1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም ኤኮኖሚ ይዞታ፤ የታዳጊው ዓለም ዕጣ

ዓርብ፣ ሰኔ 10 1997
https://p.dw.com/p/E0eZ
የአውሮፓ ኮሚሢዮን ርዕስ ሆሴ ማኒኤል ባሮሶ
የአውሮፓ ኮሚሢዮን ርዕስ ሆሴ ማኒኤል ባሮሶምስል AP

በጋራ ሕገ-መንግሥት ጽድቂያው ሂደት አኳያ በቅርቡ በፈረንሣይና በኔዘርላንድ ሕዝብ ተቃውሞውን በግልጽ ካሣየ ወዲህ ቀውስ ላይ የወደቀው የአውሮፓ ሕብረት አሁን ደግሞ በመጪዎቹ ዓመታት በጀት አመዳደብ ሁኔታ በክርክር ተጠምዶ ነው የሚገኘው። የሕብረቱ መንግሥታት መሪዎች ነገና ከነገ በስቲያ ብራስልስ ላይ ተሰብስበው በዚሁ ጉዳይ መፍትሄ ለማፈላለግ ጥረት ያደርጋሉ።

ውዝግቡን ለማብረድ ሰሞኑን ከወዲሁ የተደረጉ ጥረቶች እስካሁን አስታራቂ ሊሆን የሚችል ጭብጥ መፍትሄን ሊያስገኙ አልቻሉም። የአውሮፓ ሕብረት በዚህ ችግር የተወጠረው የዓባል መንግሥታቱ ቁጥር በጨመረበትና የዓለም ኤኮኖሚ ሁኔታ መወሳሰብ ከፍተኛ የዕድገት ችግር ፈጥሮ በሚገኝበት ወቅት ነው። የሥራ-አጡ ቁጥር በተለይ ዋነኛው በጀት አቅራቢ በሆነው በምዕራቡ ክ’ፍል በሰፊው እየጨመረ ሲሆን ዓመታዊው ዕድገትም የሚያበረታታ አይደለም።

አስቸጋሪው ሁኔታ በጉዳዩ በተለይ የሚከራከሩት ብሪታኒያ በአንድ በኩልና ፈረንሣይ በሌላ ወገን ከሕብረቱ ይልቅ ብሄራዊ ጥቅማቸውን እንዲያስቀድሙ አስገድዷል። የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒይ ብሌይርና የፈረንሣዩ ፕሬዚደንት ዣክ ሺራክ ትናንት ፓሪስ ላይ ተገናኝተው በጉዳዩ ባካሄዱት ንግግርም አስታራቂ በሆነ አቅጣጫ ጭብጥ ዕርምጃ ሊያደርጉ አልቻሉም።

የአውሮፓ ሕብረት ኮሚሢዮን ከ 2007 እስከ 2013 ዓ.ም. ለሚዘልቀው የበጀት ዘመን ዓባል ሃገራቱ አንድ ሺህ ሚሊያርድ ኤውሮ እንዲያቀርቡ ይጠይቃል። ሆኖም ገንዘብ አቅራቢዎቹ 815 ሚሊያርድ ኤውሮ ብቻ ለመክፈል ነው ዝግጁ ሆነው የሚገኙት። ቀዳዳውን ለመሽፈን ብሪታኒያ ፈረንሣይና ጀርመን እንደሚጠይቁት በያመቱ ከአውሮፓ ሕብረት የምታገኘውን ተመላሽ ገንዘብ መቀበሉን ለመተው ፈቃደኛ አይደለችም።
በአንጻሩም ብሪታኒያ እንደምትሻው ፈረንሣይ ከሕብረቱ የምትቀበለው የዕርሻ ድጎማ መቆረጡን ፓሪስ አትፈቅደውም። ለውዝግቡ ቁልፍ ሆኖ የሚገኘው ይህ የሕብረቱ ቀደምት መንግሥታት የሃሣብ ልዩነት ነው። በወቅቱ በስድሥት ወሩ የሚፈራረቀውን የሕብረቱን ርዕስነት ይዛ የምትገኘው አገር የሉክሰምቡርግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዣን-ክሎድ-ዩንከር ለነገው ጉባዔ በሚያደርጉት ዝግጅት አስታራቂ ሁኔታን ለማመቻቸት ከዓባል መንግሥታት መሪዎች ጋር በተናጠል መነጋገራቸው አልቀረም። ሆኖም አንዳች የረባ ውጤት ሊያገኙ አለመቻላቸው ነው ችግሩ!።

ዩንከር የቀራቸው ምርጫ ባልተጠበቀ ሁኔታ እስካሁን ማንም ያልደፈረውን የዕርሻ ድጎማ መርህ መፈታተን ብቻ ነው። የሉክሰምቡርጉ ጠቅላይ ሚኒስትር “በሁሉም ዘርፍ ስለሚደረግ ቁጠባ መነጋገር ይኖርብናል። እዚህ ላይ ከሕብረቱ አጠቃላይ በጀት አርባ በመቶውን ድርሻ የሚይዘው የዕርሻ ዘርፍም አንዱ ነው።” ሲሉ ሰሞኑን የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ሲያነሱ የቆየውን ጥያቄ ክብደት ሰጥተውታል።

ይሁንና የፈረንሣዩ ፕሬዚደንት ዣክ ሺራክ የአገራቸውን ገበሬ ጥቅም ለማስነካት ፈቃደኛ አይደሉም። በሌላ በኩል የአውሮፓው ሕብረት የበጀት ፖሊሲውን ሥር-ነቀል በሆነ መልክ መለወጥ ይኖርበታል የሚሉትም ብዙዎች ናቸው። ለምሣሌ፤ ጀርመናዊው ኮሜሣር ጉንተር ፈርሆይገን ”አብዛኛውን ገንዘብ ይበልጥ አጣዳፊ ለሆኑ ተግባራት፤ ለምሳሌ ለዕድገት፣ ለሥራ መስኮች መስፋፋትና ለፉክክር ብቃት ማውጣት መቻል አሁን ጊዜው የሚጠይቀን ጉዳይ ነው። ግን ያሳዝናል ከጥቂት ዓመታት በፊት የዕርሻ ድጎማው ወጪ እስከ 2013 ቋሚ ሆኖ እንዲዘልቅ ከቶኒይ ብሌይር ጋር ስምምነት መደረጉ/ ፈረንሣውያኑም አሁን የሚከራከሩት ይህንኑ ስምምነት በማስረገጥ ነው።” ይላሉ።

ቶኒይ ብሌይር ትናንት ከፈረንሣዩ ፕሬዚደንት ተገናኝተው በተነጋገሩበት ወቅት ብሪታኒያ በአውሮፓው የገንዘብ አወጣጥ መርህ ላይ መሠረታዊ ለውጥ ቢደረግ ከሕብረቱ በምታገኘው ገንዘብ መቆረጥ ጉዳይ ልታስብበት እንደምትችል አስገንዝበዋል። አስታራቂ አድርገው ለሚያምኑበት መፍትሄ ፍንጭ መስጠታቸው ነው። ብሪታኒያ ከሕብረቱ ተመላሽ ገንዘብ የምታገኘው በዕርሻው ዘርፍ የምትቀበለው ድጎማ ከፈረንሣይ ሲነጻጸር እጅግ ዝቅተኛ በመሆኑ ነው። በሌላ በኩል ብሪታኒያ ከጀርመን ቀጥላ ሁለተኛዋ ዋነኛ የሕብረቱ ገንዘብ አቅራቢ ናት። እርግጥ ብዙዎች የሕብረቱ ዓባል ሃገራት የቀድሞዋ የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርጋሬት ታትቸር ከ 21 ዓመታት በፊት ታግለው ያሰገኙት ተመላሽ ገንዘብ ከፍተኛ ነው ባዮች ናቸው።

የሆነው ሆኖ በሚቀጥሉት ሁለት ቀናት ብራስልስ ላይ የሚካሄደው የአውሮፓ ሕብረቱ መሪዎች ጉባዔ በጉዳዩ ታላቅ ዕርምጃ ማድረጉ ሲበዛ ነው የሚያጠያይቀው። የሕብረቱ ኮሚሢዮን ጀርመንን የመሳሰሉት ዋነኞቹ ገንዘብ አቅራቢዎች መዋጯቸውን ከፍ እንዲያደርጉ የሚያቀርበው ጥሪ ያን ያህል ሰሚ ጆሮ ያገኘ ነገር አይደለም። በሌላ በኩል ከአንድ ዓመት በፊት በአሥር ተጨማሪ ዓባላት በመስፋፋት 25 አገሮችን ያቀፈው ማሕበረ-ሕዝብ መጤዎቹን ለመደጎም በጀቱን ከፍ ማድረጉ ግድ ነው የሚሆንበት። እነዚሁ ሀገራት ከተቀባይነት አልፈው ሰጪ ለመሆን ገና ብዙ ጊዜ እንደሚጨርስባቸው የሚታወቅ ነው። ጉባዔው ምናልባት ውሱን አስታራቂ መፍትሄን ሊያመላክት ይችል ይሆናል። ግን ይህ በቂ አይሆንም።

በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት መንግሥታት የታዳጊውን ዓለም፤ በተለይ የአፍሪቃን ድህነት ለማለዘብ እስካሁን ከነበረው የበለጠ የልማት ዕርዳታ ይጠበቅባቸዋል የሚለው ማሳሰቢያ በዚህ በሶሥተኛው ሺህ ምዕተ-ዓመት መግቢያ ላይ የተባበሩት መንግሥታት የሚሌኒዬም ዕቅድ ከወጣ ወዲህ አዘውትሮ ሲሰማ የቆየ ጉዳይ ነው። ብዙ ተብሏል፤ ግን በተግባር ዕቅዱን በጊዜው ለማጠናቀቅ የሚያበቃ ዕርምጃ ተወስዷል ለማለት አይቻልም።

ለነገሩ የሰባቱ የበለጸጉ መንግሥታትና የሩሢያ የገን’ዘብ ሚኒስትሮች ባለፈው ቅዳሜ በዓለም ላይ የድሃ ድሃ ለሚባሉት አገሮች ከአርባ ሚሊያርድ ዶላር የሚበልጥ የዕዳ ምሕረት ለማድረግ ተስማምተዋል። ይህ በጉዳዩ በቅርቡ ስኮትላንድ ላይ ለሚመክረው የ G-8 መሪዎች ጉባዔ ቅድመ-ዝግጅት መሆኑ ነው። ግን የተባለው ስምምነት ከችግሩ ሲነጻጸር ሊያጽናና የሚችል አይሆንም።

የዓለም ባንክ የቅርብ መረጃ እንደሚያመለክተው ከሣሃራ በስተደቡብ የሚገኘው የአፍሪቃ ክፍል አጠቃላይ የውጭ ዕዳ ከሁለት ዓመታት በፊት 231 ቢሊዮን ዶላር ገደማ የተጠጋ ነበር። የአፍሪቃ ዕዳ በመላው አሕጉር ደረጃ ደግሞ እንዲያውም 321 ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል። በልማት ዕርዳታ ተግባር የተሰማሩ ድርጅቶች እንደሚሉት የሚሌኒዬሙን ዕቅድ ከግቡ ለማድረስ ለ 62 አገሮች መቶ በመቶ የሀነ ሙሉ የዕዳ ምሕረት ያስፈልጋል።
እስካሁን በ G-8 አኳያ ሰወራ የሰነበተው ግን በመጀመሪያ ለ 18 ሃገራት፤ ከዚያም በሚቀጥለው አንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ለተጨማሪ ዘጠኝ ሃገራት፤ በጠቅላላው በሚቀጥሉት ዓመታት ለ 38 አገሮች ሙሉ የዕዳ ምሕረት እንደሚደረግ ነው። የዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቋም የ IMF የወርቅ ክምችት ተሽጦ ለድጎማ ሥራ በመዋሉ ጉዳይ የተነሣው ውይይትም አከራካሪ ሆኖ ይገኝ እንጂ ከመጪው ጉባዔ አጀንዳ ገና አልተሰረዘም።

በሌላ በኩል የዕዳ ምሕረቱ ጥረት ዋነኛ አንቀሳቃሽ የሆነው የብሪታኒያ መንግሥት የገንዘብ ሚኒስትር ጎርደን ብራውን እንደሚሉት ዕቅዱ ከተቀባዮቹ ሃገራት በጎ የአስተዳደር ብቃትና ግልጽ የአሠራር ዘይቤ ጋር ተመሳክሮ ገቢር መሆኑ ቁልፍ ጉዳይ ነው። ሚኒስትሩ ገንዘቡ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች መድረሱ የስምምነቱ ቁልፍ ነው ብለዋል። ስኬት እንዲያገኝም የንግድ ፍትህን መስፈንና የሙስናን መወገድ የመሳሰሉ ፍቱን ዕርምጃዎች የግድ አስፈላጊ ይሆናሉ። የዕቅዱ ዝርዝር ይዘት በስኮትላንዱ ጉባዔ ላይ ይፋ እንደሚሆን ነው የሚጠበቀው።

የዕዳ ምሕረትን በተመለከተ የበለጸጉት መንግሥታት መሪዎች ባለፉት ዓመታት በያጋጣሚው የሰጡት ተሥፋ ዕውን ሲሆን አልታየም፤ መስፈርቱን አሻሚና ግራ አጋቢ አድርገው ያገኙት የልማት ዕርዳታ ተሟጋቾች ብሉዎች ናቸው። በምዕራቡ ዓለምና በታዳጊ አገሮች መካከል በንግድና በመዋዕለ-ነዋይ እቅስቃሴ አኳያ እየሰፋ የመጣው ልዩነት እንዲያውም አሁን የደቡብ-ደቡብ ግንባር የመፍጠር ጥረት እንዲነቃቃ ምክንያት ሆኗል።

በትናንትናው ዕለት 132 የዓለም ታዳጊ አገሮች የደቡብ-ደቡቡን ትብብር የሚያጠናክር የተግባር ዕቅድ ለማስፈን ካታር ርዕሰ-ከተማ ዶሃ ላይ የሁለት ቀናት ስብሰባ ከፍተዋል። የስብስቡ ዓላማ የደቡብ-ምሥራቅ እሢያ አገሮችን ማሕመር፤ በአሕጽሮት አሴያን፣ የማግሬብ ሕብረትን ወይም የምዕራብ አፍሪቃን የኤኮኖሚ ተራድኦ ድርጅት ኤኮዋስን መሰል ፈለግ መከተል ነው። መንግሥታቱ ትስስሩ በኢንዱስትሪ ልማት ከበለጸጉት ከሰሜኑ የዓለም ክፍል መንግሥታት ጋር ያለውን ግንኙነት ይተካል ብለው አያምኑም። ሆኖም የደቡብ-ደቡቡ ትብብር ለጋራ ልማት መሣሪያ እንደሚሆን አይጠራጠሩም።

በአስተናጋጃ አገር በካታር ባለሥልጣናት ዕምነት ትብብሩ መጠናከሩ የገበያ ገደብ በሚደረግበት፣ የዕዳ መናር ባየለበት፣ የምርት ዋጋ መውደቅ በያዘበትና የልማት ዕርዳታም ከመቼውም ይልቅ ባቆለቆለበት በአሁኑ ጊዜ አስፈላጊነቱ እጅግ ከፍተኛ ነው። የታዳጊዎቹ አገሮች ማበር በዓለምአቀፍ ደረጃ የደቡቡን ክፍል የመደራደር ሃይል እንደሚያዳብርም ጽኑ ዕምነት አለ።

የደቡብ-ደቡቡ ትብብር ጽንሰ-ሃሣብ መሠረት መያዝ የጀመረው የታዳጊ አገሮች ተራድኦ ጉባዔ ከ 27 ዓመታት በፊት በአርጄንቲና-ብዌኖስ አይርድ ከተካሄደ ወዲህ ነበር።