1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኮሌራ በሽታ ስጋት በኢትዮጵያ

ማክሰኞ፣ ግንቦት 27 2011

የኢትዮጵያ የጤና ጥበቃ ሚንስቴርና የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት ሰሞኑን ባወጡት መረጃ በኢትዮጵያ አራት ክልሎች እና በአዲስ አበባ ከተማ የኮሌራ በሽታ መከሰቱን አመልክተዋል። በሽታዉ እስካሁን ለዘጠኝ ሰዎች ሞት ምክንያት መሆኑም ተገልጿል።

https://p.dw.com/p/3JqOr
Hepatitis-B-Virus
ምስል picture-alliance/dpa

«የዘጠኝ ሰዎች ሕይወት አልፏል»

 በኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜዎች ድንገት በሚጀምር አጣዳፊ ተቅማጥና ተዉከት /አተተ/ በሽታ ሰዎች መጠቃታቸዉ ተደጋግሞ ይገለጻል። ሆኖም በሽታዉ ከኮሌራ ጋር ግንኙነት እንደሌለው ነበር ሲነገር የቆየው። ከሰሞኑ የጤና ጥበቃ ሚንስቴር እና የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት በቅርቡ ያወጡት መረጃ ግን በአተት ከተያዙ ሰዎች መካከል በኮሌራ የተያዙ መኖራቸውን በቤተሙከራ መረጋግጡን ጠቁመዋል። እንደመግለጫው በሽታዉ አዲስ አበባን ጨምሮ በአራት ክልሎች ታይቷል።
እንደ ዓለም ዓቀፉ የጤና ድርጅት ኮሌራ፤ ቫይብሮ ኮሌራ በተባለ ተዋሲ አማካኝነት የሚመጣና አንጀትን የሚያጠቃ በሽታ ነዉ። በሽታዉ በዚህ ተዋሲ በተበከለ ምግብና ውኃ አማካኝነት የሚመጣ ሲሆን በድንገት የሚጀምር የአጣዳፊ ተቅማጥ እና ተውከት ምልክቶቹ ናቸዉ። የሰውነት ፈሳሽን በማሟጠጥና አቅም በማሳጣት ተገቢዉ ህክምና ካልተደረገ በጥቂት ስዓታት ውስጥ ለሞት ሊዳርግ የሚችል በሽታም ነዉ ኮሌራ። በሽታዉ ተላላፊና በወረርሽኝ መልክ የሚከሰት ሲሆን የበሽታዉ ምልክት መታየት ከጀመረ  ባሉት አምስት ቀናት ውስጥ የመግደል ሀይሉ ከፍተኛ መሆኑን የዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት መረጃ ያሳያል። ይህ በሽታ በኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ  በአማራ፣ በትግራይ፤ በኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልሎች እንዲሁም  በአዲስ አበባ ከተማ መታየቱን የኢትዮጵያ  ጤና ጥበቃ ሚንስቴር አስታዉቋል። ሚንስትሩ ዶክተር አሚር አማን በተለይ ለዶይቼ ቬለ DW እንደገለፁት በተጠቀሱት ቦታዎች በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች በአጣዳፊ ተቅማጥና ትዉከት ተይዘዋል። ከነዚህም  መካከል በዘጠኝ  ሰዎች ላይ የኮሌራ በሽታ ተገኝቷል።

«ኢትዮጵያ ዉስጥ በአራት ክልሎችና በአዲስ አበባ ወደ 366 ሰዎች እስከዛሬ ድረስ ባለዉ መረጃ በአተት ተይዘዋል።እነዚህ የታመሙ ሰዎችም ህክምና እንዲያገኙ ተደርጓል።ከነዚህም ዉስጥ በዘጠኝ ሰዎች ላይ በደረገዉ ምርመራ የኮሌራ ተገኝቶባቸዋል።» ብለዋል። በበሽታዉ ዘጠኝ ሰዎችም ህይወታቸዉ አልፏል።

የኢትዮጵያ የጤና ጥበቃ ምንስቴርና የኅብረተሰብ ጤና ተቋም የኮሌራ በሽታ መከሰቱን  ካሳወቁ  ካለፉት ሦስት ቀናት ወዲህ በሽታዉ በኅብረተሰቡ ዘንድ ካሳደረዉ ስጋት ባሻገር አተት ኮሌራ በሚለዉ ቃል ተቀየረ እንጅ በፊትም ቢሆን በሽታዉ ነበር የሚለዉ መነገጋሪያ ሆኖ ነው የሰነበተዉ። እናም አተት ኮሌራ ነዉን? አልናቸው ዶክተር አሚርን።


Flash-Galerie Somalische Flüchtlinge im Lager Dolo Ado Äthiopien
ምስል DW

«በላብራቶሪ በአጠቃላይ የሰገራ ምርመራ ተደርጎ መነሻዉ ምን እንደሆነ እስኪታወቅ ድረስ በምልክቱ ብቻ  አንድ ሰዉ በተደጋጋሚ ካስቀመጠዉና የሚያስታዉክ ከሆነ ያ ደግሞ አጣዳፊ ከሆነ አተት ይባላል።በላብራቶሪ ሲታይ መነሻዉ ቫይብሮ ኮሌራ የሚባል ተዋህሲ ከሆነ ኮሌራ ይባላል » ሲሉ ነበር የገለፁት። ነገር ግን ኮሌራ ሁሉ አተት ይሆናል።አተት ሁሉ ግን ኮሌራ አይደለም ሲሉም አክለዋል። 

የበሽታዉ ምልክቶች አጣዳፊ ተቅማጥና ተውከት፣ራስ ምታት፣ የቆዳ መሸብሸብ ሲሆኑ፤ ምልክቶቹ የታዩበት ሰዉ በአፋጣኝ ወደ ጤና ተቋም መሄድና በቂ ፈሳሽ መውሰድ እንደሚኖርበት ባለሙያዎቹ ይመክራሉ። በሽታውን ለመከላከልም የግልና የአካባቢ ንፅህናን መጠበቅ፣ መጸዳጃ ቤት ደርሰው ሲመለሱም ሆነ ከመመገብ አስቀድሞ እጅን ቢቻል በሳሙና ካልሆነም በውኃ በደንብ መታጠብ፤ ምግብን በደንብ አብስሎ መመገብ እና የመመገቢያ ቁሳቁሶችን በንፅህና መያዝ፤ እንዲሁም ውኃን በማፍላት ወይም በማከም መጠቀም ይመከራል።
የንፅህና ጉድለት እንዲሁም ንፁህ የመጠጥ ውሃና የምግብ  እጥረት ከበሽታዉ ጋር በቀጥታ የሚያያዙ በመሆናቸዉም ኮሌራ የድህነት በሽታ በሚልም ይታወቃል።
የዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየዉ የኮሌራ በሽታ ከጎርጎሮሳዊው 2005 ዓ/ም ጀምሮ በድሃ ሀገሮች እየጨመረ መጥቷል። በተለይ ኢትዮጵያን በመሳሰሉ  መሠረተ ልማቶች ባልተሟሉባቸው ሃገራት ከንፁህ መጠጥ ዉኃ እጥረት ጋር ተያይዞ የአካባቢና የግል ንፅህናን ለመጠበቅ አስቸጋሪ በሆነባቸዉ ቦታዎች በሽታዉ የከፋ ጉዳት ያደርሳል። በሽታው በንፅህና  እና ጥንቃቄ ጉድለት ሰዎች ተፋፍገዉ በሚኖሩባቸዉ ቦታዎች የመዛመት ዕድሉ ከፍተኛ በመሆኑም በወረርሽኝ መልክ የሚከሰትባቸው ጋጣሚዎች ከፍተኛ ናቸው። በዚህ ረገድ ከቀያቸዉ ተፈናቅለዉ በአንድ አካባቢ ሰፍረዉ በሚገኙ ሰዎች ላይ ሊያስከትል የሚችለው አደጋም በቀላል  የሚታይ አይደለም።
 በሌላ በኩል ከመጭዉ ክረምት ጋር ተያይዞ በአዲስ አበባ ከተማ 169 ቦታዎች የጎርፍ አደጋ ሊከሰት እንደሚችል የእሳትና ድንገተኛ አደጋ በቅርቡ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። የንፁህ መጠጥ ውኃ አቅርቦትን በተመለከተም በከተማዋ ውኃ በፈረቃ የሚያገኙ አካባቢዎችም ብዙ ናቸዉ። እነዚህንና የመሳሰሉት አባባሽ ምክንያቶች ባሉበት በሽታዉ የከፋ ጉዳት ሳያስከትል ለመከላከል አስቸጋሪ ይመስላል። የጤና ጥበቃ ሚንስትሩ ዶክተር አሚን እንደሚሉት ግን ሁኔታው የቱንም ያህል አስቸጋሪ ቢሆንም ከክረምቱ መምጣት ጋር ተያይዞ አተትንም ሆነ ኮሌራን ለመከላከል እንዲሁም በሽታዉ ሲከሰት ህመምተኞች  በቶሎ ህክምና እንዲያገኙ ለማድረግ ኅብረተሰቡን እና የተለያዩ መስሪያ ቤቶችን ያሳተፈ በክልሎች በምክትል ርዕሰ መስተዳድሮች የሚመራ በአዲስ አበባ ደግሞ በከተማዋ ከንቲባ የሚመራ ሥራ ተጀምሯል። የበሽታዉ መነሻ ሰዎች በብዛት የሚሰባሰቡባቸዉ ቦታዎች በተለይም የሃይማኖት ቦታዎች በመሆናቸዉ ከሃይማኖት አባቶች ጋር በመሆን በመስጊዶችና በፀበል ቦታዎች የጥንቃቄ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

Äthiopien Cholera-Ausbruch
ምስል DW/Y. Geberegziabeher


በተለያዩ ቦታዎች ከቤት ንብረታቸዉ የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመርዳት እና የወደሙ የጤና ተቋማትን መልሶ ለመገንባትም ከሰላም ሚንስቴር ጋር በጋራ እየተሠራ ሲሆን፤ ለዚህም ግብረ ሀይል መቋቋሙን አመልክተዋል። ለበሽታዉ የሚሰጠዉን ክትባት በተመለከተም  የኢትዮጵያ የጤና ጥበቃ ምንስቴር ከዓለም የጤና ድርጅት ጋር በመነጋገር በሽታዉ ሊከሰት ይችላል በሚል ስጋት የዳሰሳ ጥናት ቀደም ብሎ ማድረጉን የገለፁት ዶክተር አሚን በጥናቱ መሠረት 730 ሺህ ክትባት ከለጋሾች መገኘቱን ጠቅሰዋል። የኮሌራ በሽታ ከተከሰተ ወዲህም ተጨማሪ ክትባት ለማግኘት ጥያቄ መቅረቡን አመልክተዉ 130 ሺ ተጨማሪ ክትባት በቅርቡ ወደ ሀገር እንደሚገባ ገልፀዋል። ወደፊትም በሀገሪቱ በቋሚነት ከሚሰጡ 11 የክትባት አይነቶች በተጨማሪ የኮሌራ ክትባትን ተጋላጭ ለሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች በመደበኛነት ለመስጠት መታቀዱን አስረድተዋል።

Impfaktion für Jugendliche
ምስል picture-alliance/dpa/B. Roessler


ኮሌራ ክትባት ካላቸዉ በሽታዎች አንዱ በመሆኑ ቀድሞ ለመከላከል ከሚደረግ ጥንቃቄ ጎን ለጎን ክትባት ዓይነተኛዉ መፍትሄ ቢሆንም የክትባቱ ዋጋ ውድ ፤ በዓለም ላይ ያለዉ አቅርቦትም አነስተኛ መሆኑን የአልም አቀፉ የጤና ድርጅት ዘገባ ያሳያል። ስለሆነም የግል እና የአካባቢ ንፅህናን በመጠበቅ በሽታዉን መከላከል ቀላሉና ብዙ ወጭ የማያስወጣ መፍትሄ መሆኑን የህክምና ባለሙያዎች አበክረው ይመክራሉ። ለዚህም  የኅብረተሰብ ጤና ትምህርቶችን ማዳረስ፣ የኅብረተሰቡን የኑሮ ሁኔታ የሚያሻሽሉ እና ከድህነት የሚያወጡ የኢኮኖሚ አማራጮችን መፍጠር እንዲሁም መፈናቀልን የሚያስከትሉ ግጭቶችን በማስቆም በሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን መሥራት መፍትሄ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።

ሙሉ ቅንብሩን የድምጽ ማዕቀፉን ተጭነዉ ያድምጡ።

 

ፀሐይ ጫኔ

ሽዋዬ ለገሰ