1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኬንያና የዩጋንዳ የነዳጅ ቧምቧ ዉል

ረቡዕ፣ ነሐሴ 6 2007

ኬንያና ዩጋንዳ የነዳጅ ማስተላለፊያ ለመገንባት ተስማሙ። ዩጋንዳ እ.ኤ.አ. በ2018 ለመጀመር ያቀደችውን የድፍድፍ ነዳጅ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ በሞምባሳ አሊያም ወደ ላሙ ወደቦች የሚገነባውን ማስተላለፊያ ግንባታ ወጪ ከኬንያ ይጠበቃል ተብሏል።

https://p.dw.com/p/1GESo
Symbolbild - Erdöl
ምስል Getty Images/J. Raedle

[No title]


ኬንያና ዩጋንዳ የነዳጅ ማስተላለፊያ ለመገንባት ከስምምነት ደርሰዋል። የዩጋንዳን ድፍድፍ ነዳጅ ወደ ኬንያ የባህር በር ለማድረስ የሚያስችል ማስተላለፊያ ለመገንባት የተደረሰው ስምምነት በዘርፉ ለተሰማሩት ኩባንያዎች ከውሳኔ ለመድረስ የሚያስችል ነው ሲሉ የሁለቱ አገሮች ፕሬዝዳንቶች መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል። በዚህ ስምምነት መሰረት ኬንያ በክልሏ ለሚገነባው ማስተላለፊያ የደህንነት ጥበቃ የማድረግ ግዴታ የሚኖርባት ሲሆን አስፈላጊውን የግንባታ ገንዘብም ታፈላልጋለች። ከማስተላለፊያ ግንባታው በኋላ ዩጋንዳ ለኬንያ የምትከፍለው ክፍያ በሌሎች አማራጮች ሊከፈል ከሚችለው መጨመር እንደማይኖርበትም ከስምምነቱ መካተቱን ሮይተርስ ዘግቧል።
ዩጋንዳ ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በምትዋሰንበት ምዕራባዊ ክፍል 6.5 ቢሊዮን በርሜል የሚገመት የድፍድፍ ነዳጅ ይዞታ እንዳላት የሚገመት ሲሆን የኬንያ ሊለማ የሚችል አንድ ቢሊዮን በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ በከርሰ ምድሯ እንዳላት ይገመታል።
ሁለቱ የምስራቅ አፍሪቃ አገሮች ባለፈው አመት የድፍድፍ ነዳጅ እንዳላቸው ከታወቀ ጀምሮ ቀድሞ የማልማት ፍክክር ውስጥ እንደገቡ ይነገራል። ዩጋንዳም ሆነ ኬንያ የድፍድፍ ነዳጅ ሃብታቸውን በአግባቡ ማልማት ከቻሉ የአገራቱን ገቢ ለማሳደግና የስራ እድል ለመፍጠር ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ተብሏል። የዩጋንዳ ፔትሮሊየም ዳይሬክቶሬት ቃል አቀባይ በሺር ሃንጌ አሁን የተፈረመው ስምምነት አገሪቱ ያላትን ሀብት ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እንደሚያግዛት ተናግረዋል።
«የዩጋንዳ መንግስት ሲኖክና ታሎው ከተሰኙ ኩባንያዎች ጋር የአገሪቱ ነዳጅ ለግብይት በሚቀርብበት ሁኔታ ላይ የመግባባቢያ ሰነድ ተፈራርሟል። በመግባቢያ ሰነዱ የነዳጅ ማጣሪያ በዩጋንዳ ለመገንባት ከስምምነት የተደረሰ ሲሆን የድፍድፍ ነዳጅ ማጓጓዣም ይኖራል። ስለዚህ አሁን በዩጋንዳና ኬንያ መካከል የተደረሰው ስምምነት የዩጋንዳን ነዳጅና ዘይት ለውጭ ገበያ ለማቅረብ በር ይከፍታል።»

በአሁኑ ስምምነት መሰረት ለማስተላለፊያው ግንባታ ሁለት አቅጣጫዎች በአማራጭነት ቀርበዋል። አንደኛው አሁን የነዳጅ ምርቶች ማስተላለፊያ የሚገኝበትን መስመር ተከትሎ በኬንያ ደቡባዊ አቅጣጫ ወደ ሞምባሳ ነው። ሁለተኛው ኬንያ አዲስ ልትገነባ ወዳቀደችበት የላሙ ወደብ የሚያቀና ሲሆን በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል ይሆናል። ይሁንና ሰሜናዊው ኬንያ ከሶማሊያ ጋር የምትዋሰንበት አካባቢ በመሆኑ የጸጥታ ስጋት አለበት።

በዓለም ገበያ የነዳጅ ዋጋ ማሽቆልቆል አዳዲስ የነዳጅ ፍለጋና ልማት ስራዎችን አትራፊነት ጥያቄ ውስጥ ከቷል። ይሁንና የዩጋንዳና ኬንያ የሚገኙት በሌሎች የባህር ዳር አካባቢዎች ከሚደረጉ ፍለጋዎች በተሻለ በቀላሉና በርካሽ የሚሰሩ በመሆናቸው አዋጭ እንደሚሆኑ ተንታኞች ይናገራሉ። የዩጋንዳ ፔትሮሊየም ቃል አቀባዩ በሺር ሃንጌ አሁን የተፈረመው ስምምነት ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዳለው ይናገራሉ።
«ይህ ለዩጋንዳ እንዲሁም ለቀጣናው ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል። ምክንያቱም የድፍድፍ ነዳጅ ዘይታችንን ለውጭ ገበያ በማቅረብ እጅጉን አስፈላጊ የሆነውን የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ያስችለናል። ሁሉም ድፍድፍ ነዳጅ ለውጭ ገበያ አይቀርብም። የተወሰነውን በአገር ውስጥ የምናጣራ ይሆናል።»
በኬንያና ዩጋንዳ የብሪታኒያ፤ፈረንሳይና ቻይና ኩባንያዎች በነዳጅ ፍለጋ ስራ ላይ ተሰማርተዋል። ዩጋንዳ በምስራቃዊ የአገሪቱ ክፍል ሆዪማ በተባለች አነስተኛ ከተማ በቀን 30,000 በርሜል የማጣራት አቅም ያለው የድፍድፍ ነዳጅ ማጣሪያ የመገንባት እቅድ አላት። ይህ የድፍድፍ ማጣሪያ የአገሪቱን ፍላጎት ከማሟላት ባሻገር ለቀጣናው የግብይት ማዕከል ይሆናል ተብሏል።

እሸቴ በቀለ
አርያም ተክሌ

Kenianischer Präsident Uhuru Kenyatta
ምስል picture-alliance/AA
Uganda Präsident Museveni
ምስል AP