1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኮቪድ 19 ስርጭት በአዲስ አበባ መባባሱ

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 18 2013

ካለፉት አራት ሳምንታት ወዲህ አዲስ አበባ ውስጥ በኮቪድ 19 የሚያዙ እንዲሁም ሕይወታቸው የሚያልፍ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሄዱ ተሰምቷል። አንዳንድ ለኮቪድ 19 ህሙማን ተለይተው ማስታመሚያ እንዲሆኑ የተዘጋጁ የጤና ማዕከላት የጽኑ ሕሙማን መታከሚያ ክፍሎችም መሙላታቸውን ሃኪሞች እየገለጹ ነው።

https://p.dw.com/p/3zRBI
Äthiopien COVID-19-Kampagne
ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

ሦስተኛው የኮቪድ ማዕበል ስጋት

 

ኢትዮጵያ ውስጥ ከዓመት በፊት የኮሮና ተሐዋሲ በሌላው ዓለም በስፋት መሰራጨቱ እንደተሰማ የታየው ጥንቃቄ አሁን ላይ ተግባራዊ ቢሆን ኖሮ በተሐዋሲው ሕይወቱ የሚቀጠፈው ወገን ቁጥር ይቀንስ እንደነበር ትዝብታቸውን የሚገልጹ ጥቂት አይደሉም። ስለተሐዋሲው በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ሳይቀር በየዕለቱ ይቀርብ የነበረው መረጃ ብዙዎችን ስጋት ላይ በመጣሉ ተገቢውን ጥንቃቄ ለማድረግ የሚያመነታ ይኖራል ተብሎም አይገመትም። ውሎ ሲያደር ግለሰቦች ያደርጉት የነበረው ጥንቃቄ መላላት ሲጀምር በተሐዋሲው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በአንድ ጊዜ ማሻቀብ ጀመረ። በመንግሥት የሚተላለፉ የጥንቃቄ ደንቦች ያዝ ለቀቅ አይነት መሆናቸው  ስለበሽታው በቂ ግንዛቤ የሌለው አብዛኛው ኅብረተሰብ ችላ እንዲላቸው መንገድ የከፈተ ይመስላል የሚሉ ጥቂት አይደሉም ።ከብዙ ጥንቃቄዎች ጎን ለጎን የኮቪድ 19 መከላከያ ክትባትን ለአብዛኛው ዜጋቸው ባዳረሱ ሃገራት ዛሬም ተሐዋሲው መስፋፋቱን አልገታም። በዚህ ሁሉ የጥንቃቄ ርምጃ መካከል ኮቪድ 19 አይነቱን እየለወጠ መንሰራፋቱ በሚወራበት በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው ግዴለሽነት ውሎ አድሮ ዋጋ እንዳያስከፍልም ያሰጋል። ባለፉት አራት ሳምንታት በተሐዋሲው የተያዙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ፍጥነት መጨመሩንም የዚህ ማሳያ ለመሆኑ አያነጋግርም። በተለይ በዋና ከተማ አዲስ አበባ ከሚመረመሩ ሰዎች በተሐዋሲው የሚያዙ ሰዎችም ሆኑ የሚሞቱት ቁጥር  መጨመሩን ዶክተር ዮሐንስ ጫላ የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ኃላፊ ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል። እንደ ጤና ቢሮ ኃላፊው በየዕለቱ የሚታየው የታማሚዎች ቁጥር ከፍ ማለት የወረርሽኙ ሦስተኛ ማዕበል መነሳቱን ነው።

Äthiopien l Start der COVID-19-Impfung
ምስል Solomon Muchie/DW

ኤካ ኮተቤ አዲስ አበባ ውስጥ በኮቪድ 19 የተያዙ ሰዎች የሚታከሙበት ለዚሁ ሥራ የተለየ የህክምና ማዕከል ነው። ከአራት ሳምንታት በፊት የታማሚዎች ቁጥር ቀንሶ በማዕከሉ ህክምና ላይ የነበሩት ቁጥር በ20 እና 40 መካከል እንደነበር የህክምና ማዕከሉ ዋና የህክም አገልግሎት ኃላፊ ዶክተር ናትናኤል በኩረ ጽዮን ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል። የህክምና ማዕከሉ ካሉት ከእነዚህ ክፍሎች 30ዎቹ ለጽኑ ህሙማን መታከሚያ ሲሆኑ በአሁኑ ወቅት ሁሉም የጽኑ ህሙማን ክፍሎች እንደተያዙም አመልክተዋል። በዚህም በተሐዋሲው የሚያዙዎች ቁጥር መበራከት ይታያል። በኤካ ኮተቤ የኮቪድ 19 ህክምና ማዕከል ህመምተኞችን እየረዱ ከሚገኙ የህክምና ባለሙያዎች መካከል በተሐዋሲው የተያዙ ቢኖሩም እስካሁን የከፋ ነገር አልገጠመንምም ይላሉ ዶክተር ናትናኤል። ሃኪሞቹ ራሳቸውን ከተሐዋሲው ሊከላከሉበት የሚያስችላቸው ቁሳቁስ አቅርቦትን በተመለከተም አልተጓደለም ነው ያሉት። ስለተሐዋሲው ኅብረተሰቡ ያለውን ግንዛቤ አስመልክቶ ዘጋቢያችን ስዩም ጌቱ ካነጋገራቸው መካከል በአዲስ አበባ የኮልፌ አስኮ አካባቢ ነዋሪ የሆነው ተሾመ ደሳለኝ አንዱ ነው። ተሾመ በአሁኑ ወቅት የሚታየው የኅብረተሰቡ መዘናጋት ወረርሽኙ ስለመኖሩ የረሳ አስመስሎታል ባይ ነው። መሰረትም የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ናት። አብዛኛው ሰው የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ እንደማይጠቀም ታዝባለች።

Äthiopien Büro der Stadtverwaltung Addis Abeba
ምስል Seyoum Getu/DW

የኤካ ኮተቤ የኮቪድ ህሙማን መታከሚያ ማዕከል የህክም አገልግሎት ኃላፊ ዶክተር ናትናኤል በኩረ ጽዮን ኅብረተሰቡ ራሱንም ሆነ አብሮት የሚኖረውን ወገን ከዚህ ተሐዋሲ ሊከላከል ይገባል ሲሉ ይመክራሉ። ክትባትን በተመለከተ የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ከአንድ ሚሊየን በላይ ሰዎችን ለማዳረስ አቅዶ መዘጋጀቱን። ክትባቱንም በማንኛውም ሀኪምቤት ማግኘት እንደሚቻል ነው የተገለጸው። ዶክተር ዮሐንስ ጫላ የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ኃላፊ በቂ ክትባት አለ ነው ያሉት።

የጤና ሚኒስቴር ትናንት አመሻሹ ላይ ባወጣው ያለፉት 24 ሰዓታት የኮቪድ ምርመራ ውጤት መሰረት 6,353 ሰዎች ተመርምረው 927 ሰዎች በተሐዋሲው መያዛቸው ተረጋግጧል። 510 ሰዎች ደግሞ በጽኑ ህመም ላይ እንደሚገኙ አመልክቷል። እስካሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ባጠቃላይ 296,731 ሰዎች በተሐዋሲው መያዛቸው፤ 270,271 ደግሞ ከህመሙ ማገገማቸው፤ 4,571 ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸው ማለፉን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል። ከ2,3 ሚሊየን በላይም የኮቪድ 19 ክትባቶችን መውሰዳቸውንም ገልጿል። ተሐዋሲው መስፋፋቱን በማስመልከትም ከስድስት ዓመት በታች ከሆኑ ሕጻናት እና የመተንፈሻ አካል ችግር ካለባቸው ሰዎች በቀር በማንኛውም ስፍራ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ አለማድረግ መከልከሉን የሚያመለክት ድንጋጌ በድጋሚ ወጥቷል።  

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ