የወሲብ ጥቃቶችና የፍትህ አሰራር
ዓርብ፣ ጥር 9 2006የሕንድ ፖሊስ ይፋ እንዳደረገው አንዲት ጀርመናዊት እና ዴንማርካዊት በጥቂት ቀናት ልዩነት ወሲባዊ ጥቃት ደርሶባቸዋል። የ18 ዓመቷ ጀርመናዊት ደቡብ ህንድ ውስጥ በአንድ የማደሪያ የባቡር ፉርጎ ውስጥ ሳለች ነበር አንድ ወንድ ወሲባዊ ጥቃት እንደደረሰባት ፖሊስ ባለፈው ዕሮብ ዕለት የገለፀው። የደፈራትም በቁጥጥር ስር መዋሉ ተገልጿል። እንዲሁ ባለፈው ማክሰኞ በሀገር ጉብኝት ላይ የነበሩ የ51 ዓመት ዴንማርካዊት ደግሞ ወደ ሆቴላቸው በጉዞ ላይ ሳሉ መንገድ ተሳስተው መንገድ ሲጠይቁ የተወሰኑ ወንዶች በጩቤ አስፈራርተው ጭር ወደ አለ ስፍራ እንደወሰዷቸው እና ኋላም በቡድን እንደደፈሯቸው ተናግረዋል። ፖሊስ በመጀመሪያ 15 ወንዶችን ቃል እንዲሰጡ ካደረገ በኋላ 8ንቱን በቁጥጥር ስር አውሏል። አገር ጎብኚዋ ወዲያው ክስ መስርተዋል። ወይዘሮዋ በሀገራቸው ኤምባሲ ትብብር አግኝተውም ወዲያው ወደ ሀገራቸው መመለሳቸው ተገልጿል። የደረሰባቸውን በደል በግልፅ አውጥተው የከሰሱት የውጭ ሀገር ዜጎች ጉዳይ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ይፋ ይሁኑ እንጂ ህንድ ውስጥ በየቀኑ በርካታ ሰዎች ወሲባዊ ጥቃት ይደርስባቸዋል።
በሕንድ አንድ ሰው አስገድዶ መድፈሩ ከተረጋገጠ ከተወነጀለ እስከ የሞት ፍርድ ድረስ ሊበየንበት ይችላል። ይህ በኢትዮጵያስ ምን ይመስላል? በአራት የአቃቢ ህግ መስሪያ ቤቶች በተለይ በወንጀል ጉዳዮች ላይ ከ15 ዓመት በላይ ያገለገሉት አቶ ዮሀንስ ወልደገብርኤል በህግ ድንጋጌዎች ውስጥ አስገድዶ መድፈር ከፍተኛ ቅጣት የሚያስበይን ነው ይላሉ። እንደእየሁኔታው እና ክብደቱም ፍርዱ እስከ 25 ዓመት ፅኑ እስራት ሊያስበይን እንደሚችል አቶ ዮሀንስ ገልፀውልናል። ወሲባዊ ጥቃት ከምን ይጀምራል? በግብረ ሶዶማውያን የሚደፈሩ ወጣት ወንዶች ጉዳይስ ምን ይመስላል? ለዚህ እና ሌሎች ጥያቄዎች መልስ ሰጥተውናል።
ሌላው ያነጋገርናቸው የኢትዮጵያ ሕግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር የሥራ አስፈፃሚ ዳሬክተር የሆኑት ወ/ሮ ዜናዬ ታደሰን ነው። ወይዘሮዋ ወደ ማህበራቸው በርካታ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች እንደሚመጡ እና ከዚህም ውስጥ የወሲብ ጥቃት የደረሰባቸው እንደሚገኙ ገልፀውልናል። ወደ ማህበሩም የሚመጡት ሴቶች በተለያዩ የእድሜ ክልል የሚገኙ ናቸው ። ማህበሩም የግንዛቤ ማስጨበጥ አገልግሎት በመስጠት ይተባበሯቸዋል።
ወሲባዊ ጥቃትን በተመለከተ አብዛኛውን ጊዜ ሴቶች ከማያውቁት ሰው ይልቅ በሚያውቋቸው ሰዎች ጥቃት እንደሚደርስባቸው መዘርዝሮች ያመላክታሉ። አዳጊ ወጣቶች የወሲባዊ ጥቃት ሙከራን በጊዜ ተረድተው ርምጃ እንዲወስዱ ወ/ሮ ዜናዬ የሚመክሩት አለ።
በኢትዮጵያ የሚደርሱ የወሲብ ጥቃቶችና ያለውን የፍትህ አሰራር አስመልክቶ ያደረግነውን ሙሉ ዝግጅት ከድምፅ ዘገባው ያገኙታል።
ልደት አበበ
ነጋሽ መሐመድ