የእስራኤል ጥቃት እንዲቆም ተጠየቀ
ዓርብ፣ ኅዳር 7 2005እስራኤል በጋዛ የምትሰነዝረውን ጥቃት እንዲያስቆሙ የአለም መንግሥታት ተጠየቁ ። ዛሬ በጋዛ አጭር ጉብኝት ያደረጉት የግብፅ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃሺም ካንዲል የአለም መንግሥታት እስራኤልን አንድ እንዲሉ ተማፅነዋል ። በቦምብ የተደበደበውን የጋዛ ክፍል የጎበኙትና ዛሬ በተፈፀመ ጥቃት ተገድለዋል የተባሉትን ሰዎች አስከሬን ያዪት ካንዲል የተኩስ አቁም ስምምነቱ እንዲፀናና እስራኤልም ጥቃቱን እንድታቆም ግብፅ ጥረቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል ተናግረዋል ። በካንዲል የጋዛ ጉብኝት ወቅት ስምምነት ላይ የተደረሰበት ተኩስ አቁም ወዲያውኑ ተጥሶ ሰሜን ጋዛ ውስጥ በተፈፀመ የእስራኤል የአየር ጥቃት 2 ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል ። ሆኖም ሃማስን ስምምነቱን በመጣስ የወነጀለችው እስራኤል ዛሬ የአየር ጥቃት አልፈፀምኩም ብላለች ። የእስራኤል ጦር ቃል አቀባይ ከ60 በላይ ጓዳ ሰራሽ ሮኬቶች ወደ እስራኤል እንደተተኮሱ ተናግረዋል ። ሃምስ በበኩሉ 40 ሮኬቶች መተኮሳቸውን አምኗል ። እስራኤል ዘመቻዋን
በማጠናከር 16 ሺህ ተጠባባቂ ወታደሮቿን ጠርታለች ። የእስራኤል ካቢኔ አባል ሞሼ ያሎን መንግሥታቸው የሚሰነዘረውን የሮኬት ጥቃት ከነአካቴው ለማስቀረት እግረኛ ጦሯን ለማዝመት እያሰላሰለ መሆኑን ተናግረዋል ። የአውሮፓ ህብረት ሃማስን አውግዞ የእስራኤልም እርምጃም ተመጣጣኝ እንዲሆን ጥሬ አቅርቧል ። የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳዮች ሃላፊ ካትሬን አሽተን ሃማስና ሌሎችም ቡድኖች ወደ እስራኤል ሮኬቶች መተኮሳቸው ፍፁም ተቀባይነት እንደሌለው አስታውቀው መቆም አለበትም ብለዋል ። ህዝቧን ከጥቃት የመከላከል መብት አላት ያሏት እስራኤልም የምትወስደው እርማጃ ተመጣጣኝ እንዲሆን ጠይቀዋል ።
ሂሩት መለሰ
ተክሌ የኋላ