የዴሞክራቲክ ኮንጎ ሬፓብሊክ የፀጥታ ሁኔታ
ቅዳሜ፣ ሐምሌ 7 2004
በኮንጎ ያለው ሞንዩክ በሚል መጠሪያ የሚታወቀው የተመ ሰላም አስከባሪ ሠራዊት ወታደሮች አሁን በዚሁ አካባቢ ኅልውናውን ቢያጠናክርም፡ አሥራ አንድ የምሥራቅ እና ማዕከላይ አፍሪቃ ሀገራት፡ ኮንጎ እና ርዋንዳ ጭምር፡ ይህ በቂ አለመሆኑን በማመልከት፡ ዓማፅያኑን የሚደመስስ ዓለም አቀፍ የጦር ኃይል እንዲቋቋም ጥሪ አቅርበዋል። አዲሱ ተዋጊ የጦር ኃይል ካካባቢው ሀገራት የሚውጣጡ ወታደሮችን የሚያጠቃልልና በተመድ የሚረዳ እንዲሆን ለአፍሪቃ ህብረት ስብሰባ በአዲስ አበባ የተገኙት የሀገራቱ ውጭና መከላከያ ሚንስትሮች በአዲስ አበባ ባለፈው ሐሙስ ተስማምተዋል።
የዴሞክራቲክ ኮንጎ ሬፓብሊክ ፕሬዚደንት በጦር ወንጀል የሚፈለጉት የቀድሞው ጀነራል ቦስኮ ንታንጋንዳ ተይዘው ወደ ዴን ኻግ ፍርድ ቤት እንዲላኩ ከጠየቁ በኋላ ነበር ያማፂው ቡድን M23 ባለፈው ሚያዝያ ወር ንታንጋንዳን ለመደገፍ በተነሳሱ ከኮንጎ ጦር በከዱ ቱትሲ ወታደሮች የተቋቋመው። ዓማፅያኑ ከዩጋንዳ ጋ በሚያዋስነው ድንበር አካባቢ ያለውን ቡናጋንን ላጭር ጊዜ በያዙበት ወቅት ብዙ ያካባቢው ነዋሪዎች ወደ ዩጋንዳ በመሸሻቸው፡ ርዳታ የማቅረቡ ተግባር አዳጋች መሆኑን በዚያ የሚገኘው ድንበር የማይገድበው የሀኪሞች ድርጅት የጀርመን ቅርንጫፍ ኃላፊ ፍራንክ ደርነር አስታውቀዋል። አቅርቦቱ ተግባር
« እኛ ርዳታ እያቀርብን ባለንበት የዩጋንዳ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ከ 10.000 የሚበልጡ የሚገኙ ሲሆን፡ ማስተናገድ ከሚገባው በላይ ተጨናንቆ ይገኛል። »
በተለይ በሰሜን ኪቩ ርዕሰ ከተማ ጎማ የፀጥታው ሁኔታ ከፍተኛ ውጥረት የሚታይበት ሲሆን፡ አልፎ አልፎም የተኩስ ልውውጥ ይሰማል። ለደህንነታቸው የሰጉት ይህንኑ ያማፂ ቡድን የጎረቤት ርዋንዳ መንግሥት ይረዳል በሚል አንድ የተመድ ከጥቂት ጊዜ በፊት ዘገባ ካወጣ ወዲህ በከተማይቱ ነዋሪዎችና በዚያ በሚኖሩ የርዋንዳ ዜጎች መካከል ውጥረት ተካሮዋል። በምሥራቃዊ ኮንጎ የሚታየውን ከፍተኛ የርዋንዳ ተፅዕኖን በመቃወም ሰሞኑን አደባባይ የወጡት የጎማ ነዋሪዎች ርዋንዳውያኑን ከሀገር እንዲወጡ ጠይቀዋል።
« እኛ የኮንጎ ዜጎች እውነቱን ለመናገር አያስፈራንም። ዓማፅያኑ ከጎረቤታችን ርዋንዳ ድጋፍ ያገኛሉ። »
ርዋንዳ ለ M23 ዓማፅያን አንዳችም ርዳታ ትሰጣለች መባሉን የርዋንዳ ፕሬዚደንት ፖል ካጋሜ በማስተባበል፡ ይህንኑ በተመለከተ የተመድ ጠበብት ያወጡት ዘገባ አንድን ወገን ብቻ አናግሮ የተጠናቀረ ሀቁን ያላንፀባረቀ ዘገባ ነው በሚል አጣጥለውታል።
ፊሊፕ ዛንድነር/አርያም ተክሌ
መሥፍን መኮንን