1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዶ/ር አቢይ አህመድ ማንነት

ሐሙስ፣ የካቲት 22 2010

ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደስ አለኝ የስልጣን መልቀቅያ ደብዳቤ ካስገቡ በኋላ የኢትዮጵያ ገዥ ፓርቲ ኢህአዴግ በምትካቸዉ አዲስ ሊቀመንበርና አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመምረጥ በዝግጅት ላይ መሆኑ እየተነገረ ነዉ። ፓርቲዉ ለያዝነዉ ሳምንት የጠራዉ ስብሰባ ወደሚቀጥለዉ ሳምንት ሳይሸጋገር እንዳልቀረ ተዘግቧል።

https://p.dw.com/p/2tXkz
Dr. Abiy Ahmed
ምስል DW/S. Teshome

ዶ/ር አቢይ አህመድ ማን ናቸዉ?

 

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያምን ይተካሉ ተብለዉ ከሚገመቱት ፖለቲከኞች አንዱ ባለፈዉ ሳምንት ኃሙስ የኦሮሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት የ«ኦህዲድ» ፕሬዚዳንት ሆነዉ የተመረጡት ዶ/ር አቢይ አህመድ ናቸዉ። ዶክተር አብይ አህመድ፤ በሃገር መከላከያ ሠራዊት የሌተና ኮሎኔልነት ማዕረግ የደረሱ ፤ በሚኒስትርነትም ያገለገሉ ናቸዉ። አቢይ  ማንነት የሚቃኝ አጭር ዘገባ አለን። 

ዶ/ር አቢይ አህመድ የኦሮሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት የ«ኦህዲድ» ፕሬዚዳንት ሆነዉ እንደተመረጡ የተዜመላቸዉ ሙዚቃ ነበር። በ1968 ዓ,ም ጅማ ዞን አጋሮ ወረዳ የተወለዱት ዶ/ር አብይ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸዉን በአጋሮና ጅማ ከተሞች ተከታትለዋል። በመቀጠል በተለያዩ የሃገር ዉስጥና የዉጭ ሃገራት ዩንቨርስቲዎች  እስከ PHD የሚያደርስ ትምህርታቸዉን አጥንተዋል። ዶክተር አብይ አህመድ በተካኑት የንግግር ስጦታቸዉና የአድማጭን ቀልብ ከመሳብና ቅቡልነት አቅም ሌላ በቂ የፖለቲካ ብቃት እንዳላቸዉ በበደቡብ ኢትዮጵያ ኮንሶ ከተማ በጥርስ ህክምና የሚያገለግሉት ዶ/ር መንግስቱ አሰፋ ተናግረዋል። መምህርና የድረገፅ ፀሐፊዉ አቶ ስዩም ተሾመ በበኩላቸዉ ዶክተር አቢይ በዓለም አቀፍ ደረጃም ተፅኖ መፍጠር የሚችል ችሎታ እንዳላቸዉ አምናለሁ ብለዋል።  

«ሊሰመርበት የሚገባዉ ነገር ሁለት ምርጫ የለንም ያለን ምርጫ መደመር ብቻ ነዉ»  ዶ/ር አብይ አህመድ ከ 1980 ዎቹ ጀምሮ የኦህዴድ አባል ናቸዉ። ከ 2002ዓ,ም ጀምሮ የ«ኦህዲድ» ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ከ 2007 ዓ,ም ጀምሮ የ«ኦህዲድ» ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል በመሆን እያገለገሉ ናቸዉ። ከዚህ ሌላ ዶ/ር አቢይ በሃገር መከላከያ ሰራዊት የሌተናኮነሪልነት ማዕረግንም ተቀብለዋል።  የመንግሥታቱ ድርጅት የሰላም አስከባሪ አባል ሆነዉ ሩዋንዳ ኪጋሊ ላይ የተመድ ተልእኮ አገልግለዋል። ዶ/ር አብይ ጠ/ሚር ሆነዉ ቢሾሙ በኢትዮጵያ የሚታየዉን የፖለቲካ ቀዉስ ለመፍታትና ማኅበረሰቡን ለማረጋጋት ምን ያህል ሚና ይጫወቱ ይሆን ? ዶ/ር መንግሥቱ አሰፋ ጥርጣሪ አላቸዉ፤

መምህር ስዩም ተሾመ በበኩላቸዉ ዶ/ር አቢይ አህመድ የፖለቲካዉን ቀዉስ ለመፍታት ፓርቲዉ ምቹ ሁኔታን ይፈጥርላቸዉ ይሆን ? ሲሉ ጥያቄዉን በጥያቄ ይመልሳሉ።

ዶ/ር አቢይ  በጅማ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ሆነዉ፤ የብሔራዊ መረጃ መረብ « ኢንሳ» መስራችና ዋና ዳይሬክተር የሳይንስና ቴክኖሎጂ መረጃ ማዕከል ዳይሬክተር በመለጠቅ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር እንዲሁም  ከ 2008 ዓ,ም ጀምሮ የኦሮሚያ ከተሞችና ከተማ ልማት ቢሮ ኃላፊ ሆነዉም አገልግለዋል። ዶ/ር አቢይ አህመድ ለኢህአዴግ በተለይ ለህዉሃት ባለስልጣናት አጎብዳጅ ናቸዉ ከሚባሉት ከጠ/ሚ ኃይለማርያም ደስአለኝ ይለዩ ይሆን? የሃገርን ጉዳይ በተመለከተ ዶክተር አቢይ አህመድ አንድ ወቅት ይህን ተናግረዉ ነበር።                         

«ይህ ሃገር የወረስነዉ ሃገር አይደለም ብለናል። ከአባት ከናት የወረስነዉ ሳይሆን ከልጆቻችን የተዋስነዉ ሃገር ነዉ። ዉርስ መሸጥ መለወጥ ይቻላል ትዉስት ግን አጥቦ አጽድቶ የሚመለስ ነገር ነዉ። አሳምረን ማሸጋገር አለብን። » የሃገርን ጉዳይ በተመለከተ ዶ/ር አቢይ አንድ ወቅት እንዲህ ተናግረዉ ነበር። ለኢትዮጵያ  ፖለቲካ  ቅርበት ያላቸዉ የሃገሪቱ መከላከያና የደኅንነት መዋቅር በህዋሃት የበላይነት ሥር መሆኑን ይናገራሉ። ዶ/ር አቢይ ወደ ጠ/ሚሩ ሥልጣን  ቢመጡ የኢህአዴግ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ማሻሻያ እንደሚያደርግ የገባዉን ቃል ተግባራዊ ያደርጋሉ ተብሎ ይታመን ይሆን? ሙሉ እንብሩን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉ።

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ