1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም ኤኮኖሚ መድረክ በአፍሪቃ

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 26 2003

በአፍሪቃ ላይ ያተኮረው የዘንድሮው የዓለም ኤኮኖሚ መድረክ ጉባዔ ዛሬ ደቡብ አፍሪቃ ርዕሰ-ከተማ ኬፕታውን ላይ ተከፍቷል።

https://p.dw.com/p/RLyp
ምስል DW

እስከፊታችን አርብ በሚዘልቀው ጉባዔ ላይ ከመላው ዓለም የሄዱ ሰባት መቶ ገደማ የሚጠጉ የምጣኔ-ሐብት አዋቂዎችና በርካታ ቀደምት የአፍሪቃ ባለሥልጣናት ይሳተፋሉ። የመድረኩ ስብሰባ የሚካሄደው “ከራዕይ ወደ ተግባር፤ ቀጣዩ የአፍሪቃ ምዕራፍ” በሚል መርሆ ነው። በጉባዔው ሶሥት ቀናት ለአፍሪቃ የኤኮኖሚ ዕድገት ጥርጊያ ለማበጀትና ክፍለ-ዓለሚቱ ከዓለምአቀፍ ተባባሪዎች ጋር ያላትን የንግድ ግንኙነት ለማሻሻል ጠቃሚ በሆኑ ነጥቦች ላይ ውይይት ይደረጋል። በኬፕታውን የጀርመኑ የንግድ ጋዜጣ የሃንደልስብላት ወኪል ቮልፍጋንግ ድሬክስለር የመድረኩን ዋነኛ የውይይት ነጥቦችና የተሳታፊዎቹን ግብ ሲዘረዝር በአፍሪቃ ከፍተኛና ዘላቂ ዕድገት መደረጉ ዋናው ነገር መሆኑን ነው የገለጸው።

“የመድረኩ ዋነኛ ርዕስ በመርሆው ላይ እንደተጠቀሰው “ከራዕይ ወደ ተግባር” የሚል ነው። እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ በመድረኩ ስለ ዕቅድ ወይም ጽንሰ-ሃሣቦች ብቻ በማውራት መወሰኑ አይፈለግም። በአፍሪቃ የሚመነጨው በጥሬ ዕቃ ዋጋ ላይ ብቻ ጥገኛ ያልሆነ የከፍተኛ ኤኮኖሚ ዕድገት ዕቅድና ሃሣብ ገቢር መሆን ይኖርበታል። የዚህ መድረክ ዋና ገጽታ ይህ ነው። አንድ አብሬ ልጠቅሰው የምፈለገው ንዑስ ርዕስም አለ። ይሄውም ደርባን ላይ የሚካሄደው የአካባቢ አየር ጉባዔ ሲሆን በአፍሪቃ ላይ ሊኖረው ስለሚችለው ተጽዕኖ ንግግር ይደረጋል። ስለ አፍሪቃና ስለ ቱሪዝምም እንዲሁ! ሆኖም ግን ዋናው ርዕስ የአፍሪቃ ኤኮኖሚ ነው። ወደታች በማቆልቆል መቀጠል የለበትም። ከላቲን አሜሪካና ከሁሉም በላይ ደግሞ ከእሢያ ጋር፤ በተለይም ከቻይናና ከሕንድ አብሮ መራመድ መቻል ይኖርበታል። ንኪኪውን ማጣት የለበትም”

ለነገሩ የአፍሪቃ ኤኮኖሚ ባለፉት ዓመታት ያለማቋረጥ እያደገ መምጣቱን ብዙ የምጣኔ-ሐብት ጠበብት ናቸው የሚናገሩት። አፍሪቃ የቅርቡን ዓለምአቀፍ የፊናንስ ቀውስም በሚያስደንቅ ሁኔታ ያለ ከባድ ውድቀት ልትቋቋም በቅታለች። ሆኖም ግን የዕድገቱ ተጠቃሚዎች ገዢዎቿና በእጣት የሚቆጠሩ አበሮቻቸው እንዲሁም የተፈጥሮ ሃብቷን የሚያወጡ ዓለምአቀፍ ኩባንያዎች ናቸው። በዚህ በኩል በቅርብ ጊዜ ለውጥ ይደረጋል ብሎ መጠበቁም በወቅቱ ከባድ ነገር ነው።

“የተጠቀሙት ኩባንያችና ገዢዎች ብቻ ናቸው ማለቱ ይከብዳል። እርግጥ በአፍሪቃውያኑ ከፍተኛ መደብ ላይ በሚባለው እስማማላሁ። አፍሪቃ በአብዛኛው በአንድ ፓርቲ የበላይነት የምትገዛ በመሆኗ ላይ የተቀመጡት የመንግሥትን በጀት ይቆጣጠራሉ። ይካብታሉ ማለት ነው። ኩባንያዎችን በተመለከተ ጥቂት ለዘብ ማለቱን እመርጣለሁ። ምክንያቱም ዛሬ አንድ ኩባንያ በቀላሉ አፍሪቃ ገብቶ ጥሬ ሃብት መበዝበዝ አይችልም። በኮንኮ የመዳብ መቀነት ላይ የተሰማራ፣ በአንጎላ ወይም በናይጄሪያ ነዳጅ ዘይት የሚያወጣ ኩባንያ መንገድ መሥራት፣ ማሕበራዊ ፕሮዤዎችን ማራመድና ሃኪም ቤቶችን ማነጽ ይኖርበታል። ኩባንያዎቹ ከፍተኛ ቅድመ-ግዴታ አለባቸው ማለት ነው። እናም ከመውሰድ በስተቀር የሚሰጡት ነገር የለም ለማለት አይቻልም”

በሌላ በኩል አፍሪቃ በመጪዎቹ ዓመታት በዓለም ላይ የተፋጠነነ ዕድገት ከሚካሄድባቸው አካባቢዎች አንዷ እንደምትሆን ጠበብት ይናገራሉ። ሆኖም ጥያቄው የሚገኘው የኤኮኖሚ ዕድገት ማሕበራዊውን ገጽታ በሰፊው ለመቀየር የሚበቃ ይሆናል ወይ ነው። ቮልፍጋንግ ድሬክስለር እንደሚለው ለውጥ ለማግኘት ዕድገቱ ከአሁኑ በጣሙን ከፍ ያለ መሆን ይኖርበታል።

“አፍሪቃ በመጪዎቹ ዓመታት የተፋጠነ ዕድገት ታሳያለች የሚለው አባባል ትክክለኛ ነው። አፍሪቃ አሁን እንዳለፉት አሥር ዓመታት ሁሉ ኤኮኖሚዋን በአማካይ 5,7 ከመቶ ማሳደጉ ሆኖላታል። ግን ይህ የ 5,7 ከመቶ ዕድገት በዝቅተኛ የዕድገት መሠረት ላይ ለምትገኝ ክፍለ-ዓለም ምኗ ነው። በቂ አይደለም። አፍሪቃ በመሠረቱ በእሢያ በ 70, 80, እና 90ኛዎቹ ዓመታት ከተገኘው የተስተካከለ ዕድገት ማድረግ አለባት። ይሄም ለሃያ ዓመታት ያህል አሥር ከመቶና ከዚያም በላይ መሆኑ ነው። እንግዲህ አሁን ጥሬ ሃብትን ብንወስድ ለምሳሌ ነዳጅ ዘይት ያላት አንጎላ ኤኮኖሚዋን ብዙ-ወጥ አድርጋ ለማሳደግ አልቻለችም። ታዲያ ክፍለ-ዓለሚቱ በዕድገት ብዙ ብትወደስም መዋቅራዊ ይዞታዋ ግን እንደ ላቲን አሜሪካ ወይም እንደ እሢያ ለከፍተኛ ዕድገት ያመቸ ሆኖ አልተለወጠም”

በአፍሪቃ ክፍለ-ዓለም የኤኮኖሚ ዕድገት ተገኘ ማለት ሁልጊዜ ማሕበራዊና ሕብረተሰብን ያካተተ ዕድገት አስከተለ ማለት አይደለም። በሌላ አነጋገር በብዙዎቹ ፈጣን ዕድገት ታየባቸው በተባሉት የአፍሪቃ አገሮች የኤኮኖሚው ዕድገት በሕዝቡ ማሕበራዊ ኑሮ መሻሻል ወይም ከድህነት መላቀቅ ሁኔታ በሰፊው አልተገለጸም። በአንጻሩ ሙስናና ያላግባብ በሕዝብ ንብረት መካበት የተለመደ ነገር ነው። እንዲህም ሆኖ አፍሪቃ ሁለት ገጽታ አላት ሊባል ይቻላል።

“እሱ ትክክለኛ አመለካከት ነው። የኤኮኖሚው ዕድገት የተጣጣመ አይደለም። በናይጄሪያ ለምሳሌ በነዳጅ ዘይት ኢንዱስትሪው የተነሣ ከፍተኛ ዕድገት አለ። ግን መረጃዎችን ተመልከት። በ 1970 እና በ 1980 ከናይጄሪያ ዘጠና ሚሊዮን ሕዝብ 19 ሚሊዮኑ ከድህነት መስፈርት በታች የሚኖሩ ነበሩ። ዛሬ ደግሞ ከሕዝቡ ብዛት ጋር አብሮ በሰፊው ጨምሯል። በወቅቱ ከ 150 ሚሊዮን ሕዝብ ከድህነት መስፈርት በታች የሚኖረው 90 ሚሊዮን ይደርሳል። እንግዲህ የሚገኘው ገንዘብ ሁሉ ከተገቢው ቦታ አይደርስም ማለት ነው። ይህ ምሳሌ ለአይቮሪ ኮስትም ይሰራል። በዚህች አገርም ከድሕነት መስፈርት በታች ያለው ሕዝብ ከ 19 ወደ 50 በመቶ ከፍ ብሏል። አይቮሪኮስት ዛሬ ለምን ከዚህ እንደደረሰችም ምክንያቱን እናውቃለን”
ቮልፍጋንግ ድሬክስለር ቀጠል በማድረግም፤
“እንዳልከው ትክክል ነው። ገንዘቡ ከሕዝብ አይደርስም። ግን የተለዩ አገሮችም አሉ። እነዚህም ዴሞክራሲ የሚሰራባቸው ናቸው። ለምሳሌ የመንግሥት ለውጥ ባለባት፣ አንድ ፓርቲ በአንድ፣ በሁለት ወይም ሶሥት በመቶ ድምጽ ብልጫ ብቻ ማሽነፍ በሚችልባት፤ ተቃዋሚዎችም ከተሽነፉ ውጤቱን በሚቀበሉባት በጋና ይህ ሃቅ አለ። በአፍሪቃ ከተለመደው የተለየ ነገር መሆኑ ነው። በሌላ በኩል ገዢዎች ተሸንፈው ሥልጣን አልለቅም ያሉባቸውን ዚምባብዌን፣ ኬንያን፣ አይቮሪ ኮስትን አስታውሳለሁ። ጋና እንግዲህ አርአያ ናት። ቦትሱዋናም በአንድ ጥሬ ሃብት በአልማዝ ላይ የተወሰነች ትሁን እንጂ ይህንኑ ጸጋ በትክክል ተጠቅማበታለች። ገንዘቡ በጤና ጥበቃ፣ በቴሌኮሙኒኬሺን፣ በትምሕርት ወዘተ... በጥሩ ሁኔታ ሲፈስ ታይቷል። ይህ በሁሉም የአፍሪቃ አገሮች ሃቅ ቢሆን ኖሮ ዘላቂ ዕድገትንና የተሻለ የኑሮ ሁኔታ ለማረጋገጥ በበጀ ነበር”

የደቡብ አፍሪቃው የዓለም ኤኮኖሚ መድረክ ጉባዔ “ከራዕይ ወደ ተግባር” የሚል መርሆ ራሱ የሚያመለክተው በአፍሪቃ እስካሁን ሁሉም ነገር ቢቀር በተፈለገው መጠን ያልተራመደ መሆኑን ነው። ለምሳሌ በመዋቅራዊ ግንባታ፣ በትምሕርት፣ በጤና ጥበቃ፣ የግሉን የኤኮኖሚ ዘርፍና ሲቪሉን ሕብረተሰብ በማጠናከሩ ረገድ ክፍለ-ዓለሚቱ ገና ብዙ ይቀራታል። እንደ ቮልፍጋንግ ድሬክስለር ከሆነ ሁኔታው በፍጥነት ይቀየራል ብሎ ተሥፋ መጣሉ የማይታሰብ ነው።

“የለም፤ በፍጥነት እንደማይሆን እርግጠኛ ነኝ። አፍሪቃ ውስጥ ዴሞክራሲ አልታነጸም። መዋቅሩ ደካማ ነው። አፍሪቃን እስቲ ከአንድ ባለኢንዱስትሪ ወይም በተፋጠነ ዕድገት ላይ ከሚገኙት ሃገራት አንጻር እንመልከት። እነዚህ አገሮች ከዜጎች ግብር ይሰበስባሉ። ግብሩ ደግሞ አንድ መንግሥት የራሱን ወጪ እንዲችል የግድ አስፈላጊ ነው። በውጭ ገንዘብ ላይ ጥገኛ ላለመሆን ከተፈለገ! እና የሚያሳዝን ሆኖ ለዚህ ተግባር ፍቱን የሆነ መዋቅር በአፍሪቃ የለም ማለት ይቻላል። ግብር በራሷ ሰብስባ ለመጠቀም የምትችለውና በኢንዱስትሪም ራመድ ያለችው ብቸኛዋ የክፍለ-ዓለሚቱ አገር ደቡብ አፍሪቃ ናት። አፍሪቃ በተወሰነ ጊዜ ወደተራመዱት ሃገራት ለመጠጋት በመቻሏ የሚያጠራጥረኝ ሌላ ነገር ደግሞ የዴሞክራሲ ተጠናክሮ አለመገንባት ነው። ይሄም ገዢዎች ከነተከታዮቻቸው ሁሉን ነገር እንዲቆጣጠሩ ያደርጋል። በአፍሪቃ እንግዲህ ጤናማ ዴሞክራሲ በእጣት በሚቆጠሩ የተወሰነ ነው”

በሌላ በኩል ትናንት በመድረኩ ጉባዔ ዋዜማ የወጣ አንድ የጥናት ውጤት በአፍሪቃ የውጭ መዋዕለ-ነዋይ እጅጉን እንደጨመረ አመልክቷል። ኤርንስት-ኤንድ-ያንግ የተሰኘው አማካሪ ቡድን ያቀረበው መረጃ እንደሚያሳየው የውጩ ቀጥተኛ መዋዕለ-ነዋይ ባለፉት ሰባት ዓመታት ውስጥ ከ 80 በመቶ በላይ ነው ያደገው። በትክክል በ 2003 ዓ.ም. 338 ይደርሱ የነበሩት ፕሮዤዎች ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ ወደ 633 ጨምረዋል።

መሥፍን መኮንን

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ