1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዩናየትድ ስቴትስና የደቡብ አሜሪካ ሐገራት ግንኙነት

ሰኞ፣ ሚያዝያ 12 2001

ከአይዘናወር-እስከ ቡሽ ከነበሩት አስር-ቀዳሚዎቻቸዉ ሥሕተት የመማራቸዉ ብስለት፤ የደደረዉን ዉልግድ-ለማረቅ-የመድፈራቸዉ ጀግንነት ያስደንቅ ይሆናል።ተዓምር ግን አይደለም።ሐቅ እንጂ

https://p.dw.com/p/HakN
ኦባና ሻቬዝምስል AP

መስከረም-ሁለት ሺሕ (ዘመኑ በሙሉ እንደ አዉሮጳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) የያኔዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳት ቢል ክሊንተን ከኩባዉ መሪ ፊደል ካስትሮ ጋር ድንገት ሳያስቡት ያዉም ለቅፅበት ያደረጉት ወራት በዘለቀ-የትችት፣ ወቀሳ ማዕበል የሚገፋ «ተዓምር» ነበር-የሆነዉ።ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማም ከትችት ወቀሳ አያመልጡ ይሆናል።ሰሞኑን ያሉት መደረጉን-የጀመሩት ዳር መዝለቁን በያኙም በርግጥ ጊዜ-ና ሁነት ነዉ።ከአይዘናወር-እስከ ቡሽ ከነበሩት አስር-ቀዳሚዎቻቸዉ ሥሕተት የመማራቸዉ ብስለት፤ የደደረዉን ዉልግድ-ለማረቅ-የመድፈራቸዉ ጀግንነት ያስደንቅ ይሆናል።ተዓምር ግን አይደለም።ሐቅ እንጂ።ሐቁ መድረሻችን፣ የሐቫና ዋሽንግተን ግንኙነት ዳራ-ጉልሕ፥ የአሜሪካ እዉነት ስስ-አብነታችን፣ የአሜሪካኖች ጉባኤ መነሻችን ነዉ-ላፍታ አብራችሁን ቆዩ።
--------------------------------------------------------------
ፊደል ካስትሮ የመሯቸዉ አማፂዎች በ1959 ሐቫናን-እስኪቆጣጠሩ ድረስ እንደዘበት አይተዋቸዉ የነበሩት የዋሽንግተን መሪዎች ዳግመኛ-አልተዘናጉም።ዋሽንግተኞች በነካስትሮ፣ በነቼ-ጉቤራ ርዕዮት፣ገድል-ድል ልቡ የሸፈተዉ የደቡብ አሜሪካ ወጣት ኮሚንስት ቺሊ ላይ በሕዝብ ምርጫ ሥልጣን ሲይዝ በጄኔራል አጉስቶ ፒኖሼ አስጨፈጨፉት።

የኒካራጓ ሶሻሊስቶችን በኮንትራ አማፂያን ለማስደፍለቅ አሜሪካዉያንን ካገቱት ከቴሕራን እስላማዊ አብዮተኞች ጋር እስከመዋዋል ደርሰዋል።ጥቅምት 1983 ቤርናርድ ኮርድ የመሯቸዉ የግሪናዳ ኮሚንስቶች-የጠቅላይ ሚንስትር ማዉሪሲ ቢሾፕን መንግሥት አስወግደዉ ትንሺቱን ሐገር ተቆጣጠሩ።ሳምንት ግን አልቆዩም።

የዩናይትድ ስቴትስና የተባባሪዎቿ ጦር ግሪናዳን ወርሮ-ከስልጣን አስወገዳቸዉ።አስፈጠማቸዉም። ለረጅም ጊዜ የዋሽንግተን ታማኝ የነበሩት የፓናማዉ ገዢ ጄኔራል ማኑኤል ኑርኤጋ በ1980ዎቹ ማብቂያ ዉልፊጥ ቢሉ-የአሜሪካ ጦር ማንቁርታቸዉን ይዞ-ወሕኒ ወረወራቸዉ።ዩናይትድ ስቴትስ ሲሻት ጦሯን-እያዘመተች፣ ሲፈልጋት የቦጎታ መንግሥትን እየረዳች፤ የኮሎምቢያ ጫካዎችን መደብደብ ማስደብደቧ የአደንዛዥ እፅ-ተክል ዝዉዉርን ከማጥፋት ይልቅ የኮሚንስቶችን እንቅስቃሴ ለመግታት በርግጥ በእጅጉ ጠቅሟታል።

ሶቬት ሕብረት በተፈረካከሰች፣ አለም ኮሚንዝምን እርም ባለበት በ1999 የቬኑዙዌላ ሕዝብ የመረጣቸዉ ሁጎ ራፋኤል ሻቬዝ ፍሪያስ ዳግማዊ ካስትሮ-መሆናቸዉ ለትልቂቱ ሐገር ትላልቅ መሪዎች ትልቅ ራስ ምታት ነዉ-የሆነዉ።ፕሬዝዳት ቢል ክሊንተን የሻቬዚን መርሕ-አላማ ቢያዉቁቱም ወደ ኒዮርክ ያቀኑት ሻቬዝ የትልቅ-ሐገራቸዉ ያፍንጫ-ሥር መዥገር መሆን-አለመሆናቸዉን ሳይወስኑ ነበር።


የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአመአቱ ጉባኤ ያለዉ-የመሪዎች ጉባኤ ለክሊንተን የመጨረሻዉ፤ ለሻቬዝ የመጀመሪያቸዉ፣ ለካስትሮ ምናልባት አርባኛቸዉ ነበር።።የአለም መሪዎች ከምሳ-እረፍት ወደ ጉባኤዉ አዳራሽ እየተመሙ ነዉ።ክሊተን እያወጉ-ሲያዘግሙ፣ ካስትሮ ቀደም፣ ሻቬዝ ከተል ብለዉ ደረሱባቸዉ።ካስትሮ-እጃቸዉን ዘረጉ።ክሊንተንም።ተጨባበጡ።የኒዮርክ ተዓምር።መስከረም-ስድት ሁለት ሺሕ።

ተዓምሩ ለሰላም ጥሩ ጀምር በሆነ-ነበር።ሥልጣናቸዉን ለማስረከብ የአራት ወር እድሜ የቀራቸዉ ክሊንተን በጅምሩ ሊቀጥሉ ቀርቶ የጅምሩን ጥሩ-መጥፎነት ለማስተንተን እንኳን በርግጥ ጊዜ አልነበራቸዉም።«በቃ-ድንገት ሆነ» ብለዉ-አለፉት።

ለሌላዉ ግን አይዘናወር ከካስትሮዋ ኩባ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ካቋረጡበት ከ1960 ጀምሮ፣ በካስትሮዋ ኩባ ሰበብ ሰወስተኛዉን የአለም፤ የመጀመሪያዉን የኑክሌር ጦርነት ለመግጠም የቆረጡት፣ ካስትሮን ለማስወገድ የቤይ ኦፍ ፒግ ተዋጊዎችን ያዘመቱት፤ ማዕቀብ የጣሉት፣ ካስትሮን ለማስገድል ስድስት መቶ-ሰላሳ ስምንት ጊዜ የወሰኑት የስምንት ቀዳሚዎቻቸዉን ዉግዘት ክሊንተን አረከሱት ነበር-ፍቺዉ።በዘጠነኛ አመቱ በቀደም ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ አሜሪካዊ-ኩባዉያን ኩባን እንዳይጎበኙ፥ለወዳጅ ዘመዳቸዉ ገንዘብ እንዳይልኩ፣የሚደነግገዉን ደንብ ማላላታቸዉ-በአክራሪ አሜሪካዉያን ዘንድ ብዙ ያስወቅስ-ያስተቻቸዉ ይሆናል።

አላማዉ ግን ቃል አቀባይ ሮበርት ጊብስ እንዳሉት ዲሞክራሲ፥ ሰብአዊ መብትን መደገፍ ነዉ።
ድምፅ
«ሁላችንም ከረጅም ጊዜ ጀምሮ የምንመኘዉ ለዜጎችዋ በሙሉ የሰብአዊ መብት፥የፖለቲካ እና የምጣኔ ሐብት ነፃነት መሠረት የሆኑት የዲሞክራሲያዊ እሴቶች የሰፈኑባት ኩባ እንድትኖር ነዉ።ፕሬዝዳንት ኦባማ ዛሬ የወሰዱት እርምጃ ይሕን አላማ ከግብ ለማድረስ ይረዳል ብለዉ-ያምናሉ።»

በክሊንተንን ድንገተኛ ጅምር ላይ የተሰነዘረዉ ጠንካራ ትችት የጅምሩን ጥሩ መጥፎነት ለማስተንተ ብቃቱ፤ ፍላጎቱ፤ ብስለቱም ላልነበራቸዉ ለፕሬዝዳት ጆርጅ ቡሽ አጓጉል መርሕ ጠንካራ መሸፈኛ ነበር-የሆነዉ።የቡሽ መስተዳድር በሐቫና እና በካራካስ፣ መሪዎች ላይ ሲዝቱ፤ ብራዚልን ከሜክሲኮ ሲያላትሙ፣ ቦሊቪያ ላይ «ሳልሳዊ ካስትሮ» ስልጣን ያዙ።ኢቮ ሞራሌስ።

የቡሽ መስተዳድር የኩባ፤ በቬኑዝዌላ እና የቮልቪያ ገዢዎችን ለማዳከም ኮሎምቢያን የመሳሰሉ ታማኞቹን ሲያስተባብር፥ በ1980ዎቹ የሬጋን መስተዳድር ሊያጠፋቸዉ ሲባትል ከቅሌት የተነከረባቸዉ ዳንኤል ኦርቴጋ ዳግም የኒካራጉዋ መሪ ሆኑ።«አራተኛዉ ካስትሮ።»

Nicaragua Daniel Ortega Wahlen
ኦርቴጋ «...ኦባማ ተጠያቂ አደሉም»ምስል AP

ኦርቴጋ ባለፈዉ ቅዳሜ ፖርት ኦፍ ስፔን ለተሰየመዉ የአሜሪካ ሐገራት ጉባኤ ባደረጉት ንግግር የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም ያሉት ሥርዓት በደቡብ አሜሪካ ሕዝብ ላይ ፈፀመ ያሉትን በደል-ሲዘረዝሩ-ሁለት አብነት ጠቅሰዉ ነበር።የሬጋን መስተዳድር በኒካራጓ-፣የኬኔዲ በ1961 ቤይ ኦፍ ፒግስ በተባለዉ ዉጊያ በኩባ ሕዝቦች ላይ ፈፀሙ ያሉትን ግፍ።ኦባማን ግን ለዚሕ ግፍ አይጠየቁም ነዉ-ያሉት-ኦርቴጋ።

«የሰወስት ወር ሕፃን እያለሁ ለተሰራዉ» መለሱ-ኦባማ «እኔን ተጠያቂ ባለማድረጋ
ቸዉ» አመሰግናለሁ።የሰወስት ወር ሕፃን-አይደለም ጨርሶ ከመወለዳቸዉ በፊት ጀምሮ የፀናዉን የኩባና የዩናይትድ ስቴትስን የጠላትነት ግንኙነት መለወጡ እራሳቸዉ ኦባማ እንዳሉት ከባድ፥ጊዜ የሚጠይቅም ነዉ።
ድምፅ
«ዩናይትድ ስቴትስ ከኩባ ጋር አዲስ ግንኙነት እንዲጀመር ትሻለች።ዘመናት ያስቆጠረዉን አለመተማመን ለማስወገድ ብዙ ርቀት መጓዝን እንደሚጠይቅ አዉቃለሁ።ይሁንና ካዲሱ ዕለት ለመድረስ መሠረታዊ የሆኑ እርምጃቸዉን መዉሰድ እንደምንችል አዉቃለሁ።»

የቡሽ መስተዳድር በ2006 የተመረጡትን የቺሊ ፕሬዝዳት የወዝሮ ቬሮኒካ ሚሼላ ባችቤት የሪያን ግራ ዘመም መንግሥትን ለማዳከም ከፔሩና ከአርጀቲና ጋር ለማናቆር ሲባትል ከቺሊዋ መሪ ጋር ፆታም የፖለቲካ መርሕም የሚጋሩት ወይዘሮ ክርስቲና ኤሊዛበት ፈርዲናንዴስ ኪርቺነር የቦኒስ አይሪስን ቤተ-መንግሥት ተቆጣጠሩት።የቡሽ ባለሥልጣናት ክሪችኒር-እንዳይመረጡ ፥ለምርጫ ዘመቻቸዉ ከቬኑዝዌላዉ ፕሬዝዳት ሁጎ ሻቬዝ አንድ ሚሊዮን ዶላር ተቀብለዋል በማለት እስከመወንጀል ደርሰዉ-ነበር።

50 Jahre Revolution Kuba Raul Castro
ራኡል ካስትሮ «... እንደራደር»ምስል AP

የአርጀቲና ሕዝብ ዋሽግተኖችን ሰማቸዉ-ታዘባቸዉ።ሴትዮዋን ይበልጥ ወደዳቸዉ መረጣቸዉም።ኦባማን ኦርቴጋ-ለአልወነጀሏቸዉም፥ፕሬዝዳት ጆርጅ ቡሽን ዳቢሎስ በማለት ይሳደቡ የነበሩት ሁጎ ሻቬዝ ለኦባማ መፀሐፍ ነዉ-ያበረከቱላቸዉ።በቡሽ መስተዳድር አቂመዉ የነበሩት ከቦልቪያ እስከ አርጀንቲና፥ ከብራዚል እስከ ቺሊ ያሉት ሐገራት መሪዎችም በታላቅ አክብሮት ነዉ-የተቀበሏቸዉ።ራኡል ካስትሮ ደግሞ የሁሉንም አሉት-እንደራደር።
ድምፅ
«ለዩናይትድ ስቴትስ እናገራለሁ።በሁሉም ጉዳይ ለመደራደር ዝግጁ ነን።ሥለ ሰብአዊ መብት፥ሥለ ፕረስ ነፃነት፥ሥለ ፖለቲካ እስረኞች-እዉነት እላችኋለሁ-ሥለሁሉም።ድርድሩ ግን በእኩለት ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት።ሉአላዊነታችን መቼም ቢሆን ሊያጠራጥር አይገባም።»

ይሕ አይነቱ ምላሽ ኦባማ የክሊተንን ደመነሳዊ-ጅምር በበሳል-መርሕ ለመተካት-ለመጣራቸዉ፤እስከ ክሊንተን የዘለቀዉን ጅምላ ስሕተት በነጠረ-እዉነት ለማረም-ለመሞከራቸዉ፣ የቡሽን የስምንት አመት የጥፋት ጉዞ ቀና ፈር ለማስያዛቸዉ ጥሩ እማኝ ነዉ።ይሕ ቢቀር ሰባ-ከመቶ የሚበልጠዉ አሜሪካዊ ሐገሩ ኩባን ከመሳሰሉ ጎረቤቶቿ ጋር መልካም ግንኙነት እንድትመሰርት ይፈልጋል።ኦባማ ሌላ አላደረጉም። የመራጣቸዉን ሕዝብ ፍላጎት ማስፀም እንጂ።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

dw,wikipedia

ነጋሽ መሐመድ