የኬንያ ምርጫና ማህበራዊ ብዙሃን መገናኛ
ሐሙስ፣ ጥር 23 2005በኬንያ የፊታችን መጋቢት ምርጫ ይካሄዳል ። ምርጫው የሃገሪቱን ዲሞክራሲ የሚያጎለብት ትልቅ እርምጃ ተደርጎ ነው የተወሰደው ። በመጋቢቱ ምርጫም በርካታ የአዲሱ ህገ መንግሥት ማሻሻያዎች ተግባራዊ ይሆናሉ ። የምርጫ ጣቢያዎች ቅነሳ ፣ ለሴቶች የተሰጠው ኮታ ፣ እና የቀበሌ ምክር ቤቶች መቋቋም እስካሁን ለትልቁ የፕሬዝዳንትነት ሥልጣን የሚደረገውን የኃይል እርምጃን ያካተተ ትግል ለመከላከል እገዛ ያደርጋሉ ተብሎም ይታመናል ። በሌላ በኩል ባለፉት 5 አመታት በርካታ ኬንያውያን ኢንተርኔትን በምርጫ ዘመቻ በንቃት ለመሳተፍ እየተጠቀሙበት ነው ። የዶቼቬለዋ ማያ ብራውን ማህበራዊ ብዙሃን መገናኛ በኬንያ ዲሞክራሲ እድገት ላይ ስላሳደሩት ተፅዕኖ ያዘጋጀችውን ዘገባ ሂሩት መለሰ አጠናቅራዋለች ።
ማዕከላዊ ናይሮቢ በሚገኝ ጎዳና በየምሽቱ ከሥራ ተባዕት ኬንያውያን ፣ ማን ለምን የትኛውን እጩ ተወዳዳሬ እንደሚደግፍ ይነጋገራሉ ።
በየጎዳናው የሚሆነው በተመሳሳይ ጊዜ በኢንተርኔት የሚካሄደውን ህይወት ያለው ውይይት ያንፀባርቃል። ኬንያውያን ማህበራዊ ብዙሃን መገናኛ ማለትም ብሎጎች ፌስቡክ ና ትዊተርን በፖሊሲዎች ላይ ክርክር ለማካሄድ ይጠቀሙባቸዋል ። ፖለቲከኞችም ከረዥም ጊዜ አንስቶ የዚሁ አገልግሎት ተጠቃሚዎች ናቸው ። የት እንዳሉና ምን እንደተናገሩ በየሰአቱ በፌስቡክ ያሳውቃሉ ። አንዳንዶች ደግሞ በትዊተር አጫጭር መልዕክቶችን ያስተላልፋሉ ከህዝቡ ጋርም ይነጋገራሉ ። በዚህ ሂደትም ብዙዎች ትችቶችን ይቀበላሉ ። ኬንያዊው የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ና የመብት ተሟጋች ምዋሊሙ ማቲ ማህበራዊ ብዙሃን መገናኛ ጠቃሚ ጎኖች እንዳሏቸው ሁሉ ጎጂ ጎኖች እንደማያጡም ይናገራሉ ።
« በርካታ ፖለቲከኞች ማህበራዊ ብዙሃን መገናኛን በምርጫ ዘመቻ መድረክነት እየተጠቀሙበት ነው ። ስለራሳቸው ና ስለእቅዳቸውም ይበልጥ እየተናገሩበት ነው ። ሆኖም በማህበራዊ ብዙሃን መገናኛ ስለ ፖለቲከኞች እቅድ መናገር የሚቻለው የተገደበ ነው ። ያም ሆኖ እንደሚመሰለኝ ይህ ለፖለቲከኞቹ አነሰም በዛም ሜዳውን ያስተካክላል ። ምክንያቱም ሃብት የሌላቸው እጩ ተወዳዳሪዎቹም ከህዝቡ ጋራ የሚገናኙበትን መንገድ እንዲፈልጉም ያስችላቸዋል »
ሆኖም ማቲ እንደሚሉት ተፅእኖው ኤሌክትሪክና የኢንተርኔት አገልግሎት ማግኘት በሚችሉ ከተሞች ብቻ የተገደበ ነው ። ከዛሬ 5 አመቱ የኬንያ ምርጫ ወዲህ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ቁጥር በጣም አድጓል ። በኬንያ ማስታወቂያ ሚኒስቴር መረጃ መሰረት 14 ሚሊዮን ኬንያውያን ማለትም ከህዝቡ 30 በመቶው የኢንተርኔት ተጠቃሚ ነው ። ከ 5 አመት በፊት ግን ወደ 5 በመቶ ገደማ ብቻ ነበር ።
በኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ቁጥር ማደግ በርካታ የሲቪል ማህበራት ብዙ ጥቅሞች አግኝተዋል ። ይህም በአንዳንዶች አስተያየት የፖለቲካውን ምህዳር አስፍቶታል ። ቦኒፌስ ምዋንጊን የመሳሰሉ አንዳንድ የመብት ተሟጋቾች ፌስቡክን ለሠላማዊ ሰልፍ ጥሬ ይጠቀሙበታል ። ሆኖም በርሳቸው አስተያየት ፌስቡክ ከዚህ ለላቀ ጉዳይ በቂ አይደለም ።
« ማህበራዊ ብዙሃን መገናኛ የሚያሳድሩት ተፅእኖ በጣም ዝቅተኛ ነው ። ለመጮህና ድምፅን ለማሰማት ጥሩ ቦታ ነው ። ሆኖም ውጤታማ መሆኑን በጣም እጠራጠራለሁ ። ሌላው ለአሁኑ አሳሳቢው ጉዳይ ትክክለኛው ኃይል የሚገኘው ከነዚህ መድረኮች ውጭ መሆኑ ነው ። በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በትዊተር ከሚፃፉ ስሞታዎች ይልቅ ሰዉን አሰባስቦ መፈክር ይዞ ወደ ጎዳና መውጣቱ የተሻለ ነው »
በኬንያ ማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን እንደሚነበበውና እንደሚሰማው ፕሬዝዳንታዊ እጩ ማርታ ካሩዋ የተሻለ የማሸነፍ እድል ሊኖራቸው ይገባ ነበር ። የቀድሞዋ የፍትህ ሚኒስትር ካሩዋ እነዚህን መድረኮች በመጠቀም ቀዳሚዋ ከመሆናቸውም በላይ ለምርጫ ዘመቻቸውም ብዙ ገንዘብ አሰባስበውበታል ። ሆኖም ከህዝብ በተሰበሰበ አስተያየት መሰረት ግን አሁንም ወደ ኃላኛው ስፍራ ላይ ነው የሚገኙት ። ለሁሉም ክፍት የሆኑትን ማህበራዊ ብዙሃን መገናኛ በኬንያው የጎሳ ፖለቲካ ለማራመድ አለአግባብ
የሚጠቀሙባቸውም አሉ ። ከአሁኑ እንኳን ባለፈው ምርጫ ወቅት የነበረውን አይነት ስሜት የሚቀሰቅሱ ፅሁፎች ይወጣሉ ። ባለፈው ምርጫ ከተከሰተው ብጥብጥ በኋላ ጥላቻን የሚቀሰቅሱ ንግግሮች በህግ ተከልክለዋል ። በርካታ ተቋማት እነዚህ መሰል ንግግሮች ወይም ፅሁፎች ህጉን የሚፃረሩ መሆን አለመሆናቸውን ይከታተላሉ ። ከነዚህም አንዱ ብሔራዊ የህብረትና የውህደት ኮሚሽን ነው ። ሊቀ መንበሩ ማዛሌንዶ ኪቡንጃ በማህበራዊ ብዙሃን መገናኛ የሚሰራጩ መልዕክቶች ጥንቃቄዎች የሚያሻቸው መሆናቸውን ነው የሚያሳስቡት ።
« በምንም አይነት ጉዳይ ላይ ዘመቻ ስናካሂድ ጥንቃቄ ማድረግ አለብን ። የምርጫ ዘመቻ በሚካሄድበት መንገድ ላይ ጥንቃቄ ማድረግ ያሻል ። ያ ብቻ አይደለም ግለሰቦች የሚናገሩትም ሁሉ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል ። የፖለቲከኞቹ ንግግር የተገደበ ሊሆን ይገባል ።ምክንያቱም ምን ሊያጋጥም እንደሚችል አታውቅም »
መንግሥት ማህበራዊ ብዙሃን መገናኛ እንደሚከታተል በቅርቡ በሰጠው ዝርዝር መግለጫ አስታውቋል ። ዘለፋም ሆነ ማስፈራሪያ ያላቸው መልዕክቶች ፀሃፊዎች ከባድ ቅጣት ይተላለፍባቸዋል ።
ሂሩት መለሰ
ተክሌ የኋላ