የደቡብ ሱዳን ነፃነት 3ተኛ ዓመት
ረቡዕ፣ ሐምሌ 2 2006ማቻርም ከአዲስ አበባ የሰላሙ ንግግር እንዲቀጥል እንደሚፈልጉ ተናግረዋል ። በጁባው በዓል ላይ ከተገኙት እንግዶች መካከል የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ይገኙበታል ። ለ7 ወራት የዘለቀው የደቡብ ሱዳን የርስ በርስ ጦርነት መፍትሄ ሳያገኝ በርካታ ዜጎችም ለረሃብ እንደተጋለጡ የተከበረው የደቡብ ሱዳን ሶስተኛ ዓመት የነፃነት በዓል የብዙ ዜጎችን ትኩረት አልሳበም ። በዓሉን ምክንያት በማድረግ የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ባሰሙት ንግግር አማፅያን ትጥቃቸውን ፈተው ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበዋል ። ሪክ ማቻር ደግሞ ከአዲስ አበባ በሰጡት መግለጫ ለሃገሪቱ ችግር ሰላማዊ መፍትሄ እንዲፈለግ ለመነጋገር ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል ።ኪር በጁባው በዓል ላይ የተገኙትን የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒንም አመስግነዋል ። የደቡብ ሱዳን ሰላም አስተማማኝ እስኪሆን ድረስ የኡጋንዳ ወታደሮች ጥበቃ ለማድረግ እንደሚቆዩም ተናግረዋል ።
የዛሬ 3 ዓመት ዕውን ለሆነው ለደቡብ ሱዳን ነፃነት መንገዱን የጠረገው የሱዳን መንግሥትና የሱዳን ህዝቦች ነፃ አውጭ ንቅናቄ በምህፃሩ SPLM እጎአ በ2005 የተፈራረሙት የሰላም ስምምነት ነው ። ይሁንና መቀመጫውን ለንደን ያደረገው ቻተም ሃውስ የተባለው የጥናት ተቋም ባልደረባ ጄሰን ሞስሊ ለዶቼቬለ እንደተናገሩት ሂደቱ ብዙ ጉዳዮችን ወደ ጎን ትቶ በማለፉ ሃገሪቱ አሁን የምትገኝበት ችግር ውስጥ ከቷታል ። በርሳቸው አስተያየት የሰላም ስምምነቱ ስያሜው የሚያመለክተውን ተግባር አለማከናወኑ ነው መሠረታዊው ችግር ።
« አጠቃላዩ የሰላም ስምምነት ስሙ እንደሚያመለክተው በየአካባቢው በሚንቀሳቀሱ ቡድኖችና በማዕከላዊ መንግሥት መካከል የሚካሄዱ ግጭቶችን ሁሉ አይጨምርም ።የዳርፉር ግጭትም ሆነ በምሥራቅ ሱዳን ያለው ሁኔታ በሂደቱ አልተነሳም ።ስምምነቱም በደቡባዊ ሱዳን የሚገኙ ወገኖችን በሙሉ አላካተተም ።ከዚያ ይልቅ ያተኮረው በዋነኛውን የአማፂ ቡድን ላይ ብቻ ነው ።»
የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎችን በማግባባት በሃገሪቱ ሰላም ለማውረድ አዲስ አበባ ውስጥ በኢጋድ ሸምጋይነት ሲካሄድ የቆየው የሰላም ንግግር እንደተቋረጠ ነው ።ሁለቱ ወገኖች ከዚህ ቀደም የተፈራረሟቸው የተኩስ አቁም ስምነቶችም አልፀኑም ። ለውጊያው አለመቆም ና ለሰላሙ ንግግር መደናቀፍ አንዳቸው ሌላኛቸውን ተጠያቂ ማድረጋቸውን ቀጥሏል ። በበዓሉ ዋዜማ ተሰናባቿ በደቡብ ሱዳን የተመድ ተጠሪ ሂልደ ጆንሰን በሰጡት መግለጫ የሃገሪቱን ባለሥልጣናትና አማፅያንንም ራሳቸውን ብቻ የሚጠቅሙ በሙስናም የታመሙ ሲሉ ወቅሰዋቸው ነበር ። የደቡብ ሱዳን የሰላም ጥናት ተቋም ባልደረባ አብርሃም አቮሊች ደግሞ የህዝቡን አንድ አለመሆን ፖለቲከኞች ለሥልጣናቸው ማራዘሚያ እየተጠቀሙበት ነው ይላሉ ።
« በመሠረቱ ህዝቡ ተለያይቷል ተከፋፍሏል ። ይህን ለመቋቋም መሞከር ያስፈልጋል ። ሁሉም መንግሥትን እንዲለይ መልሶ ለመገንባት መጣር ያስፈልጋል ። ለሁሉም ህዝብ የሚሰራ መንግሥት ቢኖር እርቀ ሰላም ቢወርድ እንኳን አንዳንዱ ህዝብ እንደደኽየ ነው የሚቀጥለው ። ፖለቲከኞች ሁል ጊዜም እነዚህን ልዩነቶች በመጠቀም ወደ ሥልጣን ለመውጣት ነው የሚሞክሩት ። »
ካለፈው ታህሳስ አንስቶ በሚካሄደው የደቡብ ሱዳን የርስ በርስ ጦርነት ወደ 10 ሺህ የሚጠጋ ህዝብ ህይወት እንዳለፈ ይገመታል ። የእርዳታ ድርጅቶች የሞቱት ሰዎች ቁጥር ከዚህም በላይ ነው ይላሉ ። ኦክስፋም የተባለው ድርጅት በቅርቡ እንዳስታወቀው ከህዝቡ አንድ ሶስተኛው ወይም ወደ 4 ሚሊዮን የሚሆነው ለአሳሳቢ የረሃብ አደጋ ተጋልጧል ።
ሂሩት መለሰ
ነጋሽ መሃመድ