀው ተገን ጠያቂ ቁጥር 800 ሺህ ሊደርስ እንደሚችል ነበር የሚነገረው ።የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል በቅርቡ በተካሄደው የአውሮፓ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ እንዳረጋገጡት ግን በዚህ ጊዜ ውስጥ በባልካን ሃገራት በኩል በዚህ ጊዜ ውስጥ ወደ ጀርመን የገባውና ወደፊትም የሚገባው ተገን ጠያቂ ቁጥር በአጠቃላይ እስከ 1 ሚሊዮን ሊደርስ ይችላል። በጀርመን ተገን የሚጠይቀው ስደተኛ ቁጥር ከተጠበቀው በላይ እየጨመረ መሄድ ጀርመን ውስጥ ያስነሳው ክርክርና ውዝግብ ተባብሶ ቀጥሏል ። ጦርነት ግድያና ጭቆናን የሚሸሹ ስደተኞች ወደ ጀርመን በብዛት መግባት እንደጀመሩ ፣ሃገሪቱ በሯን ለስደተኞች ክፍት በማድረጓን ብዙዎች ድጋፋቸውን ገልፀው ነበር ።ሆኖም እየዋለ ሲያድር ቁጥራቸው ከተገመተው በላይ መሆኑ እና በአንዳንድ አካባቢዎችም በቂ ዝግጅት ሳይደረግ መግባታቸው በመራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ላይ ጠንካራ ትችቶችን ማሰንዘሩ ቀጥሏል ። ከፓርቲያቸውና ከተጣማሪው መንግሥት ፓርቲዎች በኩልም ጫናው እንዲበረታባቸውም አድርጓል ።ተገን ጠያቂዎች በብዛት የሚገቡባት የደቡብ ጀርመንዋን ፌደራዊ ግዛት የባቫርያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆርስት ዜሆፈር ፣ ሜርክል እስካለፈው እሁድ ድረስ የጀርመንን ድንበር ክፍት ያደረገውን የፖለቲካ መርሃቸውን እንዲያነሱና ተገን ጠያቂዎችም ጀርመን መቆየት መቻል አለመቻላቸው ድንበር ላይ በአስቸኳይ ውሳኔ እንዲያገኝ እንዲደረግ ጠይቀው ነበር ። የጀርመን ሶሻል ክርስቲያን ህብረት ፓርቲ በምህፃሩ CSU መሪ ዜሆፈር በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ጥያቄአቸው ካልተመለሰም ፓርቲያቸው አስቸኳይ ያላቸውን እርምጃዎች እንደሚወስድም አስጠንቅቀውም ነበር ። በዚህ መነሻነትም ከ2 ዓመት በፊት ተጣማሪ መንግስት የመሠረቱት የክርስቲያን ዲሞክራት ህብረት ፓርቲ CDU ፣ የክርስቲያን ሶሻል ህብረት ፓርቲCSU እና የሶሻል ዲሞክራቶቹ ፓርቲ SPD መሪዎች ከትናንት በስተያ እሁድ በጉዳይ ላይ ንግግር አካሂደው ነበር ። ይሁንና ከCSU በኩል በቀረቡት ጥያቄዎች ላይ ሁሉም አልተስማሙም ። በዚህ የተነሳም የCDU ፓርቲ መሪ አንጌላ ሜርክል ፣የCSU ው ሊቀመንበር ኽርስት ዜ ሆፈርና የSPD ው መሪ ዚግማር ጋብርየል ስምምነት ባልተደረገባቸው ጉዳዮች ላይ ሐሙስ እንደገና ለመወያየት ሌላ ቀጠሮ ይዘዋል ።አንጌላ ሜርክል የሚመሩት የክርስቲያን ዴሞክራት ህብረት ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አርሚን ላሼት እስከ ሐሙስ መፍትሄ ላይ ለመድረስ ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል ።

Serbien Mazedonien Flüchtlinge bei Preshevo
ምስል Reuters/O. Teofilovski
Griechenland Flüchtlinge auf Lesbos
ምስል Reuters/Y. Behrakis

« ጀርመን የሚገቡትን ተገን ጠያቂዎች ቁጥር ለመቀነስ ና በሌላ በኩል ከለላ የሚያስፈልጋቸውንም ለመቀበል አንድ መፍትሄ ላይ መድረስ ይኖርብናል።ስለዚህ ከሶሻል ዲሞክራቶች ጋር ለመፍትሄ ፍለጋው ሰኞ ማክሰኞ ረቡዕን ተጠቅመን ጊዜ ወስደን እንመክርበታለን »

የሦስቱ ፖርቲዎች መሪዎች እሁድ ባካሄዱት ንግግር መግባባት ላይ ካልደረሱባቸው ጉዳዮች አንዱና ዋነኛው በተለይ ስደተኞች በሚገቡባቸው ድንበሮች ላይ ቁጥጥር የሚደረግበት ለጊዜው የሚያርፉበት የሽግግር ጣቢያ ይቋቋም የሚለው ሃሳብ ነው ። የሜርክል ቃል አቀባይ ሽቴፈን ዛይበርት እንዳሉት ከCSU በኩል የቀረበው ይኽው ሃሳብ ተገን ጠያቂዎች በሚገቡባቸው የጀርመን ድንበሮች በአውሮፕላን ማረፊያና መነሻ ጣቢያዎች ያለው ዓይነት የኢሚግሬሽን ቁጥጥር እንዲደረግና ተገን ማግኘት የሚያስችሉ መስፈርቶችን ያላሟሉትን ስደተኞችም ወዲያውኑ ለመመለስ የሚያስችል አሠራር እንዲዘረጋ ይጠይቃል ።ይህም በሐሙሱ ስብሰባ ውይይት ከሚካሄድባቸው ጉዳዮች አንዱ ነው ። ይህን ሃሳብ የሶሻል ዲሞክራቶቹ ፓርቲ SPD አልተቀበለውም ። ጊዜያዊ ጣቢያዎቹን እጅግ ገዳቢ የሚለው SPD ከዚያ ይልቅ በ16ቱ የጀርመን ፌደራዊ ግዛቶች የተገን ጠያቂዎች መመዝገቢያና ማስተናገጃ ማዕከላት እንዲቋቋሙ ሃሳብ አቅርቧል ። በጀርመን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የእህትማማቾቹ የክርስቲያን ዴሞክራት ህብረት CDU ና የክርስቲያን ሶሻል ህብረት የCSU ፓርቲ ተወካዮች ሊቀ መንበር ፎልከር ካውደር በጉዳዩ ላይ በሰጡት አስተያየት አሁን ትኩረት የተሰጠው ጀርመን ድንበሯን መዝጋት አለመዝጋትዋ ሳይሆን የአውሮፓን ዳር ድንበር የማስከበሩ ሃላፊነት ነው ይላሉ ።

Österreich Spielfeld Grenze Slowenien Flüchtlinge Zaun
ምስል picture-alliance/PIXSELL

« ‘ድንበር መክፈትወይምድንበር መዝጋትእንደ አማራጭ ቀርቦም አያውቅም ።ከዚያ ይልቅ የአውሮፓን የውጭ ድንበሮች ማስከበር እንደሚገባን ሁሌም የምናነሳው እና ወደፊትም ተግባራዊ ማድረግ አለማድረጋችን በአውሮፓ ቅድሚያ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ነው ።ስለዚህ አውሮፓ የውጭ ድንበሩን የማስጠበቅ ሃላፊነቱን መወጣት ይኖርበታል ።በዚሁ ላይ እኛም መወሰድ ያለባቸውን ዝርዝር እርምጃዎች አስቀምጠናል ። ወደ ኛ የሚጎርፈውን ስደተኛ አቀባበል ስርዓት ማስያዝና ማስተካከል ይገባናል ። ሃገሪቱን ለቀው መውጣት ያለባቸውም እንዲሁ መሄድ አለባቸው ።»

Slowenien Österreich Flüchtlinge bei Sentilj
ምስል Reuters/S. Zivulovic

CDU CSU በእሁዱ ንግግራቸው ሙሉ ጥገኝነት ያላገኙ ስደተኞች የቤተሰብ አባላት ለሁለት ዓመት ወደ ጀርመን እንዳይመጡ ለማገድ ፣በብዛት የሚገባውን ስደተኛ ለመቆጣጠር የጀርመን ፖሊስ ከኦስትሪያ ፖሊስ ጋር እንዲተባበር ተስማምተዋል ።ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ታይቶ የማይታወቅ የተባለውን አውሮፓን ያስጨነቀውን በብዛት የሚመጣውን ስደተና ለመግታት ጀርመን በቅርብ ሳምንታት ውስጥ የተለያዩ እርምጃዎችን ወስዳለች ።ከመካከላቸው አልባንያ ሞንቴኔግሮና ኮሶቮን ከመሳሰሉ ሃገራት ለመጡ ስደተኞች የፖለቲካ ተገን መስጠት እንዲቀር ወይም እንዲገደብ እና የተገን ጥያቄአቸው ውድቅ የተደረገባቸውም በአስቸኳይ እንዲባረሩ የሃገሪቱ ምክር ቤቶች ያሳለፏቸው ውሳኔዎች ይገኙበታል ።ከዚህ ሌላ ባለፈው አርብ ጀርመን ወደ ሃገርዋ የሚመጡ ስደተኞች ከኦስትርያ ወደ ጀርመን መግባት የሚችሉባቸውን አምስት የድንበር መተላለፊያዎች ለይታለች ። ጀርመንን ከኦስትርያ ጋር በሚያዋስነው 800 ኪሎ «ሜትር ርዝመት ባለው የሁለቱ አገራት ድንበር በኩል ፣ኦስትሪያ ካለ አንዳች ማስጠንቀቂያ ስደተኞችን ወደ ጀርመን በመልቀቅዋ ሁለቱ ሃገራት ተቃቅረው ነበር የከረሙት።በቅርቡ ከኦስትሪያ ጋር በተደረሰበት ስምምነት መተላለፊያዎቹ መወሰናቸው በብዛት የሚመጣውን ስደተኛ በተሻለ ሁኔታ ለመቆጣጠር እንደሚረዳ ታምኖበታል ። ስደተኞችን በሥርዓት ለማስተናገድ የሚወሰዱት እነዚህን የመሳሰሉት እርምጃዎች ቢደገፉም ጉዳያቸው ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት ያላገኘ ተገን ጠያቂዎች ቤተሰቦች እንዳይመጡ ለማገድ ስምምነት ላይ መደረሱ ግን ተቃውሞ ገጥሞታል ። በጀርመን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተቃዋሚው የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ የህዝብ እንደራሴዎች ሊቀ መንበር ጎሪንግ ኤካርት ይህ ስምምነት አደጋ ማስከተሉ አይቀርም ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

እህትማማቾቹ ፓርቲዎች ከውዝግቡ በኋላ አሁን ይፋ እንዳደረጉት ከሁሉም በላይ ቤተሰብ እንዳይመጣ ገደብ አድርገዋል ። ያ ማለት ተጨማሪ ሰዎች ደህንነታቸው ባልተረጋገጠ ጀልባዎች በመጥፎ የአየር ንብረት ከልጆቻቸው ጋር በባህር ጉዞ ወደ አውሮፓ ለመምጣት ይሞክራሉ ማለት ነው ።አንዳንድ ሰዎች እንደነገሩኝ ብዙዎቹ አሁን ወደ አውሮፓ የሚመጡት የአውሮፓ ድንበር ይዘጋል ፤ዜሆፈር የሚባሉ ሰው ስለዚህ ጉዳይ ይናገራሉ ሲባል ስለሰማን ነው ይላሉ ። በዚህ ምክንያት ነው ብዙ ሰዎች አሁን ወደ አውሮፓ የሚመጡት ።በበኩሌ ሰዎች ህፃናት ቤተሰቦች ሜዴትራንያን ባህር ውስጥ እንዲሰጥሙ ይህ መሰሉን ሃላፊነቱን ከነርሱ ጋር መውሰድ አልፈልግም ።ይህ ለአውሮፓ አሳፋሪ ነው ። »

ስደተኞች በባህር ጉዞ መሞቸው የወደፊቱ አሳሳቢ ጉዳይ ብቻ አይደለም ።አሁንም ከሶሪያና ፣ጦርነት ና ግጭት ካመሰቃቀላቸው ሌሎች ሃገራት በቱርክ አድርገው ወደ ግሪክ ደሴቶች በአነስተኛ ጀልባዎች ለመሻገር ሲሞክሩ ብዙዎች መንገድ ላይ የውሃ ሲሳይ ሆነው እየቀሩ ነው ። ባለፈው እሁድ እንኳን በጀልባ ከቱርክ ወደ ግሪክ ለመሻገር ከሞከሩ ስደተኞች መካከል የ15 ቱ ህይወት አልፏል ። የተመ የስደተኞች ጉዳይ መርጃ ከፍተና ኮሚሽን UNHCR ባለፈው ሳምንት እንዳስታወቀው ሊገባደድ ከሁለት ወር ያነሰ ጊዜ በቀረው በጎርጎሮሳዊው ጥቅምት 2015 በሜዴትራንያን ባህር በኩል ወደ አውሮፓ ለመጓዝ ሲሞክሩ የሞቱ ና የደረሱበት ያልታወቀ ስደተኞች ቁጥር ወደ 3440 ይጠጋል ። ድርጅቱ እንዳለው እድል ቀንቷቸው በጎርጎሮሳዊው ጥቅምት 2014 ብቻ ፣የሜዲቴራንያንን ባህር አቋርጠው ወደ አውሮፓ የገቡት ስደተኞች ቁጥር ደግሞ ከ218 ሺህ በልጧል ። ይህም በጎርጎሮሳዊው 2014 በተመሳሳይ መንገድ ወደ አውሮፓ ከመጡት ቁጥር ጋር እንደሚስተካከል ነው ድርጅቱ የተናገረው ። ካለፈው ዓመት ጥር እስከ አለፈው መስከረም ድረስ ጀርመን የገባው ተገን ጠያቂ ቁጥር ደግሞ 577 ሺህ ይደርሳል ።ወደ ጀርመን የሚገባው ስደተኛ ቁጥር ከተጠበቀው በላይ መጨመር ሥልጣን ከያዙ ከሳምንታት በኋላ 10 ዓመት የሚሞላቸውን መራሂተ መንሥት አንጌላ ሜርክልን አጣብቂኝ ውስጥ ከቷል ። ለሐሙስ የታቀደው ድርድር በጀርመን ተጣማሪ መንግሥት አባላት በCDU SCU እና SPD መካከል በተገን ጠያቂዎች ጉዳይ የተፈጠረውን መከፋፈል ያስወግድ አያስወግድ ከወዲሁ ለመገመት ያስቸግራል ።ሆኖም በውይይቱ አንድ አግባቢ ነጥብ ላይ ይደረሳል የሚል ተስፋ አለ ።

China Bundeskanzlerin Angela Merkel in Hefei
ምስል picture-alliance/AP Photo/J. Eisele

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ