የዶቼ ቬለ መታፈንና የኢትዮጵያ መንግሥት
ዓርብ፣ መጋቢት 30 200308 04 11
የዶቼ ቬለ የአማርኛ ሥርጭት ባለፉት ጥቂት ቀናት ዉስጥ አልፎ አልፎ ግን ሆን ተብሎ እየታፈነ ወይም ጃም እየተደረገ መሆኑንን የጣቢያዉ የቴክኒክ ባለሙያዎች አስታወቁ።የሥርጭቱን አድማስና ጥራት የሚከታተሉት የቴክኒክ ባለሙያዎች እንዳሉት የአማርኛዉ ዝግጅት የሚሠራጩባቸዉ የሞገድ መስመሮች በፈረቃ በሚመስል መልኩ እየታፈኑ ነዉ።ዶቸ ቬለ እርምጃዉን ተቃዉሞታል።የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ግን ስርጭቱ ሆን ተብሎ ሥለመታፈኑ የምናዉቀዉ ነገር የለም ብለዋል።ነጋሽ መሐመድ ዝር ዝር ዘገባ አለዉ።
የተለያዩ አድማጮች ከተለያዩ አካባቢዎች በላኳቸዉ የSMS መልዕክቶች የዶቸ ቬለ ሥርጭት አንዳዴ ሙሉ በሙሉ፥ ሌላ ጊዜ በከፊል፥ አልፎ አልፎ እያሰለሰ እንደሚታፈን፥ ወይም በስርጭቱ መሐል ያልተለመደ ባዕድ ረባሽ ድምፅ እንደሚገባበት በተደጋጋሚ እያስታወቁን ነበር።የዶቸ ቬለ የሥርጭትና የሞገድ መስመሮች ጥራት ክፍልም ይሕኑ ነዉ ያረጋገጠዉ።
የክፍሉ የቴክኒክ ባለሙያዎች ባደረጉት ክትትል መሠረት ቢያንስ በሁለት የሞገድ መስመሮች የሚተላለፈዉ የአማርኛ ሥርጭት ሆን ተብሎ መታፈኑ ወይም መታወኩ ተረጋግጧል።የቅርቡ አብነት የትናንቱ ሥርጭት ነዉ።የቴክኒክ ክፍሉ እንዳረጋገጠዉ ትናንት ከተለያዩ የማሰራጪያ ሞገዶቻች አንዱ ከ11 ሠዓት ከ14 ደቂቃ እስከ 11 ሠዓት 38 ደቂቃ ድረስ፥ ሁለተኛዉ ደግሞ ከ11: 14 ደቂቃ እስከ 11 ከ33 ደቂቃ ድረስ ታፍኖ ወይም ጃም ተደርጎ ነበር።
ስርጭቱ የሚታፈነዉ ወይም የሚታወከዉ ከኢትዮጵያ አካባቢ እንደሆነ ባለሙያዎቹ ጠቁመዋል። የዶቸ ቬለ የፕሮግራሞች የበላይ ሐላፊ ክርስቲያን ግራምሽ የኢትዮጵያ መንግሥት የዶቸ ቬለ ሥርጭት ከእወካ ነፃ መሆኑን እንዲያረጋግጥ ጠይቀዋል።
«ይሕ አዲሱ እርምጃ ዶቸ ቬለ ሚዛኑን የጠበቀ ፖለቲካዊ፥ ምጣኔ ሐብታዊ እና ማሕበራዊ ጉዳዮችን የሚዳስስ መረጃ ለኢትዮጵያና ለአካባቢዋ አድማጮች እንዳያሰራጭ ያደናቅፈዋል።ሥለዚሕ የኢትዮጵያ መንግሥት የዶቸ ቬለ የአጭር ሞገድ መስመሮች ከእወካ ነፃ መሆናቸዉን እንዲያረጋግጥ እጠይቃለሁ።»
የዶቸ ቬለ የአማርኛ ሥርጭት ሆን ተብሎ ሲታፈን ወይም ሲታወክ ያሁኑ የመጀመሪያዉ አይደለም። በቅርቡ ብቻ በሁለት ሺሕ አመተ-ምሕረት ለተከታታይ ወራት እና ባለፈዉ አመት ግንቦት ወር አካባቢም ታፍኖ ነበር።በዚያን ወቅት ለደረሰዉ አፈና ለፕረስ ነፃነት የሚሟገቱ ወገኖች ባንድ ወይም በሌላ መልኩ የኢትዮጵያ መንግሥትን ወቅሰዉ ነበር።
የኢትዮጵያ መንግሥት የያኔዉን ወቀሳ አልተቀበለዉም ነበር።አሁንም የኢትዮጵያ የመገናኛ ወይም የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መስሪያ ቤት ምክትል ሐላፊ አቶ ሽመልስ ከማል «ዶቸ ቬለ አልታወከም» ብለዋል።
የዶቼ ቬለ የቴክኒክ ባለሙያዎች እንደሚሉት ሰሞኑን የደረሰዉ አፈና፥ እወካ ወይም ጃሚንግ ከዚሕ ቀደም ከደረሰዉ ጋር ተመሳሳይ ነዉ።የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ምክትል ሐላፊ አቶ ሽመልስ ከማል ግን መጀመሪያ አጣሩ ነዉ ያሉት።
ዶቸ ቬለ የአማርኛዉን ሥርጭት ከሚያዚያ ሁለት 2003 በ17780 ኪሎ ሔርዝ በ16 ሜትር ባነድ ወይም በ11 835 ኪሎ ኸርዝ ወይም በ25 ሜርትር ባንድ ማድመጥ ትችላላችሁ።
ነጋሽ መሐመድ
ሒሩት መለሰ